በኦሮሚያ ክልል፣ በምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ በኪረሙ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ሀሮ ከተማ ባለፈው እሁድ መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም የተጸፈመ ጥቃትን ተከትሎ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን እና ንብረት መውደሙን የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ገለጹ።

በምሥራቅ ወለጋ ሀሮ በተባለ አካባቢ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ንጹሀን ሰዎች እንደተገደሉ፣ ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ እንዲሁም የንብረት ውድመትም እንደደረሰ ተነግሯል። እሁድ፣ መስከረም 30/2014 ዓ.ም ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ የ15 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን መረጃ እንዳላቸው የኦሮሚያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ለቢቢሲ ተናግረዋል።በርካታ የቤተሰቦቻቸው አባላት እንደተገደሉባቸው እና ሌሎችም የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በዚህ ግጭት ሳቢያ ሕይወታቸውን እንዳጡ የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአማራ እና በኦሮሞ ወገን ያሉ ማኅበረሰቦች ለተፈጸመው ጥቃት እርስ በእርስ በመወነጃጀል ለደረሰው ጥቃት አንዳቸው የሌላኛቸውን ወገን ተጠያቂ ያደርጋሉ።በአንድ በኩል ግጭቱ የተነሳው በነዋሪዎች መካከል እንደሆነ ሲነገር፣ በሌላ በኩል ደግሞ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚለው እና መንግሥት ሸኔ የሚለው ቡድን እንዲሁም የአማራ ኃይሎች ከግጭቱ ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የሚሉ ውንጀላዎች ይሰማሉ። ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር እንዲሁም በዚህ መስከረም ላይ በአካባቢው ጥቃቶች ተፈጽመው የብዙዎች ሕይወት መቀጠፉ አይዘነጋም።

የኦሮሚያ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ኃይሉ አዱኛን ባለፈው እሑድ በምሥራቅ ወለጋ በኪረሙ ወረዳ ውስጥ የተከሰተው ምን እንደሆነ ለቢቢሲ ማብራሪያ ሰጥተዋል። “እዚያ አካባቢ ችግር የፈጠሩት ሸኔ እና አክራሪ ኃይሎቸ ናቸው። ከህወሓት የወሰደውን ተልዕኮ ለማስፈጸም በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው አክራሪው ኦነግ ሸኔ ነው ድርጊቱን የፈጸመው” ሲሉ ቡድኑን ከስሰዋል። ጨምረውም ቡድኑ ተልዕኮውን ከግብ ለማድረስ እና የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሁለቱን ሕዝቦች በማጋጨት እየተንቀሳቀሰ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

“እዚያ አካባቢ የሚንቀሳቀስ አክራሪ ኃይል አለ። ይህ ኃይል ከኦነግ ሸኔ ጋር ተቀናጅቶ የሚሠራ ነው። የሚሠራውም የአማራ እና የኦሮሞን ሕዝብ አጀንዳ አስታኮ ነው። ሁለቱን ወገኖች ለማጋጨት እና ነገሩን የሕዝብ አጀንዳ ለማስመሰል እየሞከሩ ነው።” የኦሮሞ ነጻነት ኃይል ወይንም ሸኔ ከህወሓት ጋር ለመስራት ከስምምነት ላይ መድረሱን መግለፁ ይታወሳል። የክልሉ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ “የፀጥታ አካል ወደ አካባቢው ተሰማርቶ በአሁኑ ጊዜ ሁኔታው ተረጋግቷል። የፀጥታ ኃይል ገብቶ አሁን ሰላም እየወረደ ነው” ብለዋል።

ጥቃቱን የፈጸሙት ከሌላ አካባቢ የመጡ የታጠቁ ኃይሎች ናቸው መባሉን አቶ ኃይሉ አስተባብለዋል። በሰጡት ምላሽም በተነሳው ግጭት ምክንያት ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ገልጸው ከሌላ አካባቢ መጥቶ የሚንቀሳቀስ የታጠቀ ኃይል አለመኖሩን ገልፀዋል። ግጭቱን የቀሰቀሱት ኃይሎች “አጀንዳቸው አማራ እና ኦሮሞን ማጋጨት ስለሆነ እነዚህ እየተናበቡ እየተንቀሳቀሱ ነው። የህወሓትን አጀንዳ ለማስፈጸም ካልሆነ በስተቀር ከሌላ አካባቢ መጥቶ እዚያ ቦታ የሚንቀሳቀስ ኃይል የለም።”

ረቡዕ ምሽት ጉዳዩን በሚመለከት መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ከመስከረም 30/2014 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት የሸኔ ታጣቂዎች በሀሮ ቀበሌ በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን፣ የአካል ጉዳት እንደደረሰና ንብረት እንደወደመ መረጃዎች እንደደረሱት አመልክቷል። ጨምሮም ታጣቂዎቹ በአካባቢው በመኖራቸው “የሟቾችን አስክሬን ለማንሳትና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ወደ ህክምና ለመውሰድ አለመቻሉን፣ ሴቶች እና ሕፃናት አሁንም በጫካ ውስጥ” በችግር ውስጥ እንዳሉና ነዋሪው በከፍተኛ የደኅንነት ስጋር ውስጥ መሆኑን ጉባኤው ገልጿል።

ይህንን ክስተት ተከትሎ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ በምሥራቅ ወለጋ እና አካባቢው በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በአስቸኳይ ይቁም ሲል አሳስቧል። ፓርቲው ረቡዕ ዕለት ይህንኑ ጥቃት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ “ንፁሃንን ለመታደግ በቦታው ያሉ የፌደራል የፀጥታ አካላት ቁጥራቸው ጥቂት በመሆኑ ሕዝቡን መታደግ ካለመቻላቸው ባለፈ እነሱም የጥቃቱ ሰለባ እየሆኑ እንደሆነ” ከቦታው ደረሰኝ ባለው መረጃ ማረጋገጡን ጠቅሷል።

ኢዜማ አክሎም በተደጋጋሚ የሚደርሱትን ጥቃቶች ለማስቆም እና አጥፊዎችን ሕግ ፊት አቅርቦ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ለምን እንዳልተቻለ የክልሉ መንግሥት እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ማብራሪያ እንዲሰጡበት ጠይቋል። ከዚህ ቀደም በዞኑ ውስጥ ተመሳሳይ ጥቃቶች ተፈጽመው በርካታ ሰዎች መገደላቸውንና መፈናቀላቸውን እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገልጾ ነበር።

ኮሚሽኑ ባወጣው ሪፖርት በአካባቢ ተሰማርተው የቆዩ የፀጥታ ኃይሎች ወጥተው መሄዳቸውን ተከትሎ ላይ ነሐሴ 12/2013 ዓ.ም ኦነግ ሸኔ ናቸው በተባሉ ታጣቂዎች “ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት በማድረሳቸው” ከ150 በላይ ነዋሪዎች መገደላቸውንና በርካቶች ከቀያቸው መፈናቀላቸው በከፍተኛ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን መሆኑን ገልጾ ነበር። ተከትሎም ባለፈው ወር ምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ በኪራሙ ወረዳ ቦቃ ቀበሌ መስከረም 7 እና 8 ቀን 2014 ዓ.ም በተፈጸሙ ጥቃቶች 29 ሰዎች መገደላቸውንና ከ40 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው ሪፖርት አውጥቶ ነበር።

ኮሚሽኑ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ ባወጣቸው መግለጫዎች በአካባቢው የተከሰቱት ሁኔታዎች በእጅጉ እንዳሳሰቡትና የክልሉና የፌደራል መንግሥቱ የፀጥታ ኃይሎች የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቆ ነበር። በምዕራብ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው በሽብርተኝነት የተሰየመው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚለው መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ከሚፈጸሙ ጥቃቶች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *