በመጋቢት 2010 ዓ.ም. ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣን በመረከብ ጠቅላይ ሚኒስትርነትን የተቆናጠጡት፣ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ የሰላም ኖቤል ሽልማት የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡ በመጀመርያዎቹ ወራት በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝተው ነበር፡፡ በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረው ደስታ ለ27 ዓመት አገሪቱን ሲያስተዳድር የነበረው የኢሕአዴግ የአገዛዝ ሥርዓት በኢትዮጵያውን ዘንድ የደረሰበትን ከፍተኛ ውግዘት ማሳያ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የኢሕአዴግ አራቱን አባል ድርጅቶችና አጋር ፓርቲዎችን በማካተት ብልፅግና የሚባል አዲስ ውህድ ፓርቲ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠንሳሽነት ሲመሠረት፣ ውሳኔው ያልተዋጠለት ሕወሓትና ታዋቂ ፖለቲከኞቹ በግልጽ መስመር ለይተው መንቀሳቀስ የጀመሩት በ2012 ዓ.ም. የመጀመርያዎቹ ወራት ነበር፡፡ በጊዜው የፌዴራል መንግሥቱን በሚመራና በትግራይ አመራሮች መካከል የነበረው የሁለት ወገን የፖለቲካ ተቃርኖና ሽኩቻ እየሰፋና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ፣ ልዩነቱ ጫፍ ሲደርስ የሁለቱ አካላት የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የተጀመረውና መቋጫ ያልተገኘለት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሆኗል፡፡

በዚህ ሁሉ ወጣ ውረድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የካቲት 2011 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ለኢትዮጵያ ለሕዝብ ቃል ከገቡዋቸው በርካታ ጉዳዮች ውስጥ እንዱ የሆነው የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ፣ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት አምስት አገራዊ ምርጫዎች በተለየ ቅቡልነት ኖሮት እንዲከሄድ ለማስቻል የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ገለልተኛ ሆኖ እንደገና እንዲቋቋም መደረጉ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

እንደ አዲስ የተቋቋመው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህን በብዙዎች ዘንድ ተስፋ የተጣለበት አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ በነበረበት ወቅት፣ በዓለም ላይ በተከሰተው ኮቪድ-19 ወረርሽኝና በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ሰው ሠራሽ ግጭቶች ምክንያት፣ አገራዊ ምርጫው ለሦስት ጊዜያት ተራዝሞ ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ተካሂዷል፡፡ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ በርካታ ምዕራባውያን አገሮች ፊት እንደነሱትና ጫናው የበረታበት ኢትዮጵያ መንግሥት፣ ምዕራባውያን አገሮች በተለያዩ ጊዜያት ሊካሄድ የታሰበው ምርጫ ዕርባና ቢስ እንደሆነና በምርጫው ወቅት አገራዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል በተደጋጋሚ መተንበያቸው በተደጋጋሚ ይወሳል፡፡

በሰኔ ወር በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ከ37 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵውያን ድምፅ ሲሰጡ፣ የምርጫ ፉክክር ከተደረገባቸው 436 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችሉትን 410 መቀመጫዎች ያገኘው ብልፅግና መስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በተከናወነው የፓርላማ ውሎ ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል፡፡ አዲስ  የተመረጡትና መስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም.  የመጀመርያ ሥራቸውን የጀመሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዓብይ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ከሰየሙ በኋላ፣ የተካሄደው ምርጫም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) መሰየም አልዋጥላቸው ያሉ በርካታ ምዕራባውያን አገሮችን አንገት የሚያስደፋ፣ ወይም የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታና ሕዝባዊ አንድነት በግልጽ ሊያሳይ የሚያስችል ነው ተብሎ የታሰበበት የመንግሥት ምሥረታ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

በዓይነቱ ለየት ያለውና በርካታ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች በተለይም የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ አብዱላሂ (ፋርማጆ)፣ የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ፣ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሐመዱ ቡሃሪ፣ የደቡብ  ሱዳን  ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር  ማርዲያት፣ የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል፣ የዴሞክራት ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዣን ሚሼል ሊኮንዴና ሌሎች የአፍሪካና የቀጣናው ከፍተኛ ባለሥልጣናትና በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት የመንግሥት ምሥረታው በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት መሪዎችም ኢትዮጵያን ያሞካሹ ንግግሮች ያሰሙ ሲሆን፣ ለአብነትም ኡሁሩ ኬንያታ አፍሪካውያን ነፃነታቸውን ለመወሰን ባደረጉት ጥረትና ተጋድሎ ኢትዮጵያ እናትና ብቸኛዋ ቅኝ ያልተገዛች አገር ነች በማለት ገልጸዋታል፡፡ እንዲሁም አፍሪካውያን ወንድምና እህት ከቅኝ ግዛት ነፃ እንዲወጡና የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እንዲወስኑ አብራ የቆመች የአፍሪካ የሁላችንም እናት ነች ብለዋል፡፡

‹‹ሁላችንም እንደምናቀው እናት ሰላም ካልሆነች የትኛውም ቤተሰብ ሰላም አይሆንም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹እዚህ ቆሜ ስናገር ኢትዮጵያን ለመገንባት በምታደርገው ጥረት ድጋፋችንን ለመግለጽ፣ ኬንያውያን ከኢትዮጵያውን ወንድሞችና እህቶች ጋር በጋራ በመሥራት ሰላሙ የተረጋጋና የበለፀገ ጠንካራ ቀጣና ለመመሥረት ድጋፋችንን ለመግለጽ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ ‹‹ዛሬ ሕዝቡ በድምፁ አገሪቱን እንዲመሩ፣ ሰላም እንዲሰጡና መረጋጋት እንዲፈጠር ዕድል ሰጥቶዎታል፡፡ በመሆኑም የመረጡትንም ሆነ ያልመረጡትን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ወደ አንድ ለማምጣት የእኛ ፀሎትና ድጋፍ አይለየዎትም፤›› ብለዋቸዋል፡፡

የናይጄሪው ፕሬዚዳንት ቡሃሪ የኢትዮጵያውን ለዴሞክራሲ መርሆች ግንባታ ያላቸውን  ጥንካሬና ትጋት አደንቃለሁ ብለው፣ በሰኔ 2013 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ የታየው የምርጫ ውጤት ኢትዮጵያውያን ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ ምርጫ እንዲኖር ያላቸው ፍላት ማሳያ እንደሆነ በፅኑ አምናለሁ ብለዋል፡፡  በዚህም ሁሉም አካላት ለጋራ አንድነትና ብልፅግና፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ልማት በጋራ እንዲሠሩ በመጠየቅ ናይጄሪያ የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት እንዲጠበቅ ሁልጊዜም ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል፡፡ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሙሐመድ አብዱላሂ (ፋርማጆ) በበኩላቸው፣ ስድስተኛው አገራዊ የምርጫ ውጤት ኢትዮጵያውያን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ላይ ያሳደሩት መተማመን ተስፋ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሶማሊያ በታሪክ በትብብር ላይ የተመሠረተ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነትና ወንድማማችነት እንዳላቸው በመግለጽ፣ ሁለቱ ሕዝቦች ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን እየተጋፈጡ መሆናቸውንና ከቀጣናዊና አኅጉራዊ ወዳጆች ጋር በመሆን የተረጋጋና የተዋሀደ የአፍሪካ ቀንድ ለመመሥረት እየሠሩ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

ባለፉት 60 ዓመታት ውስጥ ኡጋንዳውያን ብሔርንና እምነትን መሠረት በማድረግ እኔ ከዚህኛው አንዱ ከዚያኛው የሚል ማንነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ ችግር ውስጥ ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን የብሔር ፖለቲካን በመተው ወደ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ላይ በመመለሳቸው አገራቸውን ማዳን እንደቻሉ የገለጹት ደግሞ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ናቸው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያውያን ሁለቱን ጉዳዮች እንዲያስቡ እመኛለሁ ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ሲነጋገሩ የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌም ይታያሉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ሲነጋገሩ የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌም ይታያሉ

የደቡብ  ሱዳን ፕሬዚዳንት  ሳልቫ ኪር ማርዲያት በሌላ በኩል፣ ‹‹ኢትጵያውያን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጎን እንድትቆሙና ወደ ሰላም እንድታመሩ እጠይቃለሁ፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ታላቅ እናታችን ናት፡፡ ለደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያ ባትኖረን አሁን ያለንበት ላይ አንገኝም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በደቡብ ሱዳን ተከስቶ የነበረው አስከፊ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ እንዲከሰት አንፈልግም፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም እዚህ በመጡ ጊዜ የተናገሩትን በማስታወስ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ በፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዘመን ደቡብ ሱዳንን ከሱዳን ጋር በማስማማት ነፃነታቸውን እንዲያገኙ ዕርዳታ ማድረጋቸውን ተናግረው አመሥግነዋል፡፡

የጂቡቲ ፕሬዚዳንት  ኢስማኤል ኡመር ጊሌ በቀደሙት የአቢሲንያ ግዛቶች ቅድመ ታሪክ  ኢትዮጵያ በርካታ አፍሪካዊ ጉዳዮችን ይዛ ትንቀሳቀስ እንደነበር በማስታወስ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት መሥራች አገር መሆኗን ገልጸዋል፡፡ በቅርብ ጊዜያትም ኢትዮጵያ እያሳየች ያለው ዕድገት ለአኅጉሩና ለአፍሪካ ቀንድ መነሳሳት ጠቃሚ መሆኑን በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር በሚለው የተኮላተፈ አማርኛ ንግግራቸውን ዘግተዋል፡፡ የመንግሥት ምሥረታ ሥነ ሥርዓቱና በዓለ ሲመቱ በተከናወነበት መስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ለተመረጡት አዲሱ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት በትዊተር ገጻቸው ያስተላለፉት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ በኢትዮጵያውን ከፍተኛ የሆነ ትችትና ወቀሳ ተሰንዝሮባቸዋል፡፡

ከአፍሪካ መሪዎች መልዕክት መጠናቀቅ በኋላ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ በዚህ ወሳኝና ፈታኝ ወቅት በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በዱር በገደሉ በቁር በሀሩሩ ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ለሚገኙት ለአገር መከላከያ ሠራዊት አባላትና ለመላው የፀጥታ አካላት ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ የምዕራባውያን የዲፕሎማሲ ግፊት በኢትዮጵያ ላይ የፈጠረውን ጫና በመጠቆም፣ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷንና ነፃነቷን በሚነካ ማንኛውም ጉዳይ ላይ ድርድር እንደማታደርግ አስታውቀዋል፡፡ በቅርቡም ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሔራዊ የምክክር መድረክ እንደሚጀመር በመግለጽ፣ ውይይቱ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን በማካተት እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ በማንነቱ የማይደራደር መሆኑ ዕሙን ነው፤›› ብለው፣ ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ጉዞ ስታደርግ የወዳጆችን አጋርነት እንደምትፈልግ አስገንዝበው፣ ‹‹ድጋፍ በፈለገችባቸው ጊዜያትም ስለደረሳችሁለት ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ሰይፍ ይዘን ስንዘምትም ሆነ ሰይፍ ይዘን ስንነሳ ፀባችን ኢትዮጵያ ጠል ከሆኑት ጋር ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ የተሟላ አቋም ያለው የፀጥታ ኃይል ታደራጃለች ሲሉም አስትውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል መርህ አፍሪካ በዓለም መድረክ ራሷን ችላ እንድትቆምና ችግሮቿን በራሷ እንድትፈታ በማድረግ ረገድ፣ የበኩሏን ሚና መወጣቷን አበክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *