የኢትዮጵያ ልዑካንን ጨምሮ ከመላው ዓለም የተውጣጡ መሪዎች በተገኙበት 76ኛው የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፤ በተለያዩ አገራት ያሉ ግጭቶች ጉዳይ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም ሌሎችም ወቅታዊ እና አንገብጋቢ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተዋል።

በጉባኤው ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት የተነሱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲተባበር ጠይቀዋል። በአሜሪካ፣ ኒው ዮርክ እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ባይደን “እንደ ኢትዮጵያ እና የመን ባሉ አገራት የተነሱ ግጭቶችን ከመፍታት ወደኋላ ማለት የለብንም” ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ጦርነት ውስጥ የገቡ ወገኖች ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡ ለማድረግ በሚደረግ ጥረት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተስፋ እንዳይቆርጥ ጠይቀዋል።

“በጦርነት ሳቢያ ረሃብ እየተነሳ ነው። እጅግ አሰቃቂ ጥቃት እየተፈጸመ ነው። የንጹሀን ሰብአዊ መብት እየተገፈፈ ነው። መድፈር እንደ ጦር መሣሪያ እየዋለ ነው” ሲሉ በጉባኤው ንግግር አድርገዋል። መንግሥታቸው ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን አሁን እየተስተዋለ ያለውን ሰቆቃ ለመግታት ብሎም ሰላም ለማምጣት እንደሚሠራም ቃል ገብተዋል። ወደ ዓመት እየተጠጋ ባለው የሰሜን የአገሪቱ ክፍል ጦርነት ብዙ ሺዎች ሲሞቱ፤ በርካቶች የረሃብ አፋፍ ላይ ይገኛሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመፈናቀላቸው ባሻገር የመሠረተ ልማት ውድመትም ደርሷል። አሜሪካ በጦርነቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ወደ ድርድር የማይመጡ ከሆነ ማዕቀብ እንደምትጥል አስጠንቅቃለች።

ኢትዮጵያ በጠቅላላ ጉባኤው

ኒው ዮርክ የሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ጉዳይ ከተለያዩ አገራት ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ደመቀ መኮንን ካነጋገሯቸው ባለሥልጣናት መካከል የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼህ አሕመድ ቢን አሕመድ አሊ እና የቬንዙዌላ የውጭ ግንኙነት ሚኒስትር ፌሊክስ ራሞን ፕላስሴሲያ ጎንዛሌዝ ይጠቀሳሉ። በቅርቡ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቀጣይ አባል የሆነችው ጋቦን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓኮሜ ሞቤሌት ቡቤያም ከውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ጋር ተወያይተዋል።

ከምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃን ጠቅሰው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያለው ትኩረት እየጨመረ ከመምጣቱ አንጻር “ጋቦን የአፍሪካውያን ድምጽ እንድትሆን” አቶ ደመቀ እና የጋቦኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ተነጋግረዋል። አቶ ደመቀ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ኃላፊ ዴቪድ ባስሌይ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ስላለው የሰብአዊ ድጋፍ በመንግሥት ላይ “ሚዛናቸውን ያልጠበቁ እና ትክክለኛ ያልሆኑ ክሶች ተደጋግመው ይሰማሉ” ብለዋል። አያይዘውም በሰብአዊ እርዳታ ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጋር መንግሥታቸው በትብብር እንደሚሠራ መናገራቸው ተዘግቧል።

የአየር ንብረት ለውጥ

የመላው ዓለም ራስ ምታት የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ነው። የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝን ጨምሮ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ የአውሮፓ ሕብረት አገራትና ሌሎችም በውይይቱ ተገኝተዋል። የዩኬው ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን የዓለም ኃያላን አገራት በየዓመቱ ለአየር ንብረት ለውጥ 100 ቢሊዮን ዶላር ለመመደብ የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ አሳስበዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን፤ አሜሪካ ለአየር ንብረት የምትመድበውን ገንዘብ በእጥፍ እንደምታሳድግ እና እአአ እስከ 2024 ለታዳጊ አገሮች የምትሰጠውን ድጎማ ወደ 11.4 ቢሊዮን ዶላር እንደምታሳድግ ተናግረዋል። የተመድ ዋና ጸሐፊ ጉቴሬዝ በምጣኔ ሀብት የበለጸጉ አገራት አቅመ ደካማ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን እንዲታገሉ በሚል የሚሰጡት ድጎማ “ተስፋ ሰጪ ነው” ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። ያደጉ አገራት የካርበን ልቀትን ለመቀነስ እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ የመደቡትን በጀት በሟሟላት ረገድ ገና ብዙ እንደሚጠበቅባቸው በጉባኤው ተመልክቷል።

ኮሮናቫይረስ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጉዳይ በመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ መወያያ ከነበሩ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባይደን፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ወረርሽኙን ለማሸነፍ የዲፕሎማሲ ትብብር እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል። በመላው ዓለም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የቀጠፈውን ቫይረስ ማሸነፍ የሚቻለው ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ እንደሆነ በጉባኤው ተጠቁሟል። በተለይም ያደጉ አገራት ያከማቹትን ክትባት በከፍተኛ መጠን ለታዳጊ አገሮች እንዲለግሱ በተደጋጋሚ ጫና ሲደረግባቸው እንደነበር አይዘነጋም።