የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአገራቸው የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረጉ ሙከራዎችን ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ተናገሩ።
በኒው ዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው በ76ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥታቸው የሰብአዊ እርዳታን በተመለከተ ያልተቆጠበ ቁርጠኝነት እንዳለው አመልክተው አገራቸው የትኛውንም ጣልቃ ገብነት አትቀበልም ብለዋል።
ለነጻ፣ ለገለልተኝነትና ለሰብአዊነት ምርሆች ተገዢ ለሆኑ የእርዳታ አቅርቢ አጋሮች ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ መንግሥታቸው አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ የገለጹት አቶ ደመቀ፤ “ከዚህ ውጪ ግን የትኛውም ምክንያት በውስጥ ጉዳያችን ውስጥ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግ ሙከራን ተቀባይ አያደርገውም” ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን በመግሥታቱ ድርጅት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር በተለያዩ ኢትዮጵያ በሚመለከቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የመንግሥታቸውን አቋም አብራርተዋል።
የሰብኢዊ እርዳታ አቅርቦት
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሠሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ስላለው ጦርነት ዝርዝር ያስረዱ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተደጋጋሚ የሚነሳውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ በንግግራቸው አንስተዋል።
መንግሥታቸው የሚያስፈልገውን የሰብአዊ እርዳታ ለማሟላት ጥረት እያደረገ ባለበት ጊዜ “የጥፋት ቡድኑ ሰብዓዊ ቀውስ የመፍጠር እቅዱን ተግባራዊ ከማድረጉ ባሻገር ክፋት የተሞላበት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተከፍቶብናል” ሲሉ ከሰዋል።
ጨምረውም “አሁን በደረስንበት ምዕራፍ የሰብአዊ ድጋፍ የፖለቲካ ዓላማን ማስፈፀሚያ መሳሪያ እንደሆነ እየተገነዘብን ነው” ያሉት አቶ ደመቀ፤ የሐሰት መረጃን በማቀነባበር የተዛባ ግንዛቤ እንዲፈጠርና ሐሰተኛ ውንጀላ መቅረባቸውን ተናግረዋል።
ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦት ግዴታውን መወጣቱ፣ የተናጠል ሰብአዊ የተኩስ አቁም ማወጁ እንዲሁም ጥሰቶችን በተመለከተ ምርመራ እንዲደረግና ተጠያቂነት ለማስፈን እርምጃዎችን መውሰዱን ጠቅሰው “ቢሆንም ግን የሐሰት ውንጀላዎቹን መቀልበስ አልተቻለም” ብለዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋማትና ሌሎች መንግሥታት የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ እንዳይቀርብ እንቅፋት ሆኗል በማለት በተደጋጋሚ ሲከሱ ቆይተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በመንግሥታቱ ድርጅት ጉባኤ ላይ ይህን በተመለከተ ምላሽ ሰጥዋል።
የውጭ ጫና
ኢትዮጵያ ማዕቀቦች በሌሎች ላይ ሲጣሉ መቃወሟን አቶ ደመቀ አስታውሰው “በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ፍትህና ፍትሕ የሚጎድለው አካሄድ ተግባራዊ እንዳይሆን እንመክራለን” ብለዋል።
ጨምረውም “ምንም አይነት አላስፈላጊ ጫናዎች ቢኖሩብንም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነትና የፖለቲካ ነፃነትን የማስጠበቅ ግዴታችንን እንወጣለን” ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራቸው ከወዳጆቿ የሚቀርቡ ትብብር እና ቅን ሐሳብን እንደምትቀበል በመጥቀስ ነገር ግን ገንቢ፣ መተማመንን የሚያሰፍንና መግባባትን የሚፈጥር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
“በአንድ መንግሥት ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ድጋፍን ወይም ሐሳብ ለመሰንዘር የሚደረግ ሙከራ ስለችግሩ ውስብስብነት ሙሉ ግንዛቤን ይጠይቃል” ሲሉ አሳስበዋል።
በትግራይ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ምዕራባውያን አገራት በተለይ አሜሪካ በጦርነቱ ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ ወገኖች ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ለማሳደር እየሞከሩ መሆኑ ይታወቃል።
በቅርቡም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከግጭቱ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ዕቀባዎችን ለመጣል የሚያስችል ትዕዛዝ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸው ይታወሳል።
ችግሮችን በውይይት ስለመፍታት
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ ከተለያዩ ወገኖች የሚሰነዘሩ የውይይት ሐሳቦችን በተመለከተ በንግግራቸው ላይ እንዳነሱት፤ ሁልጊዜም ውይይት የመንግሥታቸው ተመራጭ መፍትሔ እንደሆነ ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያ ለሐቀኛ የሰላም ጥረቶች በሯ ክፍት ነው” በማለት ከአፍሪካ ሕብረትና ከሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ጋር ኢትዮጵያ መር ለሆነ ብሔራዊ ውይይት ለማካሄድ መንግሥታቸው እንደሚሰራ አመልክተዋል።
ጨምረውም ኢትዮጵያ ለማንም የደኅንነት ስጋት ሆና እንደማታወቅተ በመጥቀስ “ኢትዮጵያ ሁሌም ሰላም ወዳድ አገር ሆና የምትኖርና ለቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ሰላም የበኩሏን አስተዋፅኦ ታበረክታለች” ብለዋል።
ከሱዳን ጋር ስላለው ድንበር ጉዳይ
በሠሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የሱዳን ጦር በኢትዮጵያውያን እጅ የነበረና ይገባኛል የሚለውን የድንበር አካባቢን መቆጣጡ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ተበላሽቶ ቆይቷል። ኢትዮጵያ ሱዳን ከተቆጣጠረችው አካባቢ ሠራዊቷን አስወጥታ ውይይት እንዲጀመር ብትጠይቅም ከሱዳን በኩል ተቀባይነት አላገኘችም።
አቶ ደመቀ መኮንንም ይህንን ጉዳይ በመንግሥታቱ ድርጅት ስብሰባ ላይ አንስተው የአገሪቱ ግዛት በወረራ ስር መሆኑንና አሁንም ለሰላማዊ መፍትሔ በሯ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በነበረችበት ወቅት ጎረቤት አገር ዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ ግዛታችንን የወረረ ሲሆን ይህ ወረራ እስከዛሬ ድረስ ቀጥሏል። ኢትዮጵያ ይህንን ችግር ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ የመፍትሔ ሐሳቦችን ለመቀበል ዝግጁ ናት።” ብለዋል።
የሕዳሴው ግድብ
በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል ለዓመታት ያለመግባባት መንጭ ሆኖ የቆየው የታላቁ ሕዳሴን ግድብ በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ ግድቡን ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት የገነባችው መሆኑ ሌሎችም አገራት በራስ አቅም ለሚገነባ ለሚከናወኑ ተመሳሳይ ተግባራት ይፈጥራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ የገጠማትን ፈተና በተመለከተ አቶ ደመቀ መኮንን ለምክር ቤቱ ባስረዱበት ጊዜ እንዳሉት “የሚያሳዝነው ነገር ከራሳችን ውሃ እንዳንጠጣ መከልከላችን ነው” ብለዋል።
አክለውም አገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም ያለውን የትውልዶች ፍላጎት “በቅኝ ገዢዎች ውርስና በብቸኝነት ለመጠቀም ያለ ፍላጎት ምክንያት የሚገደብ አይሆንም” በማለት ጉዳዩ ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግና በአፍሪካ ሕብረት በሚመራ ሂደት ከመቋጫ ለማድረስ ዝግጁ ይሆናሉ ብላ አገራቸው ተስፋ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ