በምክትል ከንቲባነት ሲያገለግሉ የነበሩት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሆነው ዛሬ መስከረም 18/2014 ዓ.ም አዲስ በተመሰረተው ምክር ቤት ተመረጡ።
ከንቲባዋ በምክር ቤቱ 138 አባላት በሙሉ ድምፅ የተመረጡ ሲሆን ለቀጣዩ አምስት ዓመታትም የከተማዋ ከንቲባ ሆነው ለማገልገል ቃለ መሐላ ፈፅመዋል። ሰኔ 14/2013 ዓ.ም የተካሄደውን ብሔራዊ ምርጫ ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ምክር ቤት ምስረታ ሥነ ሥርዓት ጉባኤ በዛሬው ዕለት ተካሄዷል።
የምስረታው መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ቴአትር እና ባህል አዳራሽ እየተካሄደ ሲሆን በዚህም መሰረት ተመራጮቹ የምክር ቤቱ አባላት ደንቡ በሚያዘው መሰረት ቃለ መሐላቸውን ፈፅመዋል። በዚሁ የአዲስ የከተማው ምክር ቤት ምስረታ ሥነ-ሥርዓት ላይ በቀጣይ አምስት ዓመታት ምክር ቤቱን በአፈጉባኤነት እና በምክትል አፈጉባኤነት እንዲሁም ከተማዋን በከንቲባነት የሚመሩ ግለሰቦች የተመረጡ ሲሆን ሲሆን፤ በአዲስ አባባ አስተዳደር ካቢኔ አባላት በመሆን የሚያገለግሉትንም ሰዎችንም ይመርጣል።
ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤነት የተመረጡት አሸናፊው ፓርቲ ብልጽግና ያቀረባቸው ዕጩ የ47 ዓመቷ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር ሃጂ ዘሊ ናቸው። ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅም ወይዘሮ ቡዜናን ለአፈ ጉባኤ የመረጠ ሲሆን በምክር ቤቱ አፈ ጉባኤነትም ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።
ወይዘሮ ቡዜና የቀድሞዋን አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ዘርፈሽዋልን የተኩ ሲሆን ወደዚህ ኃላፊነታቸው ከመምጣታቸው በፊት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ድኤታ ነበሩ። ወ/ሪት ፋይዛ መሐመድ እንዲሁ በሙሉ ድምፅ የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ሆነው ተሾመዋል።
በዘንድሮው ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ በፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ካሉት 436 መቀመጫዎች ውስጥ 410 ያሸነፈ ሲሆን ለቀጣዩ አምስት ዓመታትም መንግሥት መመስረት የሚያስችለውን ወንበር አግኝቷል። በዘንድሮው ምርጫ ብዙ ትኩረት በነበረባት አዲስ አበባ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 1,819,343 ሲሆን ከዚህም ውስጥ 99ኛው በመቶ ድምፅ ሰጥቷል።
አዲስ አበባ ከተማ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 23 መቀመጫዎች ያሏት ሲሆን ገዢው ፓርቲ ብልጽግና 22 መቀመጫዎችን ሲያሸንፍ በግል የተወዳደሩትና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አንዱን መቀመጫ አግኝተዋል። የከተማዋን ምክር ቤት በምንመለከትበት ወቅት ብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባን ምክር ቤት ሁሉንም 138 መቀመጫዎችን አሸንፏል።
ጥቂት ስለ ወይዘሮ አዳነች
ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ወደ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ የመጡት የገቢዎች ሚኒስትር በመሆን ነበር። ወደ ሚኒስትርነት ቦታ ከመምጣታቸው በፊት የአዳማ ከተማ ከንቲባ እንዲሁም የኦዴፓ ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።
አርሲ ዞን የተወለዱት ወ/ሮ አዳነች የትምህርት ዝግጅታቸው ሲታይ በመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ተምረው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት የነበሩ ሲሆን እያስተማሩም ዲፕሎማቸውን እንዲሁም ዲግሪያቸውን በሕግ ይዘዋል።
በኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ በዐቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም በ1997 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ከተመረጡ በኋላ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል። ለስድስት ዓመታትም ያህል የኦሮሚያ ልማት ማኅበርን መርተዋል። ወ/ሮ አዳነች የአዲስ አበባ ከተማን በምክትል ከንቲባነት ማገልግል ከመጀመራቸው በፊት ለአጭር ጊዜ የፌደራል ዋና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሆነው ሰርተዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ