የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረገጽ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ቢቢሲ ከፌደራል ፖሊስ አረጋገጠ።
ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ ከቅዳሜ መስከረም 22/2014 ዓ.ም ረፋድ ጀምሮ ያለበትን እንደማያውቁ የሥራ ባልደረባውና የቅርብ ጓደኞቹ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ በፌደራል ፖሊስ እጅ ስር እንደሚገኝ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። ኃላፊው እንደተናገሩት ተስፋዓለም በአሁኑ ጊዜ “የፌደራል ፖሊስ የምርመራ ቢሮ የሜክሲኮ ማቆያ እንደሚገኝ” ገልጸው፤ “ምንም የሚፈጠር ነገር የለም። ያለውን ነገር እያጣራን ነው። ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የወንጀል ምርመራ ቢሮ ምክትል ኃላፊው፤ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም በቁጥጥር ሥር ስለዋለበት ጉዳይ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ቅዳሜ ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ በተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ የተሰሙ የተቃውሞ ድምጾችን የሚያሳይ ቪዲዮ በኢትዮጵያ ኢንሳይደር የፌስቡክ ገጽ ላይ አጋርቶ ነበር። ተስፋዓለም ወደልደየስ ዜናና ትንታኔ የሚቀርብበት ‘ኢትዮጵያ ኢንሳይደር’ የተባለው ድረገጽ መስራችና ዋና አዘጋጅ ሲሆን፤ ገጹ በተለይ ወቅታዊ የፖለቲካ ዜናዎችን በማቅረብ እየታወቀ ያለ ከመሆኑ በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይም በርካታ ተከታዮችን በማፍራት ላይ ያለ ነው።
ቢቢሲ ከታማኝ ምንጮቹ መረዳት እንደቻለው ጋዜጠኛ ተስፋዓለም በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ መኖሪያ ቤቱ ላይ ፍተሻ መካሄዱን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ኢንሳይደር የተስፋዓለም ባልደረባ የሆነው ሐሚድ አወል ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ ተስፋዓለም ቅዳሜ አዲስ አበባ እንዲሁም እሁድ ቢሾፍቱ ላይ የተከበረውን የኢሬቻ በዓል ለመዘገብ እቅድ ይዞ ተለያይተው ነበር። ተስፋዓለም ቅዳሜ በተከበረው በዓል ላይ ያቀረጸውን ቪዲዮና ፎቶግራፎች በዕለቱ አስከ ጠዋት ሁለት ሰዓት ድረስ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ካጋራ በኋላ በስልክ ማግኘት እንዳልቻለ ሐሚድ ለቢቢሲ ገልጿል።
በተለይ ተስፋዓለምን ማግኘት አስቸጋሪ ከመሆኑ በፊት በመስቀል አደባባይ በተከበረው በዓል ላይ የተሰማውን ተቃውሞ የሚያሳይ ቪዲዮ ነበር በመጨረሻ ያጋራው። ተስፋዓለም ያለበትን ለማወቅ ጓደኞቹና የሥራ ባልደረባው ቅዳሜና እሁድ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው መቅረቱን ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ቅዳሜ ዕለት የተከበረውን የኢሬቻ በዓልን ለመዘገብ ተስፋዓለም ከማለዳ ጀምሮ በስፍራው እንደሚገኝ የሚያውቀው ባልደረባው ሐሚድ፤ በተደጋጋሚ በስልክና በጽሁፍ መልዕክት ሊያገኘው ሞክሮ እንደነበርና አስከ ሰኞ ጠዋት ድረስ የት እንዳለ እንደማያውቅ ለቢቢሲ ገልጿል።
ተስፋዓለም ወልደየስ ከዚህ ቀደም በታዋቂዎቹ የእንግሊዝኛው አዲስ ፎርቹን እንዲሁም የአማርኛው አዲስ ነገር ጋዜጦች ላይ የሠራ ሲሆን ከሙያው ጋር በተያያዘ ለስደት ተዳርጎ ቆይቷል። ፖሊስ ተስፋዓለምን በቁጥጥር ስር ያዋለበትን ምክንያት ባይገልጽም ከሥራው ጋር በተያያዘ ሊሆን እንደሚችል የቅረብ ጓደኞቹ ግምታቸውን ተናግረዋል። የአሁኑ እስር ለተስፋዓለም የመጀመሪያው እንዳልሆነ የሚገልጹት ጓደኞቹ፣ ከዓመታት በፊት ከዞን ዘጠኝ ብሎገሮች ጋር ተይዞ ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ መቆየቱ ይታወሳል።
ተስፋዓለም ከእስር ከወጣ በኋላ በኬንያና በኡጋንዳ ውስጥ በስደት በቆባቸው ጊዜያት ኢትዮጵያንና የአካባቢው አገራትን የሚመለከቱ ዜናና የተለያዩ ፊቸሮች የሚቀርብበት ጋዜጣ ያዘጋጅ ነበር። ቆይቶም ወደ ጀመርን በመሄድ የጀርመን ድምጽ የአማርኛው ክፍል ውስጥ ሲሰራ የቆየ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የመጣውን አስተዳደራዊ ለውጥ ተከትሎ ወደ አገሩ በመመለስ የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረገጽን አቋቁሞ በጋዜጠኝነት እየሰራ ይገኛል።
ምንጭ – ቢቢሲ