በቤኒሻንጉልና ጉምዝ ክልል በመተከልና ካማሺ ዞኖች በተለይም በሴዳል ወረዳ  ከመስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች ‹‹የጉምዝ ታጣቂዎች›› ብለው የሚጠሯቸው ኃይሎች በወረዳው የሚኖሩ ሕፃናትን፣ ሴቶችንና አረጋውያንን ጨምሮ ከ145 በላይ የሚገመቱ የጉምዝ ብሔር ተወላጅ የሆኑ አባወራዎችን (ቤተሰቦችን) ማገታቸውን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዓርብ መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ.ም. አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ በወጣው ሪፖርት እንዳብራራው ከታጣቂዎቹ በማምለጥ ወደሌሎች  አካባቢዎች ሸሽተው የሚገኙ ነዋሪዎች እንደሚገልጹት፣ ከጥር ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በወረዳው በሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ከመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ ሆነው ቆይተዋል። በታጣቂዎቹ የተገደሉ መኖራቸውንና ሌሎቹም በአስከፊ ሥቃይ ውስጥ መሆናቸውን ካመለጡት ነዋሪዎች መረዳቱን ኮሚሽኑ ገልጿል።

መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም. በደረሰ ጥቃት ምክንያት 5,000 የሚሆኑ ተጨማሪ የሴዳል ወረዳ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ለጊዜው በወረዳው መስተዳድር ግቢ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ መረጃ እንዳለው የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ባደረገው ክትትል ከመስከረም 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎችና በታጣቂ ኃይሎች መካከል ‹‹ውጊያ›› በመካሄድ ላይ መሆኑንና ከመስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ነዋሪዎችን ወደ ዳሊቲ ከተማ ለማሸሽ ጥረት እየተደረገ መሆኑን መገንዘቡን አስረድቷል። የሴዳል ወረዳ አመራሮችም ሆኑ ከወረዳው የሸሹ ነዋሪዎች በአካባቢው የተሰማራው የፀጥታ ኃይል በቂ እንዳልሆነ እየገለጹ መሆኑን ጠቁሞ፣ በአካባቢው ያለውን የፀጥታ ሁኔታና የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ በፌዴራል መንግሥቱና በአካባቢው ኮማንድ ፖስት እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች በተሻለ ፍጥነት ሊተገበሩና ሊጠናከሩ እንደሚገባ አሳስቧል።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በካማሺና በመተከል ዞኖች በተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት፣ አካልና ንብረት አደጋ ላይ የጣሉ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቢቆዩም፣ የፌዴራልና ክልል መንግሥታት የወሰዷቸው ዕርምጃዎች አደጋውን ለመቀልበስና የሲቪል ሰዎችን ሕይወት ከሞት ለመታደግ በቂ ባለመሆናቸው፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሁለንተናዊ መፍትሔ የማፈላለጉ ሒደት አሁንም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅት በሴዳል ወረዳ ታግተው የሚገኙ ነዋሪዎች ለተባባሰ የሰብዓዊ ቀውስ እንዳይጋለጡና ከወረዳው ተፈናቅለው በዳሊቲ ከተማና በሌሎች ጊዜያዊ መጠለያዎች የሚገኙ ነዋሪዎች አስፈላጊው የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርስላቸው አፋጣኝ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ ማሳሰባቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *