በትግራይ ጦርነትና ረሃብ እንዲቆም እርምጃ መወሰድ አለበት በሚል 31 ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝና ለድርጅቱ የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት ተወካዮች ደብዳቤ አስገብተዋል።
ድርጅቶቹ በሠሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት እንዲቆምና በረሃብ አፋፍ ላይ የሚገኙ ሚሊዮኖችን እርዳታ እንዳይደርስ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ ጠይቀዋል። ደብዳቤው ግሎባል ሴንተር ፎር ዘ ሪስፖንሲቢሊቲ ቱ ፕሮቴክት በሚል ድረ-ገፅ የወጣ ሲሆን ከድርጅቶቹም መካከል አክሰስ ቡክስ፣ አሊያንስ ፎር ፒስ ቢዩልዲንግ፣ አሶሺየሽን ኦፍ ኮንሰርድ አፍሪካ ስኮላርስ፣ ሲቪል ሶሳይቲ አክሽን ኮሚቴ፣ ኤጁኬተርስ ኢንስቲትዩት ፎር ሂውማን ራይትስ፣ ኢትዮፕያን ኮሚዩኒቲ ዴቨሎፕመንት ካውንስል ይገኙበታል።
ዋና ፀሐፊው በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤትን ጨምሮ በአፍሪካ ሕብረትና በሌሎች መድረኮች ላይ የትግራይ ቀውስ ላይ ትኩረት እንዲሰጡትና የግጭቱ ተሳታፊ አካላትንም በማሳተፍ በአስከፊነቱ ከ1977 በኋላ የታየውን እየጨመረ ያለውን ረሃብ መከላከል እንዲቻል መደረግ አለበት ብለዋል። የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት፣ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እና የአፍሪካ ሕብረት ይህንን እያደገ የመጣውን የዓለም አቀፍ ሰላምና ደኅንነት ስጋት ዋነኛ አጀንዳዎች ላይ ማስቀመጥ እንዳለባቸው አስምሯል።
ጦርነቱ ወሲባዊ ጥቃትንና ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ የተጠቀመ እንዲሁም ሌሎች መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያስተናገደ ነው በሚል ጠቅሷል። ይህም ሁኔታ የአሜሪካ መንግሥት የጦር ወንጀሎች፣ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች እና የዘር ማጥፋት ተከስቶ እንደሆነ ምርመራ እንዲጀምር አስገድዶታል ብሏል። ይህም ምርመራ እየተካሄደ ካለው የተባበሩት መንግሥታትና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ምርመራ ጋር በትይዩ እየተካሄደ ነው።
ጦርነቱ በሌሎች አካባቢዎች መዛመቱን ተከትሎም በሩዋንዳ፣ በብሩንዲና እና በዳርፉን እንደታየው ብሔርን የሚያዋርዱና በጥላቻ የተሞሉ ትርክቶችን የሚያስታውሱ ሁኔታዎችን በመጥቀስ የአገሪቱን ማኅበራዊ መዋቅር ለመበታተን አደጋን ደቅነዋል ሲልም ደብዳቤው አስጠንቅቋል። ከዚህም በተጨማሪ በዋነኝነት በትግራይ ክልል የተቋረጠው የመሰረተ ልማትና መገናኛ ዘዴዎች እንዲቀጠሉና እግዱ እንዲያበቃ ጠይቋል። የኢትዮጵያ ወታደሮች ከክልሉ መውጣታቸውን ተከትሎ ባንኮች በመዘጋታቸው ነዋሪዎች ምግብ ለመግዛት ገንዘብ እንዳያገኙ እክል ሆኖባቸዋል፤ ንግድ የለም፣ ነዳጅና ኤሌክትሪክ አለመኖር ፈታኝ አድርጎታ ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ዋነኛ የመንገድ መስመሮች በመዘጋታቸው አማራጩ የአፋር መንገድ እንዲሆን አስገድዶታል። ነገር ግን አሁንም የሚገቡት የጭነት መኪኖች እርዳታ የተባበሩት መንግሥታት ረሃቡን ለመታደግ ያስፈልጋል ካለው 6 በመቶ ብቻ ነው። ነሐሴ ላይ ፋሚን ኧርሊ ዋርኒንግ ሲስተምስ ኔትወርክ ባወጣው መረጃ መሰረት 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ አስከፊ የሆነ የምግብ እጥረት ማጋጠሙን ጠቅሶ ይህም አሃዝ በሽታና እና ከፍተኛ የሞት መጠን የሚያስከትል ረሃብ እያጋጠማቸው ያሉ ነዋሪዎችን ያጠቃልላል።
ጦርነቱ ወደ አጎራባቾቹ አማራ እና አፋር ክልል መዛመቱን ተከትሎ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ አፈናቅሏል እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እና ኑሮ አደጋ ላይ ጥሏል። ደብዳቤው ሕዝቡን ለመርዳት እንዲሁም አገሪቱን ለመታደግ ሊወሰዱ የሚገቡ አራት እርምጃዎችን አስቀምጧል።
ሰብዓዊ የተኩስ አቁም እንዲቀመጥና ሁሉም ኃይሎች ከትግራይ እና ከአካባቢው እንዲወጡ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታውን እገዳ እንዲያነሳ እና በእርዳታ ጥረቱ ላይ የሚደረገውን የቢሮክራሲ እንቅፋቶች እንዲያስወግድ ተጠይቋል። በጦር ወንጀሎች እና በሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊ ሕጎች ጥሰቶች ላይ ዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች እና ገለልተኛ መርማሪዎች እንዲሰማሩ ጫና እንዲያደርጉና እንደ ህወሓት ያሉ ተቃዋሚ ቡድኖችን ያካተተ ብሔራዊ ውይይት እንዲያበረታቱ ጠይቋል።
ምንጭ – ቢቢሲ