መግቢያ

የሃሰተኛ መረጃ  እና  ሃሰተኛ  ዜናዎች  ስርጭት በየጊዜው  እየጨመረ በመምጣቱ  የበርካታ አካላትን ትኩረት  ከሳበ   ዓመታት   ተቆጥረዋል።  አንዳንድ    አካላት   ሃሰተኛ    መረጃዎች    ከሚያስከትሉት መዘዝ   አንጻር   ሃሰተኛ    መረጃዎችን  የመረጃ   ወረርሽኝ   እያሉ   መጥራትን  ይመርጣሉ፤  ሰላም እንዲደፈርስ  ከማድረግ  አንጻር፣   በብሄሮችና  በተለያዩ   እምነት   ተካታዮች      መካከል  ግጭቶች እንዲፈጠሩ   በማድረግ  በአጠቃላይ  በህዝቦች   ሰላማዊ  ኑሮ   ላይ  ችግሮችን   እየፈጠሩ   ስለሚገኙ። ሃሰተኛ  መረጃዎች  ከሚያስከትሉት ጉዳት  አንጻር    የቅድመ-መከላከያ ስራዎችን  መስራት አስፈላጊ በመሆኑ የመገናኛ   ብዙሃን፣  የቴክኖሎጂ ተቋማት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ  ተቋማት አዋጭ  ነው  የሚሉትን እርምጃ  እየወሰዱ   ይገኛሉ።  በኢትዮጵያም  የጥላቻ  ንግግርን እና  የሃሰተኛ መረጃ  ስርጭትን  ለመከላከልና  ለመቆጣጠር አዋጅ  መውጣቱ ይታወሳል።  አዋጁ   በአንድ   በኩል የአገር  ሰላምና የሕዝቦችን  ደህንነት ከማስጠበቅ አንጻር  የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሚወሰዱት እርምጃዎች   መካከል አንዱ  ሲሆን፤ በአንጻሩ   ደግሞ   በትክክል  ካልተተገበረ የመናገር  ነጻነት   ላይ ጥላ ሊያጠላ ይችላል።  የተቀናጀ የመከላከል ስራ መስራት የጥላቻ ንግግር እና ሃሰተኛ  መረጃ የሚያስከትሉትን አሉታዊ ጫና  ለመቀነስ  ይረዳል።

ሃሰተኛ  መረጃዎች  የሚያደርሱትን መጠነ-ሰፊ ጉዳት ከመቀነስና ከመከላከል አንጻር  የብዙሃን መገናኛዎች  ሚና   ከፍተኛ   ነው።   የብዙሃን  መገናኛዎች  ሃሰተኛ    መረጃዎች   የሚያስከትሉትን የጥፋት  ውጤት   ለመቀነስ   እና  በሂደትም  ህዝቡ   በመረጃ  አጠቃቀምና   አረዳድ  ላይ  የሚኖረውን ንቃተ-ህሊና ከመጨመር  አኳያ   የሚኖራቸው  ሚና  የጎላ  ነው።  በዓለም  ዓቀፍ   የሚገኙ   ታላላቅ የብዙሃን  መገናኛዎች  የራሳቸው   የመረጃ   ማጣሪያ   ዴስክ   በማቋቋም  እየሰሩ   መሆናቸው  ጉዳዩ ምንያክል  አሳሳቢና  የተቀናጅ  ጥረት  እንደሚጠይቅ ያመላክታል። መረጃን  የማጣራት ስራ  ተቋማዊ በሆነ  መልኩ በአገራችን  በሚገኙ  የመገናኛ  ብዙሃን ቢሰራ  የሚኖረውን ዘርፈ-ብዙ  ፋይዳ  በመረዳት የመርሳ  ሚዲያ   ተቋም   ለተመረጡ  አራት   የብዙሃን  መገናኛዎች  ሃቅ   ማጣራትን  በተመለከተ መሰረታዊ  እውቀትና    ክህሎት  የሚያስጨብጡ  ስልጠናዎችን   ከዶቼ   ቬለ   አካዳሚ   እና   ከኮድ ፎር  አፍሪካ     ጋር   በመተባበር ሲሰጥ   መቆየቱ   ይታወሳል። ይህ  በሃቅ   ማጣራትና አሰራር   ዙሪያ የተዘጋጀ ማጣቀሻም  የዚሁ ጥረት  አንድ  አካል   ነው።

ምዕራፍ ንድ ፥ ሰተኛ መረጃዎች

የሃሰተኛ መረጃዎች  ትርጉም፣   የሃሰተኛ መረጃዎች  አይነት፣   የሃሰተኛ መረጃዎች  መዘዝና  ተዋናዮች እንዲሁም   የሃሰተኛ መረጃዎች  ዝግጅትና ስርጭት ሂደት  በዚህ  ምዕራፍ   የሚዳሰሱ  ነጥቦች  ናቸው። ሃሰተኛ   መረጃዎች   በተለያየ  ጊዜ  በተለያየ  ቅርጽ  እና  ሁኔታ  ሲሰራጩ የቆዩ  ቢሆንም  በአሁኑ ጊዜ  ግን በከፍተኛ   ፍጥነት  የሚዛመቱ  እና   መጠነ-ሰፊ  የሆነ   ጉዳት   የሚያደርሱ  በመሆኑ  ከፍተኛ   ትኩረትን ስበዋል። የማህበራዊና የኦን  ላይን  ሚዲያው  መስፋፋቱን ተከትሎ   የሃሰተኛ መረጃ  የመሰራጨት  አቅም በእጅጉ  የጨመረና  የፈጠነ   ሆኗል።  ሃሰተኛ   መረጃ  ከእውነተኛ   መረጃ  በይበልጥ  የሰውን   ጀሮ  የሚስብ በመሆኑና በቀላሉ  የሚረሳ   ወይም  የሚጠፉ   ባለመሆኑ መዘዙ   ከፍ  ያለ  ነው።  ሃሰተኛ   መረጃ  ለተለያየ ዓለማ  በተለያዩ  አካላት  የሚዘጋጅ ቢሆንም  ከሞላ  ጎደል  ሁሉም  አይነት ሃሰተኛ   መረጃ  በተለያዩ  አካላት ላይ  ጉዳት  ያደርሳል፡ የህብረተሰቡ  ሰላምና ደህንነት እንዲታወክ እንዲሁም  የተቋማት  መደበኛ  እንቅስቃሴ እንዲስተጓጎል  ከማድረግ አንጻር  ያላቸው  አሉታዊ አስተዋጾ  የጎላ  ነው።

የትኛውም   ትክክለኛ   ያልሆነ  እና   ከሁለትና  በላይ   በሆኑ  ሰዎች   መካከል  የሚጋራና  በተለያየ   መንገድ ጉዳት  የሚያደርስ  መረጃ  በሃሰተኛ  መረጃ  ማዕቀፍ   ውስጥ   ሊካተት   ይችላል።   አንዳንድ   ሰዎች   በተለይ ባለስልጣናት  ከሃሰተኛ  መረጃዎች   ይልቅ  ሃሰተኛ   ዜናዎች   ማለትን   ይመርጣሉ።  ይህ   አካሄድ  በብዙ የሚዲያ  ባለሙያዎች ዘንድ  ችግር  ያለበት  አተያይ  እንደሆነ ይገለጻል። በእርግጥ ሁሉም  ሰው በፈለገውና በመረጠው ርዕሰ-ጉዳይ ላይ  የተለያየ  አንድምታ  ያለው ይዘት  አዘጋጅቶ  ማጋራት የሚችል  መሆኑ በአንድ በኩል  ጠቃሚ   ቢሆንም   መረጃን   ከዜና   ለይቶ   ከመረዳት   ይልቅ  ሁለቱንም   በአንድ   ቋት  የመጨፍለቅ አዝማሚያ  መደበኛ  የዜና  ተቋማትን  ለመምታትና ስራዎቻቸውን ለማጣጣል ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። ይህ   አይነቱ  ያልተገባ  አገላለጽ  በመደበኛ   የሚዲያ   ተቋማቱ   እና   ስራዎቻቸው   ላይ  ጥላሸት   የሚቀባና በሂደትም  ህዝቡ   በሚዲያዎች  ላይ   የሚኖረውን  አመኔታ   ክፉኛ   የሚሸረሽር፣  በሚዲያውና    በህዝቡ መካከል   የሚኖረውን ግንኙነት  የሚያላላ፣ በጊዜ  ሂደትም   የሚዲያ  ተቋማቱ  የውሸት  ፋብሪካ  ተደርገው እንዲሳሉ  የሚያደረግ አደገኛ አገላለጽ ነው። ሃሰተኛ  ዜናዎችን የሚያስተላልፉ ሚዲያዎች  የሉም ማለት አይደለም፡   ጥቅል የሆነው አገላለጽ  ጥሩ  ስራ  የሚሰሩትን   ሚዲያዎች   ጨምሮ  ጉድጓድ ውስጥ  የሚከት ስለሆነ  እንጂ።  ምንም እንኳ  ሃሰተኛ  መረጃዎችን በአገራችን  ቋንቋዎች  ነጣጥሎ መጥራት የሚያስችግር ቢሆንም  ቢያንስ  በጽንስ-ሃሳብ ደረጃ ግን  መረዳት  ያስፈልጋል። በመሆኑም ሃሰተኛ  መረጃዎችን በዋናነት በሶስት  ከፍሎ   ማየት  ይቻላል።  ሀሰተኛ  መረጃዎችን ከፋፍሎ  ለማየት  የሚረዳን  ዋናው  ነጥብ  የሃሰተኛ መረጃዎች  መሰረታዊ አለማ  ምንድን  ነው  የሚለው  ጉዳይ  ነው።  በዚህ  መሰረትም፡-

1፣ ሆነ  ተብሎ  ጉዳት  ለማድረስ  የሚዘጋጅና የሚሰራጭ መረጃ  (Disinformation)፡- ይህ  አይነቱ ሀሰተኛ መረጃ  ሆነ  ተብሎ  የተወሰነ   አላማ  አንገቦ  የሚዘጋጅ ሲሆን   የመረጃው  ጠንሳሽ/አመንጭ/ እንዲሁም መረጃውን   የሚያዘጋጀው  እና  የሚያስራጨው  አካል   መረጃው  ሃሰተኛ   መሆኑን በደንብ  ያውቃሉ። ሰለዚህ  ሆን  ተብሎ  አንድን   ግለሰብ፣  ማህበረሰብ፣ ተቋም  ወይም  አገር  ለመጉዳት   የሚዘጋጅ የሃሰት መረጃ ነው  ።

2፣ ሃሰተኛ   መሆኑ  ሳይታወቅ የሚሰራጭ መረጃ  (Misinformation)፡  መረጃውን  የሚያሰራጩ  አካላት መረጃው   ሃሰተኛ   መሆኑን  ባለማወቅ   በሚያሰራጩበት  ጊዜ  የሚፈጠር  የሃሰተኛ  መረጃ   ፍሰትን የሚገልጽ ነው። ይህ  ሁኔታ በአብዛኛው በብዙ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ  እንደሚስተዋል መጥቀስ   ይቻላል፡ ምክንያቱም  ሰዎች  ያገኙት   መረጃ  እውነተኛ  ይመስላቸውና ለሌሎች  የማህበራዊ ሚዲያ  ተጠቃሚዎች  ያጋራሉ።  ከዚህ   ላይ  መነሳት  ያለበት   ነጥብ  መረጃዎን  የሚያጋሩት  ጉዳት ለማድረስ  አስበው  ሳይሆን ለሌሎች  ሰውች  መረጃው  የሚኖረውን ጠቀሜታ  በማሰብ  ነው።

3፣ በእውነተኛ  መረጃ  ላይ  የተመሰረተ ጎጂ  መረጃ  ማሰራጨት  (Malinformation)፡  አውነተኛ  መረጃን ተመርኩዞ  መጠነ-ሰፊ ጉዳት   ለማድረስ   የሚሰራጭ  መረጃን   ይመለከታል።   ይህን   ሃሳብ   በምሳሌ በማስደገፍ    እንደሚከተለው  ማብራራት    አስፈላጊ   ይመስላል።  አንድ   ባለሃብት  ከአንድ    በሙስና ከሚታማ   ባለስልጣን  ጋር   ፎቶ  ተነስቶ  ቢታይ   ወይም  ከዚሁ  ባለስልጣን  ጋር   በአንድ   ሆቴል ምሳ ሲበላ  በድብቅ  የተነሳ   ፎቶ  በማህበራዊ   ሚዲያ  ሊንሸራሸር  ይችላል።   ይህንንም   ተከትሎ   ባለሃብቱ  ያፈራቸውን   ንብረቶች  እና     የከፈታቸውን  የቢዝነስ   ተቋማት   በሙስና  የተገኙ   ሃብቶች   አድርጎ  በመወስድ  የማህበራዊ ዘመቻ  ሰለባ  የማድረግ ሂደት  ነው።  የዚህ  አይነቱ መረጃ  መነሻው  ትክክለኛ ቢሆንም  መረጃው  የሰውችን  ስብዕና፣ የግልና  የቤተሰብ ነጻነት፣  ንብረት  እና  የመሳሰሉትን ለጉዳት ያጋልጣል።      የግል  ጉዳዮች   ወይም   መረጃዎች   ለህዝብ   ጥቅምና   ለመሳሰሉት  በህግ   ለሚደገፍ  አላማዎች   ካልሆነ  በስተቀር   አግባብነት  በሌለው   መልኩ  ወደ  ህዝብ  አደባባይ   ማውጣት   ሰዎችን ለተለያዩ  ጉዳቶች  ሊያጋልጡ  ይችላሉ።

ምንጭ – በመርሳ ሚዲያ ተቋም  እና ዶይቸ ቬለ አካዳሚ  ትብብር የተዘጋጀ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *