የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኢትዮጵያ የተቋማቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ከአገር እንዲወጡ መወሰኗ “አስደንግጦኛል” ሲሉ ሐሙስ ምሽት ባወጡት መግለጫ አስታወቁ።
ዋና ፀሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የኢትዮጵያ መንግሥት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ የሚገኙ ሰባት ግለሰቦች በአስቸኳይ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማዘዙ ተከትሎ ነው የተሰማቸውን የገለጹት።የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመንግሥት ውሳኔውን በተመከተ ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ግለሰቦቹ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል በማለት በ72 ሰዓታት ከኢትዮጵያ እንዲወጡ አዟል።
ዋና ፀሐፊው በመግለጫቸው ሁሉም የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ ተግባራት የሚመሩት በሰብዓዊነት፣ ከአድልዎ ነጻ በሆነ መንገድ፣ በገለልተኛነት እና በነጻነት መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህም ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በችግር ላይ ላሉ ሰዎች ምግብ፣ መድኃኒት፣ ውሃ እና ንጽሕና መጠበቂያ የመሳሰሉ ሕይወት አድን እርዳታዎችን እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።”የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞችም ይህን በኢትዮጵያ እየተገበሩ ስለመሆኑ ሙሉ እምነት አለኝ” በማለት፤ ተመድ ሰብዓዊ እርዳታን የሚጠብቁ ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ገልጸው።
ዋና ፀሐፊ ጉቴሬዝ “የሚመለከታቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች አስፈላጊ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው” ብለዋል።የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግለሰቦቹን በተመከተ ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ግለሰቦቹ በአገሪቱ ውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ገብተዋል ያለ ሲሆን በ72 ሰዓታት ከኢትዮጵያ እንዲወጡም አዟል።
መንግሥት በ72 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ያዘዘ
- የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን የኢትዮጵያ ተወካይ አደል ኾደር
- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ መስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ማርሲ ቪጎዳ
- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ መስተባበሪያ የጽህፈት ቤቱ የሰላምና ልማት አማካሪ ክሰዌሲ ሳንስኩሎቴ
- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ መስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ሳኢድ ሞሐመድ ሄርሲ
- የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ድርጅት የክትትል፣ የሪፖርት እና አድቮኬሲ ቡድን መሪ የሆኑት ሶኒ ኦንዬግቡላ
- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ምክትል የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ የሆኑት ግራንት ሌኢተይ እና
- የተባበሩት መንግሥታት ተጠባባቂ የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ጋዳ ኤልታሂር ሙዳዊ
ሚኒስቴሩ በጻፈው ደብዳቤ ግለሰቦቹ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ስለገቡ የኢትዮጵያ መንግሥት በግዛቱ ውስጥ እንዲቆዩ ስለማይፈቅድ በሦስት ቀናት ውስጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ጠይቋል።አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበው ጦርነት በትግራይ ክልል ከተቀሰቀሰ በኋላ ከሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ምዕራባውያን አገራት ያልተገባ ጫና እያሳደሩ ነው ሲል ሲወቅስ ቆይቷል።
የምዕራባውያን መንግሥታት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የተባበሩት መንግሥት አካላት በትግራይ ውስጥ እርዳታ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት መንግሥት እያደናቀፈ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ሲከሱ ቆይተዋል።የተባበሩት መንግሥታት የትግራይ ክልል ይፋዊ ባልሆነ የሰብአዊ እርዳታ እገዳ ስር ነው ሲል የገለጸ ሲሆን፣ የድርጅቱ የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በክልሉ ረሃብ ሳይከሰት እንደማይቀር ገልጸዋል።
ጨምረውም የኢትዮጵያ መንግሥት የእርዳታ አቅርቦት የያዙ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዲገቡ እንዲያደርግ ጠይቀው “ይህ ችግር ሰው ሰራሽ ነው፣ መንግሥት እርምጃ ከወሰደ መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል” ሲሊ ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግረዋል።ኒውዮርክ ሚገኘው በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ተልዕኮ በሰጠው ምላሽ ወደ ትግራይ እርዳታ እንዳይገባ “እገዳ ተጥሏል የሚባለው ክስ መሰረተ ቢስ ነው” ሲል አጣጥሎታል።
ጨምሮም የረድኤት ድርጅቶች “እርዳታ ለማቅረብ የሚያስችሉ የጭነት ተሽከርካሪዎች እጥረት የገጠማቸው ቀደም ሲል ወደ ትግራይ እርዳታ ለማድረስ የተሰማሩ መኪኖች ሳይመለሱ በመቅረታቸው ነው” ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል።የኢትዮጵያ መንግሥት ዛሬ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ ላይ የድርጅቱ ኃላፊዎች በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባታቸው በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ከማዘዙ ውጪ የሰጠው ዝርዝር ማብራሪያ የለም።
ኢትዮጵያን ለቀው በ72 ሰዓታት ውስጥ እንዲወጡ የታዘዙት ግለሰቦች በተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሲሆን አምስቱ በድርጅቱ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ)፣ አንደኛዋ በድርጅቱ የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እንዲሁም አንደኛው የድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ውስጥ በተለያዩ ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚሰሩ ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በሚሰሩ ግለሰቦች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ዙሪያ ቅሬታ ሲያቀርብ እንደነበር የሚታወስ ነው።አንድ የተባባሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣንም በቀረበባቸው ቅሬታ ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ሌላ አገር መዘዋወራቸው ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።
የድርጅቱ ምክትል ተወካይ በመሆን ከአንድ ዓመት በላይ የሰሩት ማቲጂስ ሌ ሩቴ መንግሥት ባቀረበባቸው ቅሬታ ምክንያት ተቋማቸው ከኢትዮጵያ አንስቶ ወደሌላ አገር አዘዋውሯቸዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ