በሰሜን ኢትዮጵያ የአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ የትግራይ ኃይሎች ላይ የተጠናከረ የአየርና የምድር ጥቃት እንደተከፈተባቸው የአካባቢው ምንጮችና የቡድኑ ቃል አቀባይ ለዜና ወኪሎች ገለጹ።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑትን ጌታቸው ረዳንና አንድ ዲፕሎማቲክ ምንጭን ጠቅሶ እንደዘገበው አማጺያኑ በያዟቸው ቦታዎች ላይ ባለፉት ሁለት ቀናት የአየርና ከባድ መሳሪያ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። የፈረንሳይ ዜና ወኪል በበኩሉ የመንግሥት ኃይሎች በትግራይ አማጺያን ላይ በአማራ ክልል ውስጥ በምድርና በአየር ጥቃት እያካሄዱ መሆናቸውን በእርዳታ ሥራ ላይ የተሰማሩና የአማጺያኑ ምንጮች እንደነገሩት ዘግቧል።

ለሳምንታት ከሁለቱም ወገን የጎላ እንቅስቃሴ ሳይሰማ የቆየ ሲሆን አሁን ግን የአየር ጥቃት እንደተጀመረ ለሮይተርስ ዜና ወኪል የተናገሩት የህወሓት ቃል አቀባይ፤ ይህም በኢትዮጵያ ሠራዊት የምድር ጥቃት ሊጀመር መሆኑ ምልክት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል። አንድ ዓመት ሊሞላው በተቃረበውና ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ከጥቂት ወራት በፊት ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ የህወሓት ኃይሎች በደቡብ ጎንደርና በሰሜን ወሎ ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸው ይታወቃል።

ጥቃቶች በአማራ ክልል በሚገኙ በርካታ ስፍራዎች ላይ ሐሙስና አርብ ዕለት መካሄዳቸውን ምንጮች ለኤኤፍፒ የተናገሩ ሲሆን፤ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳም ከፍተኛ ጥቃት እንደተከፈተባቸው ገልጸዋል። አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ አቶ ጌታቸውን ጠቅሶ እንደዘገበው “አብዛኛው የአየር፣ የድሮን እና የመድፍ ድብደባዎች” በአማጺያኑ ላይ መፈጸማቸውን እንዲሁም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በሰሜን ጎንደርና በሰሜን ወሎ ዞኖች ውስጥ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

“በሁሉም ግንባሮች በኩል ግዙፍ ኃይል እየተንቀሳቀሰ ነው. . . በየትኛው ግንባር ጥቃት ሊከፍቱ እንደሚችሉ እርግጠኛ አይደለንም” ሲሉ የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ለሮይተርስ በስልክ ተናግረዋል። ጨምረውም አዲስ ተከፈተ ባሉት የተጠናከረ ጥቃት በኢትዮጵያ ሠራዊት በኩል “መድፎችና ሰው አልባ አውሮፕላኖች [ድሮን] ጥቅም ላይ ውለዋል” ብለዋል። “በሁሉም ግንባሮች የተከፈተውን ይህንን ጥቃት እናከሽፈዋለን” ያሉት አቶ ጌታቸው “የተጣለብን ከበባ እስኪነሳ ድረስ ባለንበት እንቆያለን” ማለታቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

የዜና ወኪሉ እየተካሄደ ነው ስለተባለው በገለልተኛ ምንጭ ስላልተረጋገጠው ወታደራዊ ዘመቻ ከፌደራል መንግሥቱና ከአማራ ክልል እንዲሁም ከሠራዊቱ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካ ገልጿል። ሐሙስ ዕለት የጀመረው ተከታታይ የአየር ጥቃት አርብም የቀጠለ ሲሆን፣ ትኩረቱን ያደረገውም በሦስት አካባቢዎች ላይ ነው። እነዚህም ከውርጌሳ አቅራቢያ ባለ ቦታ፣ በወገል ጤና እና በምሥራቅ በኩል ደግሞ የአማራ ክልልን ከአፋር ጋር በሚያገናኘው መንገድ ላይ ነው ብሏል ሮይተርስ።

ውርጌሳ አቅራቢያ የአየር ጥቃት እንደነበር አንድ ዲፕሎማቲክ ምንጭ እንዳረጋገጠለት የጠቀሰው የዜና ወኪሉ፣ በሌሎቹ አካባቢዎች ተፈጸመ ስለተባለው የአየር ጥቃት ከገለልለተኛ ወገን ለማረጋገጥ እንዳልቻለ ገልጿል። ሮይተርስ ከኢትዮጵያን ሠራዊት ቃል አቀባይ፣ ከአማራ ክልል አስተዳደር እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጽህፈት ቤት ስለጥቃቱ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት አመልክቷል።

የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ሐሙስ ዕለት በትዊተር ገጻቸው ላይ “በአሸባሪው ህወሓት ምክንያት ችግር ውስጥ የሚገኘውን ሕዝባችንን ነፃ ለማውጣት በሁሉም ግንባሮች የማያዳግም ኦፕሬሽን በየትኛውም ጊዜና ሰዓት ሊደረግ ይችላል” በማለት አስፍረው ነበር። ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የተቀሰቀሰው ውጊያ በትግራይ ክልል ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያፈናቀለ ከመሆኑ በተጨማሪ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ለረሃብ እንዳጋለጠ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

መንግሥት ወደ ክልሉ እርዳታ እንዳይገባ እንቅፋት ፈጥሯል እየተባለ የሚወቀስ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ክሱን አይቀበለውም። የፌደራሉ ሠራዊት በሰኔ ወር ላይ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ ክልል መውጣቱን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልል ገፍተው መግባታቸው ይታወሳል። በዚህም ሳቢያ በሁለቱም ክልሎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቀያቸው ለመፈናቀል የተገደዱ ሲሆን 1.7 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ የምግብ እርዳታን ለመጠበቅ ተገደዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *