በኢትዮጵያ መንግሥት ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት ሰባቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ከአገር መውጣታቸው ተገለጸ።

የተመድ የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) የኮምዩኒኬሽን ባለሙያ ሃያት አቡ-ሳሌህ ሰባቱ ሠራተኞች ከአገር መውጣታቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። ሃያት አቡ-ሳሌህ ሰባቱ የተመድ ሠራተኞች መቼ እና በምን ሁኔታ ከአገር እንደወጡ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት በአገር ውስጣ ጉዳዮች ጣልቃ ገብተዋል ያላቸውን በኢትዮጵያ የድርጅቱ ውስጥ የሚሰሩ ሰባት የሥራ ኃላፊዎች በ72 ሰዓታት አገር ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበረ ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰባቱ የተመድ ሠተኞች ከአገር እንዲወጡ ያዘዘበትን ምክንያት በገለጸበት መግለጫ ላይ፤ ሠራተኞቹ የአገሪቱን ሉአላዊነትን የሚጥስና ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የሚሆኑ ድርጊቶችን ፈጽመዋል ብሎ ነበር። መንግሥት በዚሁ መግለጫው ከሠራዊቱ ጋር ጦርነት ውስጥ ላሉት የህወሓት ኃይሎች የሰብአዊ እርዳታና የግንኙነት መሳሪያዎች እንዲደርስ ድጋፍ አድርገዋል ብሏል።

በተጨማሪም “ስምምነት የተደረሰባቸውን የደኅንነት አሰራሮችን” መጣስና ለእርዳታ አቅርቦት ተሰማርተው ሳይመለሱ የቀሩ ከ400 በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎች “ህወሓት ለወታደራዊ እንቅስቃሴዎቹ እየተገለገለባቸው ናቸው” በማለት እንዲመለሱ ለማድረግ አስፈላጊውን ጥረት አላደረጉም በማለት ቅሬታ አቅርቧል። መንግሥት በ72 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ካዘዛቸው የተመድ ሠራተኞች መካከል የተመድ የሕጻናት አድን ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አደል ኾደር እና የተመድ የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ማርሲ ቪጎዳ ይገኙበታል።

“ከአገር የወጡት በሌሎች ይተኩ”

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተባባሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት ሠራተኞች በሌሎች እንዲተኩ ተመድን ጠይቀዋል። አምባሳደር ታዬ በትዊተር ገጻቸው ላይ፤ የሰብዓዊ እርዳታ በማቅረብ ሥራ ላይ ያለንን ትብብር ለማስቀጠል ተመድ ከአገር እንዲወጡ የታዘዙ ሠራተኞችን በአስቸኳይ እንዲተካ እንደጠይቃለን ብለዋል። አምባሳደር ታዬ ጨምረውም አዲስ የሚተኩ ሠራተኞች በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ከተመድ ድርጅቶች ጋር በትብብር እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።

“የመንግሥት ውሳኔ አሳሳቢ ነው”

የኢትዮጵያ መንግሥት ሰባቱ የተመድ ሠራተኞች ከአገር እንዲወጡ ማዘዙን ተከትሎ በርካታ አካላት የመንግሥት ውሳኔን ተቃውመው ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ የአሜሪካ፣ ጀርመን እና የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥታት እንዲሁም የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔውን መልሶ እንዲያጤን ከጠየቁት መካከል ይገኙበታል።

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ኢትዮጵያ የተቋማቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ከአገር እንዲወጡ መወሰኗ “አስደንግጦኛል” ብለው ነበር። ጉተሬዝ ሐሙስ ዕለት ባወጡት መግለጫ ላይ ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት ሠራተኞች “. . . አስፈላጊ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው” ብለው ነበር። አሜሪካ፣ ኢትዮጵያ በተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት የሚሠሩ ሰባት ሠራተኞች በአስቸኳይ ከአገር እንዲወጡ ማዘዟ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው ስትል ተቃውሞዋን ገልጻለች።

በተመሳሳይ አዲስ አበባ የሚገኙት የዩናይትድ ኪንግደምና የጀመርን ኤምባሲዎች የኢትዮጵያ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ግዛቱን ለቀው እንዲወጡ ያዘዘበት ውሳኔ እንዳሳሰባቸው ገልጸው ነበር። የአውሮፓ ሕብረት በበኩሉ ትናንት ሰኞ ምሽት ባወጣው መግለጫ ላይ፤ ሕብረቱ እና አባል አገራቱ የኢትዮጵያን መንግሥት ውሳኔ አጥብቆ ይቃወማል ብሏል። ሕብረቱ ሠራተኞቹን ከአገር የማስወጣት ውሳኔ አስቸኳይ እርዳታ የሚሹ ሚሊዮኖች ባሉባት ኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ስራን ያስተጓጉላል ብሏል። በመጨረሻም ሕብረቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔውን ሳይዘገይ እንዲቀለብስ ጠይቋል።