አዲስ አበባ ውስጥ ሁለት ፖሊሶች አንዲት ሴትን በአስከፊ ሁኔታ ሲደብድቡ የሚታይበት ተንቀሳቃሽ ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መታየቱን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከአርብ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ በርካታ ሰዎች ሲጋሩት የነበረው ቪዲዮ ላይ ሁለት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት አንዲት ሴትን በህጻን ልጇ ፊት በአሰቃቂ ሁኔታ ሲደበድቡ የሚያሳይ ነው። ቪዲዮው በስፋት ከመጋራቱ በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ቁጣና ወግዘትን አስከትሎ መንግሥት በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ሲጠይቁ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሙያው “ሥነ ምግባር ውጪ” ባለው ሁኔታ በግለሰቧ ላይ ድብደባ የፈጸሙት አባላቱ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን አስታውቋል። በግለሰቧ ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ጥቃቱን የፈጸሙት ምክትል ኢንስፔክተር ጃፋር አሊ እና ኮንስታብል መስፍን በቀለ የተባሉ የከተማው ፖሊሶች በቆሬ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ያሰማራቸው አባላቱ መሆናቸውን ገልጿል።
ፖሊስ እንዳለው የፖሊስ አባላቱ ድብደባውን የፈጸሙት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ቦታው ሚካኤል አደባባይ አካባቢ መስከረም 21/2014 ዓ.ም ከቀኑ አምስት ሰዓት ላይ ነው። የአዲስ አበባ ፖሊስ ድርጊቱን በተመለከተ በማኅበራዊ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ተጠርጣሪዎቹ የፖሊስ ባልደረቦች የፈጸሙት ድብደባን “አስነዋሪ” ሲል የገለጸው ሲሆን በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጠራ እንደሚገኝም አመልክቷል።
በግለሰቧ ላይ ከፈጸሙት ድብደባ ጋር በተያያዘ በፖሊስ አባላቱ ላይ እየተካሄደ ያለው ምርመራ ተጣርቶ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድና ውጤቱን ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል። እንዲህ አይነቱን ድርጊት የማይታገስ መሆኑን የገለፀው የከተማው ፖሊስ ባለፈው ዓመት ውስጥ ብቻ በልዩ ልዩ ጥፋቶች ውስጥ የተገኙ “171 የፖሊስ አመራሮችና አባላቱን” ከሠራዊቱ እንዲሰናበቱ ማድረጉን አስታውሷል። ከእነዚህ ውስጥም 29ኙ ከሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ መሆኑን አመልክቷል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጨምሮም ሕግን በመተላለፍ ጥፋት በሚፈጽም አባላት እና አመራሮቹ ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቆ “ኅብረተሰቡ እንዲህ አይነት ከፖሊስ የሙያ ሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ድርጊቶች በሚፈፀሙበት ወቅት በፍጥነት ጥቆማ እንዲያደርግ” ጥሪ አቅርቧል።
ምንጭ – ቢቢሲ