የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ መስከረም 24/2014 ዓ.ም አዲሱ የፌደራል መንግሥት እንደሚመሰረት ገልጸዋል።

ክልሎችም በበኩላቸው አዳዲስ መስተዳደሮቻቸውን ለማዋቀር እየተዘጋጁ ሲሆን የኦሮሚያ ምክር ቤት ቅዳሜ መስከረም 15/2014 ዓ.ም ባካሄደው ጉባኤ አዲሱን የክልሉን መንግሥት መስርቷል። በተመሳሳይ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መስከረም 19፣ የጋምቤላ፣ የአማራ እና የሲዳማ ክልሎች ደግሞ መስከረም 20 እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 21/2014 ዓ.ም መስተዳደሮቻቸውን ያዋቅራሉ።

ለመሆኑ መስከረም 24/2014 ዓ.ም የሚመሰረተው የፌደራል መንግሥት ቁልፍ አጀንዳዎቹ ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

‘ያልተሰበረው የጦርነት አዙሪት

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር የሆኑት ውሂበእግዜር ፈረደ (ዶ/ር) አዲሱ መንግሥት የሚያስቀምጣቸውን አጀንዳዎች የመፈፀም አቅም የሚያገኘው ከሚመሰርተው መንግሥት ባህርይ ነው ይላሉ። የሚመሰረተው መንግሥት የሚኖረው ባህርይ እና አካታችነቱ ሊሰሩ ይችላሉ ተብለው የሚቀመጡ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የራሱ አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል ሲሉ ያስረዳሉ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው የሚመሰረተው መንግሥት ከዚህ በፊት ከነበረው “ትልቅ ሊባል የሚችል የምጣኔ ሀብት ተግዳሮት ነው ሊገጥመው ይችላል” ሲሉ ሙያዊ ግምገማቸውን ይሰጣሉ። አዲሱ መንግሥት ሲመሰረት ከዚህ በፊት በይደር የተቀመጡ፣ በተለያየ ምክንያት ሳይፈፀሙ ቀርተው ወደ ዛሬ የተንከባለሉ ጉዳዮችን እንደሚረከብ የሚጠቅሱት ውሂበእግዜር (ዶ/ር)፤ ከእነዚህ መካከል ደግሞ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ጥያቄ የሆነው የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዳይ አንዱ መሆኑን ያነሳሉ።

አዲሱ መንግሥት ለዚህ የዘመናት ሕዝብ ጥያቄ ቢያንስ ቁልፍ የሆነ መሠረታዊ ጅማሮ ያሳያል ብለው እንደሚጠብቁ በማንሳትም፣ ለዚህ ደግሞ አካታች የሆነ መንግሥት መመስረት ቀዳሚውና ወሳኙ እርምጃ ነው ይላሉ። አክለውም አሁን ላይ ያጋጠሙ የሰላም መደፍረሶችን ለመፍታትና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት መሥራት እንዳለበት፣ ይህም የአዲሱ መንግሥት ቁልፍ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ ይናገራሉ።

ዘላቂ መፍትሔ ተብሎ የሚቀመጠው ጉዳይ ምንድን ነው? የሚለውን ለመወሰን በወታደራዊ መንገድ ነው ወይስ በብሔራዊ መግባባት ማዕቀፍ ሊታይ ይችላል የሚለውን የሚወስነው የሚመሰረተው አዲሱ መንግሥት ይሆናል። መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ በጠመንጃ አፈሙዝ ከመፍታት ይልቅ በተሻለ መንገድ ማስተናገድ የሚችልበት ጠንካራ ማዕቀፍ ይዞ ይመጣል የሚል ተስፋ ያላቸው ውሂበእግዜር (ደ/ር)፤ እነዚህን ጉዳዮች ለመፍታት የፖለቲካ ሪፎርሙ ሂደት እንዲሁም የብሔራዊ መግባባት ውይይቱ እነማንን ያካትታል የሚለው ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ተቃርኖዎች በሃሳብ የበላይነት፣ በውይይት ይፈታሉ የሚል ተስፋ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ ዳግም የጦርነት አዙሪት ውስጥ መግባቷን ያነሳሉ።

የጦርነት አዙሪትን ለመሰብርና ኢትየጵያውያንን ወደ አንድ የፖለቲካ ስበት ማዕከል ለማምጣት በአገሪቱ የሚካሄደው የለውጥ እርምጃ አካታች ሊሆን ይገባል ሲሉ ሃሳባቸዋውን ይሰነዝራሉ::

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው በዚህ ጦርት በርካታ ቁጥር ያላቸው ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ እንዲሆን የግብርና ምርት ሰንሰለቶች፣ ብዙ የኢንደስትሪ ተቋማት ብዙ ባለሀብቶች እና ትልልቅ የንግድ ተቋማት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መጎዳታቸውን ያነሳሉ።

በሠሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት፣ በምዕራብ እና ደቡብ ያለው አለመረጋጋት ብዙ የምጣኔ ሀብት አውታሮች እና መሰረተ ልማቶች ላይ ውድመትን አድርሷል።

በዚህ በደከመ፣ በተጠቃና በተጎዳ የምጣኔ ሀብት መሠረተ ልማት አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት ምን ያህል የሕዝቡን ፍላጎት ሊያዳርስ ይችላል የሚለው ሲታሰብ ትልቅ ፈተና ሆኖ እንደሚታይ ያስረዳሉ።

የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ውሂበእግዜር ፈረደ (ዶ/ር) በበኩላቸው የተጀመረውን ሪፎርም ተቋማዊ ማድረግ እንደሚገባ አስረግጠው፤ ይህም ከንግግር በዘለለ “ኢትዮጵያ ከየት ተነስታ የት እንደምትደርስ በግልጽ የሪፎርም አጀንዳው መቀመጥ አለበት” በማለት ይመክራሉ።

ከዚህ ጋር አብሮ ተያይዞ ሪፎርሙን ተቋማዊ በማድረግ ሂደት ውስጥ አብሮ ሊታይ የሚገባው፣ “ሕገመንግሥቱን ማሻሻል አልያም አዲስ ሕገመንግሥት ማርቀቅ፤ የፌዴሬሽኑን ቅርጽ እና የወደፊት እጣ ፈንታ፣ የአገሪቱን የአስተዳደራዊ መዋቅር ቅርጽ እንዴት መሆን አለበት” የሚለው ሊሆን እንደሚችል ይጠቅሳሉ።

ከእነዚህ ጉዳዮች በላይ ግን የብሔራዊ ውይይት (ናሽናል ዲያሎግ) እንደሚቀድም ያነሳሉ።

በርካታ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ ይህንን ጉዳይ አጀንዳ አድርገው ሲወተውቱ እንደነበር ያስታወሱት ውሂበእግዜር (ዶ/ር)፣ መንግሥት በአዲሱ ዓመት ከሚመሰረተው መንግሥት ብሔራዊ መግባባትን ያመጣሉ ብሎ ያሰባቸውን ውይይቶች እንደሚጀምር ሲያነሳ መደመጡን ሳይጠቅሱ አላለፉም።

ቀጠናዊ ለውጦች እና አዲሱ መንግሥት

የአዲሱ መንግሥት ቁልፍ አጀንዳዎች ሲነሱ የሚታዩ ቀጠናዊ ለውጦች መኖራቸውን ያነሳሉ። ከሱዳን ጋር ያለን ግንኙነት ወደ አዲስ ትብብር የማሳደግ እና በሱዳን ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ እንድ በጎ እድል የመጠቀም እንቅስቃሴ ይኖራል ሲሉ ተስፋቸውን ውሂበእግዜር (ዶ/ር) በይናገራሉ።

ሱዳን ኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ስትራቴጂካዊ ማድረግ ይቻላል የሚሉት ዶክተሩ ፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከሱዳን ጋር የነበራትን የሁለትዮሽ አጋርነት ዳግም የማስቀጠል ሥራ መሰራት እንደሚኖርበት አንስተዋል።

በሱዳን ውስጥ የሚካሄደውን የለውጥ እንቅስቃሴዎች በበጎ መልኩ በመጠቀም ወደ ቀድሞው መልካም ግንኙትን መመለስ እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በሱዳን ጥቅም ላይ ይህ ነው የሚባል ጉዳት እንደማያደርስ ምሁራኖቻቸውም ሆኑ ፖለቲከኞቻቸውም ያውቁታል ያሉት ውሂበእግዜር (ዶ/ር)፣ የድንበር ውዝግቡም ቢሆን ለመፍታት “በጣም ቀላል ይመስለኛል” ሲሉ ተስፋቸውን ይናገራሉ።

ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ሲያስረዱም “ድንበሩን በጋራ የማልማት ስትራቴጂ መከተል አንዱ መንገድ” መሆኑን ያነሳሉ።

ዋናው ከሱዳን ጋር የነበረው የድንበር ውዝግብ ችግር ውስጥ እንዲወድቅ ያደረገው በኢትዮጵያ በኩል የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ድክመት መሆኑን ምሁሩ አንስተዋል።

በኤርትራ በኩል የተጀመረው አዲስ የወንድማማችነት ሕብረት በውስጡ ይዞት የሚመጣው እድል በዘላቂነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ያድጋል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም አክለው ተናግረዋል።

“በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የሚያሳድጉ ሥራዎች ይሰራሉ ብዬ እጠብቃለሁ።”

ኬንያ፣ አዲሲቱ የምሥራቅ አፍሪካ ኃይል አንቀሳቃሽ ሆና ለመውጣት እየተንቀሳቀሰች መሆኑን በማንሳትም ስትራቴጂካዊ ትብብርን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

በቀጣይ ዓመታት “ኢትዮጵያ ከቀጠናው አገራት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት ከታክቲካል ወደ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የማሳደግ ሂደት ውስጥ የምትገባ ይመስለኛል።”

ከአገሮች ጋር ከምታደርገው ግንኙነት በተጨማሪ አዳዲስ ተቋማትን የመመስረት፣ የመገንባት፣ ኢጋድን ከማጠናከር በተጨማሪ፤ የቀይ ባሕር ጉዳይን የሚመለከት አዲስ ተቋም የመገንባት፣ በአባይ ሸለቆ ላይ ደግሞ ከዚህ በፊት ከነበረው የ’ናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ’ በመውጣት የላይኛው ተፋሰስ አገራት ጥምረትን በተመለከተ አዲስ ተቋም የምታዋቅርበት ሊኖር እንደሚችል ያስረዳሉ።

ዓለም አቀፉ ግንኙነት እና አዲሱ መንግሥት

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) አሜሪካ እና አውሮፓ ከዚህ በፊት በቃል ሲዝቱበት የነበረውን የምጣኔ ሀብት ማዕቀብ አሁን በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ፈርማ ወደ ተግባር እየገቡበት መሆኑን ያነሳሉ።

“በተለይ ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ጋር ተጋጨን ማለት ኢትዮጵያን ከሰማይ ወደ ምድር እንደመወርወር ነው” የሚሉት ምሁሩ፣ አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት እስከ ዛሬ ከነበሩት መንግሥታት በተለየ ትልቅ ተግዳሮቶችና ፈተናዎች ስለሚገጥሙት “ወገቡን አስሮ መጠነ ሰፊ ርብርብ ማድረግ” እንደሚጠበቅበት ይመክራሉ።

ኢትዮጵያ የበጀት ድጋፍ በቀዳሚነት ከአሜሪካ፣ በመቀጠል ከእንግሊዝ፣ በሦስተኝነት ደግሞ ከተለያዩ የአውሮፓ አገራት እንደምታገኝ ዶ/ር ጉቱ ያነሳሉ።

“እነዚህ ሁሉ ጀርባቸውን የሚሰጡን ከሆነ፣ አሁን የጀመሩትን ማዕቀብ የሚያስቀጥከትሉ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ውስጥ ሁሉ ልትገባ ትችላለች” ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

የፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩም በበኩላቸው የኃያላን አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚፈጥሩት ተጽዕኖ፣ በተለይ በአሜሪካና ኢትዮጵያ ግንኙት ላይ ዲፕሎማሲውን ማጠናከር እንደሚያስፍልግ ያስረዳሉ።

የአውሮፓ እና የአሜሪካ መንግሥታት በትግራይ ጦርነት ምክንያት እያሳደሩ ያለውን ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ለመቋቋም የአዲሱ መንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ይሆናልም ይላሉ።

አዲስ የውጭ ግንኙነት መርህ እና እንቅስቃሴ ከእነማን ጋር ቢሆን የተሻለ ዘላቂ እና ስትራቴጂክ የሆነ ጥቅም ይኖረናል የሚለው ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

“ይህንን በሚመለከት ከቀዝቃዛው ጦርነት ኢትዮጵያ ትምህርት የምትወስድ ይመስለኛል” የሚሉት ውሂበእግዜር (ዶ/ር)፣ በአሜሪካ በኩል ያለውንም ግንኙነት “ተበላሽቷል፤ የማይታከም ነው፤ የሚል ድምዳሜ ላይ ይደርሳል ብዬ አላስብም” ብለዋል።

“የተጠና ዲፕሎማሲ በመጠቀም ከምዕራብም ከምሥራቅም ኃይል የማሰባሰብ ትኩረት የሚሰጠው ይመስለኛል” በማለት አሁን ያለው የዓለም አሰላለፍን በጥልቀት የመገንዘብና የመተንተን ሥራ እንደሚሰራም ያላቸውን ግምት ተናግረዋል።

“ከምዕራባውያን ጋር ስንጋጭ ከውጭ ባለሃብቶች ጋር ነው የምንጋጨው። እዚህ ያለው ጠቅልሎ ይሄዳል። ሌላውም አይመጣም” ያሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) ቀዳሚው ነገር ከአሜሪካ ጋር መስማማት፣ መደራደር ነው ሊሆን እነደሚገባ ያሰምሩበታል።

“የሚቻል ከሆነ በዲፕሎማሲ ጥበብ ለማሸነፍ መሞከር ነው።”

“. . .አገር ውስጥም ይሁን በውጭ አገራት የሚገኙ ዲፕሎማቶች ከየትኛውም ጊዜ ይልጥ ሽንጣቸውን ገትረው ትልቅ የዲፕሎማሲ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ መስራት የሚጠበቅባቸው ጊዜ ነው” ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

እንደ ጉቱ (ዶ/ር) አዲሱ መንግሥት ቢያንስ ቢያንስ ማዕቀቦቹ ተግባራዊ እንዳይሆኑ ለኢትዮጵያ የእፎይታ ጊዜ በሚሰጥ ሁኔታ ላይ ሊሰራ ይገባል።

ጦርነት እና አለመረጋጋት እያለ የትኛውም የምጣኔ ሀብት እርምጃ መፍትሄ አያመጣም የሚሉት ጉቱ፣ “መጠነ ሰፊ የሆነ የኢኮኖሚ መረጋጋት ለማምጣት በአገሪቱ ውስጥ ያለው ጦርነት እና አለመረጋጋት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቆም አለበት” ይላሉ።

በማጠቃላያቸውም ላይ “የሆኖ ሆኖ አሁን ከገባንበት ቀውስ ወጥተን ዘላቂ እና ፈጣን እድገት ወደ ምናስመዘግብበት ጎዳና ላይ ለመሰለፍ ከአምስት እስከ አስር ዓመት ይወስድብናል” ሲሉ ተናግረዋል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *