የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከወራት በፊት እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራውን እና መንግሥት ሸኔ የሚለውን ቡድን “አሸባሪ” ሲል መፈረጁ ይታወሳል።

ምክር ቤቱ ቡድኑ በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች ውስጥ የመንግሥት ባለሥልጣናትን እና ጸጥታ ኃይሎችን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን ዜጎችን ገድሏል፣ ንብረት ዘርፏል እና ሰዎችን ከቀዬቸው አፈናቅሏል በሚል ነበር ‘ሸኔ’ ከህወሓት ጋር አሸባሪ ቡድን ተብሎ የፈረጀው። መንግሥት ሸኔ እያለ የሚጠራው ቡድን በተለይ በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በርካታ ንጹሃን ሰዎችን ስለመግደሉ በድርጊቱ ተጎጂዎች ጭምር ይከሰሳል።

በአገሪቱ ሕግ መሠረት ማንኛውም ሰው የፖለቲካ ፍላጎትን ለማራመድ፤ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ከአስር ዓመት ባላነሰ ከባድ ጽኑ እስራት ይቀጣል። ይሁን እንጂ በቅርቡ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ደቡብ እዝ አዛዥ የነበረው ጎሊቻ ዴንጌ የትጥቅ ትግሉን አቁሞ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ በመንግሥት ባለስልጣናት አቀባበል ተደርጎለታል። ከዚህ በተጨማሪም የጎሊቻ ዴንጌን ወደ አገር መመለስ ተከትሎ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ ጌታቸው ባልቻ በክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ከሁለት ቀናት በፊት፤ “… የኦሮሞ ሕዝብ እርቅ የሚፈልግ ሕዝብ ነው። ወደ ሰላማዊ ትግል እንድትመለሱ ዛሬም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን” ብለዋል። ይህን ተከትሎም አሸባሪ ድርጅት ተብለው የተፈረጁት እና አንግበውት የነበረውን ነፍጥ አውርደው ወደ አገር የሚገቡ የኦሮሞ ነጻነት ጦር አባላት ጉዳይ ጥያቄን ፈጥሯል።

አሻባሪ ተብሎ የተፈረጀ እና በበርካታ ወንጀሎች ተጠያቂ የሚደረግ ቡድን አባላት ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ አገር ውስጥ ሲመለሱ፤ ከሕግ ተጠያቂነት እንዲያመልጡ አያደርግም ወይ ተብለው የተጠየቁት ጌታቸው ባልቻ፤ “ተጸጽተው ከመጡ እንደ ግለሰብ በሰላም እናስተናግዳቸዋለን” ይላሉ። “ኦሮሞ ባህል አለው። አውሬ ቤት ውስጥ ቢገባ እንኳ አይገድልም። መፍትሄ የሚሰጥበት መንገድ አለው። ጥሪ ተደርጎላቸው ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ያሉ አሉ። ትናንት በተከሰሱበት ወንጀል የጠየቃቸው የለም” ካሉ በኋላ፤ “የተጎዳ ቤተሰብ አለ። ያለፈው አልፏል። ወደፊት ኦሮሞ ኦሮሞን መግደል የለበትም ብሎ መወሰን ጀግንነት ነው” ይላሉ ጌታቸው።

ቃል አቀባዩ ሰላማዊ መንገድን መርጦ የሚመጣ ሰላማዊ ሕይወትን መምራት ይችላል ይላሉ። “መንሥት በእርቅ ወደፊት አብረን መሄደ እንችላለን ብሎ ነው የሚያምነው። ይህ ቡድን የሚፈጽመው ተግባር በአሸባሪነት አስፈርጆታል። ቡድኑ ነው በአሸባሪነት የተፈረጀው። ይህን ተግባር ተቃውሞ የሚወጣ ግለሰብ ግን አይጠየቅም” ይላሉ። የኦሮሞ ነጻነት ጦር የደቡብ ዞን አዛዥ የነበረው ጎሊቻ ዴንጌም እንደ ግለሰብ ቡድኑን ተቃውሞ ወደ አገር በመግባቱ በሕግ ተጠያቂ አይሆንም ብለዋል።

ጎሊቻ ዴንጌ ከመንግሥት ጋር እንዴት ተስማማ?

ጎሊቻ ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የትጥቅ ትግል ሲያደርግ ከቆየበት ቡድን እራሱን አግልሎ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለመግባት የወሰነው በሁለት ምክንያቶች መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል። ይህም በድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት እና በቅርቡ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ከህወሓት ጋር አብሮ ለመስራት መስማማቱ ድርጅቱን ጥሎ እንዲወጣ ምክንያት እንደሆኑት ይናገራል።

ጎሊቻ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ከህወሓት ጋር አብሮ ለመስራት መስማማቱ ትክክል አይደለም ማለቱ እንዲሁም “እየተካሄደ ያለው ትግል እና አመራር ትክክል አይደለም” በማለቱ ከቡድኑ ጫና ይደርስበት እንደነበረ ይናገራል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቃል አቀባይ ጌታቸው ባልቻ በበኩላቸው ጎሊቻ ወደ አገር ለመግባት የወሰነው በሦስት ምክንያቶች እንደሆነ ነግሮናል ይላሉ። የመጀመሪያ ምክንያቱ፤ ኦሮሞ የሚፈልገወን የፖለቲካ ስልጣን ስላገኘ በሰላም ለመታገል ፍልጋለሁ ብሎ ወደ አገር ተመልሷል ይላሉ።

“ሁለተኛው ምክንያት ቡድኑ ከህወሓት ጋር ስምምነት መፈጥሩ ነው” የሚሉት ጌታቸው፤ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን ከህወሓት ጋር አብሮ ለመስራት መስማማቱ ውርደት ነው ብሎ ጥሎ ስለመውጣቱ ጎሊቻ ነግሮናል ይላሉ።

ሦስተኛ ምክንያት ደግሞ “በጫካ ሆኖ ነጻነትን ማሰብ ጊዜ የሻረው አካሄደ ነው ብሎ በማሰቡ ወደ አገር ቤት ተመልሷል” ሲሉ ጌታቸው ያስረዳሉ። የኦሮሞ ነጻነት ጦር በበኩሉ የጎሊቻ ዴንጌን መመለስ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ ጎሊቻ ወደ አገር እንዲመለስ የኢትዮጵያ መንግሥት አስተዋጽኦ እንዳለበት እና “መንግሥት ጎሊቻ ይኖር ወደነበረበት ናይሮቢ ሰዎችን ልኮ ከጎሊቻ ጋር ንግግር ስለማድረጉ አውቃለሁ” ብሏል።