ከኦሮሚኛ ድምፃዊው ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ ተፈጠሮ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ በደረሰው የሰዎች ሞትና ንብረት ውድመት ጋር በተያያዘ ክስ በተመሰረተባቸው  የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩምና አስካለ ደምሌ ላይ፣ የዓቃቤ ሕግን ምስክሮች ለመስማት ተሰጥቶ በነበረው ቀጠሮ ወሠረት ዛሬ ጥቅምት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም ምስክርነቱ ሳይሰማ ቀረ፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የቀረቡት፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በግልጽ ችሎት እንታዩ ሰጥቶት በነበረው ትዕዛዝ መሠረት የከሳሽ ዓቃቤ ሕግን ምስክሮች ለመስማት በነበረው ቀጠሮ መሠረት ዓቃቤ ሕግ ሁለት ምስክሮች ይዞ መቅረቡን የገለጸ ቢሆንም በተካሾች በኩል የተቃውሞ አቤቱታ ቀርቧል፡፡

የተካሳሾች  ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ፣ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በፈረደው መሰረት፣ ምስክሮች በግልፅ ችሎት የሚቀርቡ ከሆነ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት፣ የምስክሮችን ስም ዝርዝር አስቀድሞ ለተከሳሾችና ለጠበቆች መሰጠት ያለበት ቢሆንም እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ የምስክሮቹ ስም ዝርዝር ቀድሞ መድረሱ የምስክሮችን ማንነት ለማወቅና መስቀለኛ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ እንደሚያስችላቸው በመጠቆም  እነዲሰጣቸው ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ፣ ሰሎሞን ገዛኸኝ እና ቤተ ማርያም አለማየሁ ጠይቀዋል።
ተከሳሾች ላቀረቡት አቤቱታ ምላሽ የሰጠው ዓቃቤ ሕግ፣የምስክሮቹን  ስም ዝረዝር እንዲሰጥ በፍርድ ቤት አለመታዘዙን ያስረዳ ቢሆንም፣ ጠበቆቹ ግን ጉዳዩ ቀደም ሲል በተከራከሩበት የምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ መሰረት ሳይሆን፣ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕጉ የሚታይ መሆኑን ጠቁመው፣ ለብቻው ልዩ ትዕዛዝ እንደማያስፈልገውና ስም ዝርዝራቸው አስቀድሞ መሰጠት እንዳለበት በሕጉ በግልፅ በመቀመጡ ሊሰጣቸው ይገባ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ሁለት ምስክሮች መቅረቡን በሚመለከት የተከሳሾች ጠበቆች በሰጡት አስተያየትም፣ በአንድ ችሎት ቢያንስ አራት ምስክሮች መቅረብ እንዳለባቸው ጠቁመው፣ዓቃቤ ሕግ ሁለት ብቻ ለማቅረብ መጠየቁ አግባብ እንዳልሆነና ይኸ የሚያሳየው የፍትሕ ጊዜውን ለመግፋት ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ፣ ዓቃቤ ሕግ የምስክሮችን ስም ዝርዝር አስቀድሞ እንዲያቀርብ ተዕዛዝ ሰጥቶ፤ ክርክሩ ካለፉት ችሎቶች የቀጠለ መሆኑን በመግለጽ፣ ዳኞች መዝገቡን ተመልክተው በተነሱ ክርክሮች ላይ ብይን ለመስጠት፣ ሌሎች በተከሳሾች ከመብት ጋር በተያያዘ ያነሷቸውን  አቤቱታዎች በቀጣይ ችሎት እንደሚያዩ በመናገር ምስክሮቹን ለመስማት ለመስጠት በአዳር ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *