የሱዳን መንግሥት የኢትዮጵያ ወታደሮች በአወዛጋቢው አዋሳኝ የድንበር አካባቢ ጥቃት ሰነዘሩብኝ ሲል ከሰሰ።

ከሱዳን ጦር የወጣው መግለጫ፤ ከኢትዮጵያ በኩል የተሰነዘረውን “ጥቃት መመከት” መቻሉን አመልክቷል። የኢትጵያ መንግሥት ከሱዳን በኩል ለቀረበበት ክስ አስካሁን በይፋ የሰጠው ምላሽ የለም።የሱዳን ጦር ተሰነዘረብኝ ስላለው ጥቃት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳብራራው ክስተቱ ያጋጠመው ኡማ ናራኪት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው ብሏል።

የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበርና ጦር አዛዥ ጄነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሐን ከኢትዮጵያ በኩል ጥቃት የተሰነዘረብን ቅዳሜ ዕለት ነበር ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።ጄነራሉ በቅርቡ ሱዳን ውስጥ ተሞክሮ ከሸፈ የተበላውን መፈንቅለ መንግሥት በማስታወስ፤ ክሰተቱ ጦሩ ሱዳንን እየጠበቀ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ እስካሁን በይፋ ያለው ነገር ባይኖርም፤ አል-ጀዚራ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን በመጥቀስ እንደዘገበው በሱዳን ደንበር አካባቢ የኢትዮጵያ ጦር ምንም አይነት እንቅስቃሴ አላደረገም፤ የተባለው ጥቃትም አልተፈጸምም።

በተመሳሳይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር መንግሥታቸው በሁለቱ አገራት መካከል በድንበር ይገባኛል ምክንያት የተከሰተውን አለመግባባት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ደመቀ በመንግሥታቱ ድርጅት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ግዛት በወረራ ስር መሆኑንና አሁንም ኢትዮጵያ ለሰላማዊ መፍትሔ በሯ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በነበረችበት ወቅት ጎረቤት አገር ዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ ግዛታችንን የወረረ ሲሆን ይህ ወረራ እስከዛሬ ድረስ ቀጥሏል። ኢትዮጵያ ይህንን ችግር ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ የመፍትሔ ሐሳቦችን ለመቀበል ዝግጁ ናት” ብለዋል።

የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነት መሻከር

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ይገባኛል በሚሉት የድንበር ቦታ እና በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት በመካከላቸው ያለው ውጥረት እየተባባሰ መጥቷል።ኢትዮጵያ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ በአልፈሽጋ የነበራትን ጦር ካንቀሳቀሰች በኋላ ሱዳን የድንበር ቦታውን ተቆጣጥራ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ አጋጣሚዎች ሱዳን የያዘችውን መሬት ለቅቃ እንድትወጣ ሲጠይቅ ቢቆይም የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግን መሬቱ የሱዳን እንደሆነ በመግለጽ ለቀው እንደማይወጡ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።ይልቁንም ሱዳን ሁለቱ አገራት ይገባኛል በሚሉት አካባቢ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን እየገነባች ትገኛለች።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *