የኢትዮጵያ መንግሥት ሰባት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞችን ከግዛቱ ለቀው እንዲወጡ የወሰነባቸውን ምክንያቶች ይፋ አደረገ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው የዓለም አቀፉ ድርጅት ሠራተኞች የአገሪቱን ሉአላዊነትን የሚጥስና ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የሚሆኑ ድርጊቶችን ፈጽመዋል ሲል ከሷል። ሐሙስ መስከረም 20/2014 ዓ.ም እንደተገለጸው በመንግሥታቱ ድርጅት የተለያዩ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት የሚሰሩት ግለሰቦች በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል በሚል ነበር በ72 ሰዓታት ከአገሪቱ እንዲወጡ የታዘዙት። የመንግሥታቱ ድርጅት የኢትዮጵያን እርምጃ እንደማይቀበለው ዋና ፀሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አርብ ዕለት መናገራቸውን፤ እንዲሁም የድርጅቱ ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅ የኢትዮጵያ እርምጃ በተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ባለመሆኑ ባለሥልጣናቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሆኑ መግለጻቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

መንግሥት የድርጅቱን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከአገር እንዲወጡ ያዘዘበትን ምክንያት በዘረዘረበት መግለጫው ከሠራዊቱ ጋር ጦርነት ውስጥ ላሉት የህወሓት ኃይሎች የሰብአዊ እርዳታና የግንኙነት መሳሪያዎች እንዲደርስ ድጋፍ አድርገዋል ብሏል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሠሜን ኢትዮጵያ ከተከሰተው ሁኔታ ጋር በተያያዘ የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች የተቋሙን መርኅ ሳያከብሩ መገኘታቸውን ጠቅሶ፤ እነዚህን ከባድ ጥሰቶችንም የሚመለከታቸው የድርጅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች እንዲያውቁት ቢያደረግም ውጤት እንዳላስገኘ ገልጿል። ነገር ግን በኒውዮርክ ለሚገኙት በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ መልዕክተኛ የድርጅቱ የሕግ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የላከው ማስታወሻን ተመልክቻለሁ ብሎ ሮይተርስ እንደዘገበው፣ ሠራተኞቹ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን የሚያመለክት ምንም አይነት መረጃ አለመቀበሉን ገልጿል ሲል ዘግቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚለው በመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች የሚፈጸሙት አሳሳቢ ጥሰቶች በመቀጠላቸው እንደ መጨረሻ አማራጭ መንግሥት “የተወሰኑ የድርጅቱ ተቋማት ባለሥልጣናት አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ጠይቋል” ብሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት በሦስት ቀናት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሠራተኞቹ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን ከመጥቀሱ ውጪ በወቅቱ የሰጠው ዝርዝር ማብራሪያ አልነበረም። እርምጃውን በተመለከተ ያለውን ግራ መጋባት ለማጥራት በሚል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል መንግሥት በሰጠው መግለጫ በድርጅቱ ሠራተኞች ተፈጽመዋል ያላቸውን የተወሰኑ ጥሰቶች ገልጿል።

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት ከግዛቱ እንዲወጡ ያዘዛቸው ግለሰቦች “የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶችን እና የግንኙነት መሳሪያዎችን ለህወሓት መገልገያነት አሳልፈው ሰጥተዋል” የሚል ክስ አቅርቦባቸዋል። በተጨማሪም “ስምምነት የተደረሰባቸውን የደኅንነት አሰራሮችን” መጣስና ለእርዳታ አቅርቦት ተሰማርተው ሳይመለሱ የቀሩ ከ400 በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎች “ህወሓት ለወታደራዊ እንቅስቃሴዎቹ እየተገለገለባቸው ናቸው” በማለት እንዲመለሱ ለማድረግ አስፈላጊውን ጥረት አላደረጉም በማለት ቅሬታ አቅርቧል። ከዚህ ባሻገርም መንግሥት ለውሳኔው ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ግለሰቦቹ “አሳሳች የሆኑ መረጃዎችን በማሰራጨትና የሰብአዊ እርዳታን ፖለቲካዊ” አድርገውታል በሚል ከሷቸዋል።

እነዚህ ድርጊቶች በአገሪቱ ሉአላዊነት ላይ የተፈጸሙ ጥሰቶች መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል። ይህንንም ተከትሎ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ምክንያት የሚካሄደው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንደማይስተጓጎል እምነቱ መሆኑን በመግለጽ፤ ድርጅቱ ከአገር እንዲወጡ የታዘዙትን ሠራተኞቹን በአስቸኳይ በመተካት የሰብአዊ እርዳታ ሥራው እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል። ጨምሮም አንዳንድ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላት በህወሓት በኩል የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ችላ በማለት በመንግሥት በኩል የሚወሰዱ የአንድ ሉአላዊ መንግሥት ኃላፊነት የሆኑ እርምጃዎችን እንደ ችግር ያነሳሉ በማለት ወቅሷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ዓላማቸው የሕዝቡን ስቃይ ለማቃለል ከሚንቀሳቀሱት የመንግሥታቱ ድርጅትና ተቋማቱ ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ፣ እንዲሁም በአገሪቱ ሉአላዊነትና ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ስጋትን ከማይደቅኑ ከየትኞቹም ተቋማት ጋር በጋራ መሥራቱን እንደሚቀጥል በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

ሰባቱ የተመድ ሠራተኞች

የኢትዮጵያ መንግሥት በሦስት ቀናት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ሐሙስ ዕለት ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሠራተኞቹ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን ገልጾ ነበር። ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ የታዘዙት ግለሰቦች በተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚሰሩ የተለያዩ አገራት ዜጎች ናቸው።

ከግለሰቦቹ መካከል አምስቱ በድርጅቱ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ)፣ አንደኛዋ በድርጅቱ የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እንዲሁም አንደኛው የድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ውስጥ በኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚሰሩ ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት

የኢትዮጵያ መንግሥትን ውሳኔ ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኢትዮጵያ የተቋማቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ከአገር እንዲወጡ መወሰኗ “አስደንግጦኛል” ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።

ዋና ፀሐፊው ሁሉም የድርጅታቸው ሰብዓዊ ተግባራት የሚመሩት በሰብዓዊነት፣ ከአድልዎ ነጻ በሆነ መንገድ፣ በገለልተኛነት እና በነጻነት መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህም ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በችግር ላይ ላሉ ሰዎች የተለያየ እርዳታ እያቀረበ መሆኑን አመልክተዋል። ዋና ፀሐፊ ጉቴሬዝ “የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች አስፈላጊ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው” ብለው ነበር።

አሜሪካና አውሮፓ አገራት

አሜሪካ፣ ኢትዮጵያ በተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት የሚሰሩ ሰባት ሠራተኞች በአስቸኳይ ከአገር እንዲወጡ ማዘዟ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው ስትል ተቃውሞዋን ገልጻለች። በተመሳሳይ አዲስ አበባ የሚገኙት የዩናይትድ ኪንግደምና የጀመርን ኤምባሲዎች የኢትዮጵያ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ግዛቱን ለቀው እንዲወጡ ያዘዘበት ውሳኔ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

ሁለቱ ኤምባሲዎች በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት በእርዳታ ሥራ ላይ የተሰማሩት ግለሰቦች ከአገሪቱ እንዲወጡ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ መንግሥት እርምጃውን እንዲያጤነው ጠይቀዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ