ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ ኪራሙ ወረዳ ውስጥ ታጣቂዎች በነዋሪዎች ላይ ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት መፈጸማቸው በእጅጉ እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።

ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ነሐሴ 12/2013 ዓ.ም “ኦነግ ሸኔ” ናቸው በተባሉ ታጣቂዎች በተፈጸመው ጥቃት ከ150 በላይ ነዋሪዎች መገደላቸውን ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከሌሎች ሰዎችም መረዳቱን ገልጿል። በጊዳ ኪራሙ አካባቢ ተሰማርተው የቆዩ የፀጥታ ኃይሎች ማክሰኞ ወደ ሌላ አካባቢ መሄዳቸውን ተከትሎ በነጋታው ረቡዕ ነሐሴ 12/2013 ዓ.ም ታጣቂዎች “ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት ማድረሳቸው በከፍተኛ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን” ኮሚሽኑ ገልጿል። ይህንንም ተከትሎ የወረዳው ነዋሪዎች በተለይም ሴቶችና ሕጻናት ወደ አጎራባች አካባቢዎች መሸሻቸውን የሰብአዊ መብት ተቋሙ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

“በቀጣይ ቀናትም ከነዋሪዎች የተውጣጡ ሰዎች ብሔርን መሠረት ያደረገ የአጸፋ ጥቃት በማድረሳቸው 60 ሰዎች መገደላቸውን፣ ነዋሪዎችም ወደ አማራ ክልልና ወደ ኪራሙ ከተማ መፈናቀላቸውን” ኮሚሽኑ ገልጿል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ለጥቃቱ መፈፀም ክፍተት የፈጠረው የፀጥታ ኃይሎች ከአካባቢው የወጡበትን ምክንያት እንዲያጣሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ጥቃት ተፈጽሞ በርካታ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ የፀጥታ ኃይሎች ወደ አካባቢው እንደተመለሱና ጊዳ ኪራሙ ወረዳ ወደ መረጋጋት መመለሱን ነገር ግን በወረዳውና በአጎራባች ወረዳዎች አሁንም የፀጥታ ስጋት እንዳለ ነዋሪዎች እንደተናገሩ ኢሰመኮ አመልክቷል። የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ጋር እንዲቀናጁና የአካባቢውን ነዋሪዎች ደኅንነት እንዲያረጋግጡ የጠየቁት ኮሚሽነሩ፤ “በተለይም በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ስምሪት እና እንቅስቃሴን የተመለከተ አሠራር ተገቢው ምርመራ ሊደረግበት ይገባል” ብለዋል።

ኢሰመኮ ጨምሮም ስለ ክስተቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ክትትሉን እንደሚቀጥልና “የአካባቢው ፀጥታ የደረሰበት አስጊ ደረጃ ወደ አጎራባች አካባቢዎች እንዳይዛመትና የበለጠ ሰብአዊ ቀውስ እንዳያደርስ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው” በማለት አሳስቧል። ለታጣቂዎቹ ጥቃት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን ፀጥታ በዘላቂነት ለመጠበቅ የፀጥታ ኃይል እንዲጠናከር የፌዴራል መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የፈጸሙ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የፌዴራልና የክልሉ ኃላፊዎች በቅንጅት እንዲሠሩ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጥሪ አቀርቧል።

በምሥራቅ ወለጋ ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች ተመሳሳይ ጥቃቶች በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በታጣቂዎች በተደጋጋሚ ሲፈጸም የቆየ ሲሆን፤ በመንግሥት ኦነግ ሸኔ የሚባለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጥቃቱን በማድረስ ይከሰሳል። በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረው ይህ ታጣቂ ቡድን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ የተሰየመ ሲሆን በቅርቡ ከህወሓት ጋር ጥምረት መፍጠሩን ማሳወቁ ይታወል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *