የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ እርዳታ ጫኝ መኪኖች ወደ ትግራይ አንዲንቀሳቀሱ ጠየቁ።
የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ በትግራይ ረሃብ ጉዳት እያስከተለ ነው ብለው እንደሚያስቡም ለሮይተርስ ተናግረዋል። ኃላፊው ይፋዊ ባልሆነ የሰብዓዊ እርዳታ እቀባ ስር በምትገኘው ትግራይ መድረስ ከሚኖርበት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት 10 በመቶ ብቻ ለተረጂዎች መድረሱንም ለዜና ወኪሉ ገልጸዋል።
ማርቲን ግሪፊትስ ጨምረውም ጥያቄያቸው፤ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ መሆኑን ማክሰኞ እለት ለሮይተርስ ተናግረዋል። “ይህ ሰው ሰራሽ ነው፤ በመንግሥት እርምጃ ሊሻሻል ይችላል” ሲሉ የተመድ የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የእርዳታ አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ አለማድረጉንና ይልቁንም የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ቀልጣፋ እንዲሆን እርምጃ እወሰደ መሆኑን በመግለጽ ለችግሩ አማጺያኑን ተጠያቂ ያደርጋል። ከ10 ወራት በፊት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ግጭት ከተከሰተ በኋላ በሺዎች የሚቀጠሩ በግጭቱ ስለመሞታቸው፤ እንዲሁም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል።
“ረሃብ በሚመስል ሁኔታ ውስጥ 400ሺህ ሰዎች ይገኛሉ ብለን ተንብየን ነበር፤ ግምታችን የነበረው እርዳታ የማይደርሳቸው ከሆነ ለረሃብ ይጋለጣሉ የሚል ነው” በማለት ግሪፊትስ የመንግሥታቱ ድርጅት ሰኔ ወር ላይ የነበረውን ትንበያ አስታውሰዋል። ግሪፊትስ በትግራይ የነዳጅ፣ የጥሬ ገንዝብ፣ የተሸከርካሪዎች እጥረት እና ይፋዊ ያልሆነ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እቀባ መኖሩን በማስታወስ “ይህን የመሰለ ነገር (ረሃብ) ተከስቷ ብዬ መገመት አለብኝ” ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይቀርብ ምንም አይነት እቀባዎችን አለመድረጉን ሲያሳውቅ ቆይቷል። ይልቁንም የእርዳታ ቁሳቁሶች ወደ ክልሉ በፍጥነት እንዲገቡ ለማቀላጠፍ ሰባት የነበሩትን የፍተሻ ጣቢያዎች ወደ ሁለት እንዲቀነሱ ማድረጉን መንግሥት አስታውቆ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት የእርዳቃ ቁሳቁሶችን ጭነው ወደ ትግራይ ክልል ተጉዘው ከክልሉ ሳይወጡ የሚቀሩት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎቹ በክልሉ ውስጥ ለምን አገልግሎት እየዋሉ እንደሆነ ግልጽ ባለመሆኑ ጥርጣሬን ፈጥሮብኛል ሲል ነበር።
የሰላም ሚንስቴር ጳጉሜ 01/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ላይ “በተጨባጭ ከአላማቸው [ተሸከርካሪዎቹ] ውጪ ተሰማርተው ላለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሰጥ አካል አልተገኘም” ብሎ ነበር። የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ተሽከርካሪዎቹ ከትግራይ ክልል እንዳይወጡ ያደረጋቸው የነዳጅ እጥረትና በሹፌሮች ላይ የሚደርስ እንግልት ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ፤ ተሸከርካሪዎች የእርዳታ ቁሳቁሶችን ጭነው ወደ ትግራይ በሚጓዙበት ወቅት ቢያንስ ሁለት ጊዜ ተኩስ ተከፍቶባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ተመድ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የጭነት መኪና አሸከርካሪዎች በአጎራባች አፋር ክልል በቁጥጥር ሥር የዋሉበት አጋጣሚ ስለመኖሩ አመልክቶ ነበር።
የተመጣጠን የምግብ እጥረት
ግሪፊትስ የጭነት መኪኖቹ ወደ ትግራይ ሄደው መቅረታቸው የሰብዓዊ አቅርቦት ሥራው ላይ እክል እንደሆኑ ተናግረዋል። ተሽከርካሪዎቹ እና ሹፌሮቹ “በመጀመሪያ ደረጃ ከትግራይ ለመውጣት የሚያስፈልጋቸው ነዳጅ እና ፍላጎት ላይኖራቸው ይችላል። ምክንያቱም ምንም ይሁን የሰብዓዊ እርዳታ ሥራው ላይ ችግር እየፈጠረ ነው” ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ትናንት ምሽት በትዊተር ገጹ ላይ በቅርብ ቀናት 61 የጭነት መኪኖች ከትግራይ መመለሳቸውን እና በቀጣይ ቀናትም ተጨማሪ መኪኖች ይወጣሉ ብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት በሠሜን ኢትዮጵያ የከተሰውን ግጭት ተከትሎ በትግራይ ብቻ 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ የሰብአዊ እርዳታ ይፈልጋል ይላል። ተመድ ነሐሴ ወር ማብቂያ ላይ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ህጻናት ላይ ምልከታ አድርጎ 22.7 በመቶ የሚሆኑ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው ያረጋገጠ ሲሆን፤ 11ሺህ ነፍሰጡር ወይም ከሚያጠቡ እናቶች መካከል ደግሞ 70 በመቶ ያክሉ ለከፍተኛ የተመጣጠን ምግብ እጥረት ተጋልጠዋል ብሏል።
ማርቲን ግሪፊትስ ይህን የምግብ እጥረት እአአ 2011 ላይ በሶማሊያ ተከስቶ ከነበረው ረሃብ ጋር አነጻጸረዋል። ግሪፊን በየዕለቱ የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ 100 ተሸከርካሪዎች ወደ ትግራይ መግባት ይኖርባቸዋል ያሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የሰብዓዊ እርዳታ የደረሰው 10 በመቶ ለሚሆኑት ብቻ ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ