የኢትዮጵያ ፌደራል ሠራዊት በትግራይ ኃይሎች ላይ በሁሉም ግንባሮች የተቀናጀ ጥቃት መክፈቱን እና ዓለም አቀፉ ማኅረሰብ ይህንን እርምጃ እንዲያውግዝ አማጺያኑ ጠየቁ።

ህወሓት በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች እየተሰነዘረበት ያለው ጥቃት “በከባድ ጦር መሳሪያ፣ በታንክ፣ በሮኬቶች፣ በድሮኖች እና በተዋጊ ጀቶች” የታገዘ እንደሆነ በመግለጫው አመልክቷል። የትግራይ የውጭ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ከተባለው አካል በወጣ መግለጫ ላይ ህወሓት፤ ከጥቅምት 01/2014 ዓ.ም ጠዋት ጀምሮ የኢትዮጵያ መከላከያ በአማራ ኃይሎች ድጋፍ በሁሉም ግንባሮች የተቀናጀ ማጥቃት ከፍተዋል ይላል።

የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ እንዳሉት ባለፈው ሳምንት የተከፈተው ጥቃት አሁን “በሙሉ ኃይል” እየተካሄደ ነው። ባለፉት ሁለት ቀናት የፌደራሉ መንግሥት በህወሓት ኃይሎች ላይ “ከባድ” የተባለ ጥቃት በአማራ እና አፋር ክልሎች በሚገኙ ግንባሮች እየፈጸመ እንደሆነ ሲዘገብ ቆይቷል። ወታደራዊ ጥቃት መከፈቱን በተመለከተ የተጠየቁት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም በሰጡት ምላሽ፣ መንግሥት በመላው አገሪቱ ዜጎችን ከሽብር ድርጊቶች የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት ከማለት ውጪ ተጨማሪ ዝርዝር ከመስጠት መቆጠባቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ሮይተርስ የዜና ወኪል የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑትን አቶ ጌታቸው ረዳንና አንድ ዲፕሎማቲክ ምንጭን ጠቅሶ እንደዘገበው አማጺያኑ በያዟቸው ቦታዎች ላይ የአየርና ከባድ መሳሪያ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። የፈረንሳይ ዜና ወኪል በተመሳሳይ የመንግሥት ኃይሎች በትግራይ አማጺያን ላይ በአማራ ክልል ውስጥ በምድርና በአየር ጥቃት እያካሄዱ መሆናቸውን በእርዳታ ሥራ ላይ የተሰማሩና የአማጺያኑ ምንጮች ጠቅሶ ዘግቦ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት እየተካሄደ ነው ስለተባለው ውጊያ የሰጠውም ምንም አይነት ማረጋገጫ የሌለ ሲሆን በአካባቢዎቹ ያለው የግንኙነት መስመር በመቋረጡ ከገለልተኛ አካል መረጃዎችን ማረጋገጥ አስቸጋሪ ሆኗል።

ይህን መጠነ ሰፊ የመልሶ ማጥቃትን በተመለከተ በመንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም። ይሁን እንጂ የኤታማዦር ሹሙ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ፤ ጦርነቱን በተመለከተ ምንም አይነት መረጃ እንደማይሰጡ በኢሳት ቴሌቪዝን ላይ ተናግረዋል። ህወሓት በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ አዲስ እየተካሄደነው የተባለው ውጊያ በአማራ ክልል ውስጥ ባሉት ገርገራ፣ ወገል ጤና፣ ወርጌሳ እንዲሁም በአፋር ክልል ደግሞ በአንድ ግንባር መሆኑን ገልጿል።

ባለፈው ጥቅምት ወር የተቀሰቀሰው ጦርነት ለስምንት ወራት ከተካሄደ በኋላ የፌደራሉ ጦር ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ እራሱን መልሶ ሲያደራጅ እና ሲያስታጥቅ ቆይቷል ብሏል የህወሓት መግለጫ። መግለጫው መንግሥት አዲስ ምልምል ወታደሮችን ማሰልጠኑንና ማስታጠቁን እንዲሁም ከተለያዩ አገራትም ዘመናዊ መሳሪያዎችን መግዛቱን በመጥቀስ አዲሱ ጥቃት ይህንን ተከትሎ የተከፈተ መሆኑን ገልጿል።

ጦርነት አማራጭ አይደለም

ህወሓት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ “የትግራይ ሕዝብ ወደማይፈልገው ጦርነት ተገዶ ገብቷል” ያለ ሲሆን፤ “ሕልውናውን ለማረጋገጥ ጦርነቱን ማሸነፍ ግዴታ ነው” በማለት ተከፈተብን ያለውን ጥቃት “የትግራይ ኃይሎች” እየተከላከሉ ነው ብሏል። የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ፤ “የመጨረሻ ማጥቃቱን ተከትሎ ወታደሮቻችን ቦታቸውን እንደያዙ ነው” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል። መግለጫው “ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ይህን የመጨረሻ ማጥቃት እንዲያወግዝ እና በዚህ ወሳኝ ሰዓት ለትግራይ ሕዝብ ድጋፍ እንዲሰጥ እንጠይቃለን” ብሏል።

ዓለም አቀፉ ማሕብረሰብ ከቃላት ባለፈ በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ እና በአማራ ክልል መንግሥታት ላይ ትርጉም ያለው የቅጣት እርምጃ ይወሰድ ሲልም ጨምሮ ጠይቋል። ጥቃቶች በአማራ ክልል በሚገኙ በርካታ ስፍራዎች ላይ ሐሙስና አርብ ዕለት መካሄዳቸውን ምንጮች ለኤኤፍፒ የተናገሩ ሲሆን፤ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳም ከፍተኛ ጥቃት እንደተከፈተባቸው ገልጸው ነበር። አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ አቶ ጌታቸውን ጠቅሶ እንደዘገበው “አብዛኛው የአየር፣ የድሮን እና የመድፍ ድብደባዎች” በአማጺያኑ ላይ መፈጸማቸውን እንዲሁም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በሰሜን ጎንደርና በሰሜን ወሎ ዞኖች ውስጥ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

“በሁሉም ግንባሮች በኩል ግዙፍ ኃይል እየተንቀሳቀሰ ነው. . . በየትኛው ግንባር ጥቃት ሊከፍቱ እንደሚችሉ እርግጠኛ አይደለንም” ሲሉ የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ለሮይተርስ በስልክ አርብ ዕለት ገልጸው ነበር። ጨምረውም አዲስ ተከፈተ ባሉት የተጠናከረ ጥቃት በኢትዮጵያ ሠራዊት በኩል “መድፎችና ሰው አልባ አውሮፕላኖች [ድሮን] ጥቅም ላይ ውለዋል” ብለዋል። የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ሐሙስ ዕለት በትዊተር ገጻቸው ላይ “በአሸባሪው ህወሓት ምክንያት ችግር ውስጥ የሚገኘውን ሕዝባችንን ነፃ ለማውጣት በሁሉም ግንባሮች የማያዳግም ኦፕሬሽን በየትኛውም ጊዜና ሰዓት ሊደረግ ይችላል” በማለት አስፍረው ነበር።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የተቀሰቀሰው ውጊያ በትግራይ ክልል ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያፈናቀለ ከመሆኑ በተጨማሪ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ለረሃብ እንዳጋለጠ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል። መንግሥት ወደ ክልሉ እርዳታ እንዳይገባ እንቅፋት ፈጥሯል እየተባለ የሚወቀስ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ክሱን አይቀበለውም። የፌደራሉ ሠራዊት በሰኔ ወር ላይ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ ክልል መውጣቱን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልል ገፍተው መግባታቸው ይታወሳል። በዚህም ሳቢያ በሁለቱም ክልሎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቀያቸው ለመፈናቀል የተገደዱ ሲሆን 1.7 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ የምግብ እርዳታን ለመጠበቅ ተገደዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ