የአውሮፓ ፓርላማ አባላት በሠሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በቀጣይ ሦስት ሳምንታት ውስጥ መሻሻል የማያሳይ ከሆነ በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ አካላት ላይ ማዕቀቦች እንዲጣል ጠየቁ።

የአውሮፓ ፓርላማ ሐሙስ መስከረም 27/2014 ዓ.ም ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ላይ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲገኝ ጠይቋል። በዚህም መሠረት የፓርላማው አባላት በጦርነቱ አካባቢ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ እስከ ፈረንጆቹ ጥቅምት ወር መጨረሻ ማለትም ጥቅምት 21/2014 ዓ.ም ድረስ በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል የማያሳይ ከሆነ ኮሚሽኑ በጦርነቱ ተሳታፊዎች ላይ ማዕቀብ እንዲጥል ጠይቀዋል። በዚህም መሠረት ፓርላማው ዕቀባው ያመለከታቸው ወገኖችን የጠቀሰ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥት፣ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እንዲሁም ግጭቱ እንዲራዘም እና እንዲባባስ አስተዋጽኦ አላቸው ያላቸውን አካላት ጠቅሷል።

የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ትናንት ሐሙስ በሠሜን ኢትዮጵያ ግጭት እና የሰብዓዊ እርዳታ እቅርቦት እክሎች በአስቸኳይ እንዲወገዱ ባወጡት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ጠይቀዋል። በትግራይ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት መልሶ እንዲሰፍንና የተኩስ አቁም ተደርጎ አስፈላጊው ቁጥጥር ዘዴ እንዲቋቋም ጠይቀው፤ በሌሎችም የኢትዮጵያ አካባቢ ያለው የሰብአዊ ችግር ሁኔታ እያሽቆለቆለ መሆኑን አሳስቧል። ፓርላማው ባደረገው ስብሰባ ላይ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ 618 ድጋፍ፣ 4 ተቃውሞ እና 58 ድምጸ ታቅቦ ተቀባይነት አግኝተወል ሲል ከፓርላማው የወጣው መግለጫ አመልክተወል።

ፓርላማው እንደ ምግብ፣ መድኃኒት እና ነዳጅ ያሉ መሠረታዊ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች ላይ ይፋዊ ያልሆነ እገዳ እንዲቆም ለየሚመለከታቸው ብሔራዊ እና አህጉራዊ አካላት ጥሪውን አቅርቧል። እንዲሁም በአጎራባቾቹ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ድጋፍ እንዲደረግ አሳስቧል። ፓርላማው በውሳኔ ሃሳቡ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ ሆነ ብለው ንሑሃን ዜጎችን ዒላማ ማድረጋቸውን አጥብቆ አውግዟል። የትግራይ ኃይሎችን ጨምሮ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ልጆችን ለጦርነት መመልመላቸው እና የቀጠለው አስገድዶ መድፈር እና ጾታዊ ጥቃቶችን አጥብቆ ተቃውሟል። ፓርላማው አጎራባች አገራት ግጭቱን ሊያባብሱ ከሚችሉ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እራሳቸውን እንዲቆጥቡ ጠይቋል።

የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ጨምረውም የኢትዮጵያ መንግሥት በግዛቱ ውስጥ የሚገኙ የስደተኞችን እና የተፈናቃዮችን ደኅንነት የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት በሺዎች የሚቆጠሩ በትግራይ ክልል ከሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች የተፈናቀሉ ኤርትራውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጥበቃ እና ድጋፍ እንዲያደርግ የሕብረቱ ፓርላማ አባላት ጠይቀዋል። በተጨማሪም የደረሱበት ያልታወቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ መንግሥት እንዲያሳውቅ የፓርላማ አባላቱ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ሰባት የተባበሩት መንግሥታት የሥራ ኃላፊዎቹን ከአገር ማስወጣቱንም ፓርላማው ኮንኖታል። ከተጀመረ ከአንድ ወር በኋላ ዓመት የሚሞላው ትግራይ ውስጥ ተጀምሮ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሰብአዊ እርዳታ እንዲጠብቁ ሲያስገድድ መቶሺዎች የሚሆኑት ደግሞ በረሃብ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኑ የተባባሩት መንግሥታት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

ባለፉት ሳምንታት በመንግሥት ኃይሎችና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጦርነት እየተካሄደ ስለመሆኑ የሚያመለክቱ ምንም አይነት መረጃ ባይኖርም ግጭቱ ስለመቆሙም ከየትኛውም ወገን አልተነገረም። ወደ ትግራይ ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ መቸገሩንና በትግራይ ውስጥ ያለው ሰብአዊ ሁኔታ ኣሳሳቢ መሆኑን በመግለጽ የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚከሰው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞቹ ከአገር መባረራቸው ውዝግብ አስከትሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱ የተስተጓጎለው ህወሓት ከባድ ተሽከርካሪዎችን ከትግራይ እንዳይወጡ በማድረጉ መሆኑን አመልክቶ፣ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የተደረጉት የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባትና ለአማጺያን ድጋፍ በመስጠታቸው ነው ማለቱ ይታወቃል።

ምንጭ – ቢቢሲ