የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) የኢትዮጵያ ኃላፊ “የድርጅቱን እሴቶች የማያንጸባርቅ” አስተያየት በመስጠታቸው ምክንያት አስተዳደራዊ እረፍት እንዲወስዱ መደረጉን ተቋሙ ለቢቢሲ አስታወቀ።

ቢቢሲ ጉዳዩን በተመለከተ አይኦኤምን ጠይቆ ባገኘው ምላሽ ኃላፊዋ ማውሪን አቺየንግ “የድርጅቱን እሴቶች በማያንጸባርቅ ሁኔታ የግል አስተያየታቸውን በማጋራታቸው ጉዳዩ ምርመራ አስኪደረግበት ድረስ አስተዳደራዊ እረፍት ላይ ናቸው” ብሏል። ኃላፊዋ ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ “ያልተፈቀደ ቃለ መጠይቆችን” አድርገዋል በሚል የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ አስተዳደራዊ እረፍት እንዲወስዱ ማድረጉን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተመለከትኩት ያለውን ከድርጅቱ የወጣን ደብዳቤ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ማውሪን አቺየንግ ያልተፈቀደ በተባለው ቃለ መጠይቅ ለትግራይ ኃይሎች ርህራሄ አላቸው ባሏቸው የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች ወደ ጎን ገሸሽ መደረጋቸውን ተናግረዋል። ይህንንም አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ አቀባይ ቢልለኔ ስዩም “የተባበሩት መንግሥታት ሥርዓት ከሽብርተኛው ቡድን ህወሓት ጋር ባለው ግንኙነት ተቋማዊ አድሏዊነትን መከተሉን በግልፅ በመናገራቸው ማውሪን አቺየንግ ላይ የተጣለው አስተደዳራዊ እረፍት በጣም የሚረብሽ ነው” ብለዋል።

አክለውም “በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ በከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች ያለው ውስጣዊ እና የውጭ ተፅእኖ ፓለቲካ በጥልቀት መመርመር እንዳለበት” በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል። የኃላፊዋ ከሥራ ኃላፊነታቸው መነሳት በያዝነው ሳምንት ሰኞ በተፃፈና የዜና ወኪሉ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በተመለከተው ደብዳቤ የተረጋጋጠ ሲሆን በበለጠ የእርዳታ ሥራውን እንደሚያዳክመውም ተጠቅሷል።

በቅርቡ ኢትዮጵያ “በውስጥ ጉዳዮቼ ጣልቃ ገብተዋል” ያለቻቸውን ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞችም መባረር ድርጅቱ ለሰብአዊ እርዳታ በሚሰጠው ምላሽ ላይ እክል እንደሆነበትም ሰፍሯል። ባለፈው ሳምንት ማውሪን አቺየንግና እና ሌላ ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኛ የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ላይ የሚያደርገውን ጦርነት በመደገፍ በርካታ መጣጥፎችን ለሚፅፈው ጄፍ ፒርስ ረዘም ያለ ቃለ መጠይቅ ሰጥተዋል። በቃለ መጠይቁ ላይ እንደሚሰማው የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ኃላፊ ማውሪን ጦርነቱ ከተነሳ በኋላ አዲስ አበባ የገቡ የተባበሩት መንግሥታት የሥራ ባልደረቦቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ በመተቸት መሬት ላይ ያሉ የድርጅቱ ተወካዮችን አግልለዋል ብለዋል።

ህወሓትንም “ቆሻሻ” እና “ጨካኝ” በማለትም ሲሳደቡ ይሰማል። በአንድ ወቅትም ህወሓት ከሳዑዲ አረቢያ የተባረሩ የትግራይ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ እንዲላኩ አሲረዋል በማለትም ሲከሱ ይሰማል። በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የነበሩና መውጪያ አጥተው የነበሩ የትግራይ ተወላጅ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ እንዲላኩ ጥያቄ እንደቀረበላቸውና ሩዋንዳም እንዲላኩ የተፈለገው ለሌላ አላማ እንደሆነ ሲናገሩም ይደመጣል።

“እናም ከዚያ የሽምቅ ውጊያ እንቅስቃሴ ከሩዋንዳ እንደሚጀመር አታውቅም ማለት ቆሻሻ ነው” ይላሉ። ኃላፊዋ በጭራሽ ወደ ትግራይም እንደማይመለሱ ቃል ሲገቡም ይሰማል። ባለፈው ሳምንት ኤኤፍፒ በተመለከተውና ለሥራ ባልደረቦቻቸው በታየ የውስጥ ማስታወሻ፣ ኃላፊዋ በበኩላቸው “በጥልቅ ተረብሻለሁ እናም አዝኛለሁ” ካሉ በኋላ “በስውር እንደተቀዳና ተመርጦ አርትፆት እንደተደረገበት” ተናግረዋል።

ነገር ግን በቃለ መጠይቁ ወቅት በበርካታ ነጥቦች ላይ ተሳታፊዎቹ እየተቀዳ መሆኑን በግልፅ ሲወያዩም ይሰማል። ሰኞ እለት የአይኦኤም ዋና ዳይሬክተር አንቶኒዮ ቪቶሪኖ የኃላፊዋን አስተያየቶች አስመልክቶ ደብዳቤ ፅፈዋል። “በድምፁ ላይ በድርጅቱ አባል የተሰጡት አስተያየቶች ከአይኦኤም መርሆች እና እሴቶች ጋር አይዛመዱም፣ በምንም መልኩ የድርጅቱ አቋም እንደተገለጸ ተደርጎ መታየት የለበትም” ብለዋል።

ደብዳቤው ማውሪን አቺየንግን በስም የማይጠቅስ ቢሆንም ምርመራው እስኪካሄድ ድረስ ወዲያውኑ እንደተጠሩ እና የአስተዳደር እረፍት ያደርጋሉ ተብሏል። ኢትዮጵያ ከሰሞኑ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ቀውስ ጋር ተያይዞ በወገንተኝነትና እንዲሁም ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ደቅነዋል ያለቻቸውን የተመድ ሰባት ሠራተኞች ከአገር እንዲወጡ ማድረጓ ይታወሳል።

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) የኢትዮጵያ ተወካይ አደል ኾደርን ጨምሮ ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት ከፍተኛ የተመድ ሠራተኞች ባለፈው ሳምንት አገሪቱን ለቀው ወጥተዋል። ይህንንም አስመልክቶ የጸጥታው ምክር ቤት የመከረበት ሲሆን ዋና ጸሓፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከአገር እንዲወጡ ለተደረጉበት ክሶች ማስረጃ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል። “ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን እየጣሰች ነው ብለን እናምናለን። ሰባቱን የተመድ ሠራተኞች የማባረር ሥልጣን የላትም። የኢትዮጵያ መንግሥት አንዳንድ የተመድ ሠራተኞች ወገንተኛ ናቸው ወይም የሰብአዊ እርዳታ መርህን ጥሰዋል ብሎ የሚያምን ከሆነ ከመንግሥት ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ነን” በማለት አብራርተዋል።

በወቅቱም ምላሽ የሰጡት የተመድ የኢትዮጵያ ልዑክ የሆኑት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ስለ ውሳኔዎቿ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ የመስጠት ሕጋዊ ግዴታ እንደሌለባት አስረድተዋል። “ኢትዮጵያ ያባረረቻቸው የተመድ ሠራተኞች የሙያ ሥነ ምግባራቸውን ገሸሽ አድርገው ተገኝተዋል። የሰብአዊ እርዳታ መርህንም ጥሰዋል” ሲሉም ተናግረዋል። በሰሜን ኢትዮጵያ በፌደራል ወታደሮች እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ዓመት ሊሞላው ሳምንታት የቀረው ጦርነት በአጠቃላይ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች የምግብ ዕርዳታ እና አስቸኳይ ድጋፍም ጥገኛ አድርጓቸዋል።

በተለይም በትግራይ ክልል ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በረሃብ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሲሆን 400 ሺህ ሰዎች በረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው። በአገሪቱ እየተከሰተ ያለው ቀውስ ከፍተኛ ቢሆንም የሚገባው እርዳታ በቂ እንዳልሆነና ለዚህም የመንገዶች መዘጋትና የእንቅስቃሴ ገደቦች ያሉ መሰናክሎችን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተደጋጋሚ ይጠቅሳል።

ምንጭ – ቢቢሲ