አሜሪካ፣ ኢትዮጵያ በተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት የሚሰሩ ሰባት ሠራተኞች በአስቸኳይ ከአገር እንዲወጡ ማዘዟ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው ስትል አወገዘች።
የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ጄን ሳኪ የኢትዮጵያ መንግሥትን እርምጃ ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፤ ያልተጠበቀውን የኢትዮጵያን ውሳኔ የአሜሪካ መንግሥት አጥብቆ ይቃወማል ብለዋል። በተመሳሳይ አዲስ አበባ የሚገኙት የዩናይትድ ኪንግደምና የጀመርን ኤምባሲዎች የኢትዮጵያ መንግሥት መንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች ግዛቱን ለቀው እንዲወጡ ያዘዘበት ውሳኔ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ሁለቱ ኤምባሲዎች በትዊተር ገጻቸው ላይ እናዳሰፈሩት በእርዳታ ሥራ ላይ የተሰማሩት ግለሰቦች ከአገሪቱ እንዲወጡ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ መንግሥት እርምጃው እንዲያጤነው ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ሰባቱ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ተቋማት ሠራተኞች በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል በማለት በ72 ሰዓታት ከግዛቱ ለቀው እንዲወጡ አዟል።
ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ኢትዮጵያ የተመድ ሠራተኞችን ከአገር ለማስወጣት የወሰነችው፤ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ምክንያት እየሞቱ ነው የሚል የማስጠንቀቂያ ሪፖርት ከወጣ በኋላ ነው ብለዋል። ቃልአቀባይዋ የኢትዮጵያ መንግሥት የምግብ፣ መድኃኒት እና ሌሎች ሕይወት አድን የሰብዓዊ አቅርቦቶች ለሚያስፈልጋቸው እንዳይደርሱ እክል መሆኑ እጅጉን አሳስቦናል ብለዋል።
“ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ማደናቀፍ እና የራስን ዜጋ መሠረታዊ አማራጭን ማሳጣት ተቀባይነት እንደሌለው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አባላት እና ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ለኢትዮጵያ መንግሥት ግልጽ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል። ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ጨምረውም፤ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት እንዲራዘም ምክንያት በሆኑ ግለሰቦች ላይ የፋይናንስ ዕቃባ መጣል የሚያስችል ትዕዛዝ መፈረማቸውን አስታውሰዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎችን በሚያደናቅፉ አካላት ላይ ፕሬዝደንቱ ያስተላለፉትን ውሳኔንም ሆነ “በእጃችን ያለ የትኛውንም አማራጭ ከመጠቀም ወደኋላ አንልም” ብለዋል።
“የኢትዮጵያ እርምጃ አስደንግጦኛል”
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኢትዮጵያ የተቋማቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ከአገር እንዲወጡ መወሰኗ “አስደንግጦኛል” ሲሉ ሐሙስ ምሽት መግለጫ አውጥተው ነበር። ዋና ፀሐፊው በመግለጫቸው ሁሉም የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ ተግባራት የሚመሩት በሰብዓዊነት፣ ከአድልዎ ነጻ በሆነ መንገድ፣ በገለልተኛነት እና በነጻነት መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህም ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በችግር ላይ ላሉ ሰዎች ምግብ፣ መድኃኒት፣ ውሃ እና ንጽሕና መጠበቂያ የመሳሰሉ ሕይወት አድን እርዳታዎችን እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።
ዋና ፀሐፊ ጉቴሬዝ “የሚመለከታቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች አስፈላጊ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው” ብለው ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እርምጃውን በተመከተ ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ግለሰቦቹ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል ያለ ሲሆን ለዚህም በ72 ሰዓታት ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ አዟል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሦስት ቀናት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሠራተኞቹ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን ከመጥቀሱ ውጪ የሰጠው ዝርዝር ማብራሪያ የለም። ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ የታዘዙት ግለሰቦች በተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚሰሩ የተለያዩ አገራት ዜጎች ናቸው።
ከግለሰቦቹ መካከል አምስቱ በድርጅቱ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ)፣ አንደኛዋ በድርጅቱ የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እንዲሁም አንደኛው የድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ውስጥ በተለያየ የኃላፊነት የሚሰሩ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ግለሰቦች ላይ ትግራይ ውስጥ ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር በተያያዘ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ዙሪያ ቅሬታ ሲያቀርብ እንደነበር የሚታወስ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ተቋም ወደ ትግራይ ክልል አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ በሚያደርገው ጥረት እንቅፋት እንደገጠመው በመግለጽ የኢትዮጵያ መንግሥትን ሲወቅስ ቆይቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የሚቀርብበትን ክስ የማይቀበለው ሲሆን ይልቁንም የእርዳታ አቅርቦቱ እንዲቀላጠፍ የነበሩትን የፍተሻ ኬላዎች መቀነሱን በመግለጽ ለችግሩ አማጺያኑን ተጠያቂ ያደርጋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ የትግራይ ክልል ይፋዊ ባልሆነ የሰብአዊ እርዳታ እገዳ ስር ነው ሲል ማክሰኞ ዕለት የተናገሩ ሲሆን፣ ጨምረውም በክልሉ ረሃብ ሳይከሰት እንደማይቀር ስጋታቸውን ገልጸዋል። ግሪፊትስ የኢትዮጵያ መንግሥት የእርዳታ አቅርቦት ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዲገቡ እንዲያደርግ ጠይቀው “ይህ ችግር ሰው ሰራሽ ነው፣ መንግሥት እርምጃ ከወሰደ መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል” ሲሊ ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግረዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ