ግንቦት 10/2013 ዓ.ም በግልገል በለስ ከተማ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሐሰን እና በጉሙዝ ታጣቂ ቡድን ተወካይ አቶ ጀግናማው ማንግዋ በኩል የተደረገው የሰላም ስምምነት ለበርካቶች በክልሉ ያለውን የጸጥታ ስጋት ይቀርፋል የሚል ተስፋን የሰጠ ነበር።

ይህ ስምምነት በመንግሥትም ሆነ በታጣቂው ቡድን ላይ የሚያስቀምጣቸውን ግዴታዎችን ለመፈጸም እና ሰላምን ለማምጣት ነበር ሁለቱም አካላት ፊርማቸውን ያኖሩበት። ጋብ እያለ የሚያረሸው በክልሉ ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በክልሉ የሚኖሩ ነዋሪዎችን በቁም የሚያባንን፤ ከክልሉ ውጪ ላለ ሰው ደግሞ ሕሊናን የሚረብሽ ዜና ሆኖ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ለመሆኑ ስለዚህ ግጭት እስካሁን ምን እናውቃለን?

ክልሉ በሦስት ዞኖች የተዋቀረ ሲሆን እነሱም ካማሺ፣ መተከል እና አሶሳ ዞኖች ናቸው። በቆዳ ስፋቱ ሰፊውን ክፍል የያዘው የመተከል ዞን የሕዳሴ ግድቡ መገኛ የሆነውን ጉባ ወረዳን ጨምሮ በውስጡ ሰባት ወረዳዎችን ይይዛል። ከአማራ ክልል እና ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰነው ይህ ዞን በተደጋጋሚ ጥቃቶች የሚፈጸምባቸውን ቡለን፣ ድባጤ፣ ወንበራ፣ ፓዌ፣ ዳንጉር እና ማንዱራ ወረዳዎችን አቅፏል። ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚዋሰነው ካማሺ ዞንም ከመተከል ሻል ያለ ሰላም ቢኖረውም በርካታ ሲቪሎች በተለያዩ ጥቃቶች ሲሸበሩ የቆዩበት ነው። ባለፉት ጥቂት ሳምንታትም ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የሚያመላክቱ ሪፖርቶች ተሰምተዋል።

በአሶሳ ዞን የሚኖሩ ሲቪሎችም ቢሆን ከነዚህ ጥቃቶች አላመለጡም። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኦዳ ቡልድግሉ ወረዳ የተፈጸመው መጠነ ሰፊ ጥቃት ለዚህ ማሳያ ነው። በጥቃቶቹም እጅግ በርካታ የሰው ሕይወት መጥፋቱን በተደጋጋሚ ተዘግቧል። እነዚህን ጥቃቶች የሚፈጽመው ታጣቂ ቡድን ሁለት የዕዝ ክፍሎች እንዳሉት ነዋሪነታቸው በክልሉ ውስጥ በመሆኑ ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸውን እንዳንጠቀም የጠየቁን ግጭቱን ለዓመታት ሲከታተሉ የቆዩ አጥኚ ለቢቢሲ ይናገራሉ። የሕዳሴው ግድብ በሚገኝበት የጉባ ወረዳ አካባቢ የሚገኘው የቡድኑ አንድ ክንፍ “ሻባን” ተብሎ በሚጠራ ግለሰብ ይመራል ተብሎ እንደሚታመንም እኚሁ ምንጭ ይናገራሉ።

ሁለተኛው ቡድን ደግሞ በቡለን ወረዳ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ከመንግሥት ጋር ሰላም ለማውረድ የተስማማው ይህ ክንፍ መሆኑን እንዲሁም በጉባ የሚገኘው ክንፍ ስምምነቱን ሳይቀበል መቅረቱን ምንጫችን ያስረዳሉ። ነገር ግን በዚህ ዘገባ ወቅት ሃሳባቸውን የሰጡ አካላት በሙሉ እንደሚስማሙት ይህ በተለምዶ “የጉሙዝ ታጣቂ” ተብሎ የሚጠራው ቡድን ከሌሎች አማጺያን ጋር ሲነጻጸር ጠንካራ የዕዝ ሰንሰለት፣ የደንብ ልብስ እንዲሁም ተለይቶ የሚታወቅበት ልዩ መጠሪያ የለውም። በጉባ በኩል ያለው ቡድን ከሌላው አካባቢ የበለጠ መዋቅራዊ ቅርጽ እንዳለው እና በአንጻሩ በካማሺ በኩል የሚታየው የቡድኑ እንቅስቃሴ ደግሞ “ማኅበረሰባዊ ግጭት (ኮሚውናል ቫዮለንስ) የመሰለ መልክ” እንዳለው በአካባቢው ስላለው ሁኔታ ለወራት የዘለቀ ጥናት ያደረጉ ሌላ ባለሞያ ይናገራሉ።

“በካማሺ በተለይም በ2011 እጅግ ተበራክቶ የቆየውን በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸም ጥቃትን ለመቆጣጠር የተቻለውም ለዚህ ይመስለኛል። በሁለቱ ማኅበረሰቦች (ጉምዝ እና ኦሮሞ) ሽማግሌዎች መካከል የተደረገው እርቅ የተወሰነ ውጤት አምጥቷል” ይላሉ። መስከረም 15 ቀን 2011 ዓ.ም. አራት የካማሺ ዞን አመራሮች በአሶሳ የተደረገውን ስብሰባ ጨርሰው በመመለስ ላይ ሳሉ ኦሮሚያ ክልል፤ ልዩ ስሙ መቀቢላ በተባለ ሥፍራ በታጣቂዎች መገደላቸው ብሎም ሲጓዙበት የነበሩ ሁለት መኪኖችም መቃጠላቸው ይታወሳል። ይህንን ተከትሎም በካማሺ ዞን ከመስከረም እስከ የካቲት 2011 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ200 በላይ ሲቪሎች ከሁለቱም ወገን መገደላቸውን ምንጫችን አክለው፣ ከዚያ ወዲህ ግን ግጭቶቹ ጋብ ማለታቸውንም ይጠቅሳሉ።

የሰላም ስምምነቱ ይዘት ምንድነው?

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጀመሪያ የተፈረመው ይህ ስምምነት 11 ነጥቦችን የያዘ ነው። እነዚህ ነጥቦችም ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ይዘቶች አሏቸው። በዚህም መሠረት የቡድኑ አባላት ትጥቃቸውን ፈተው መንግሥት የሚሰጠውን ስልጠና ሲያጠናቅቁ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታን ጨምሮ በመረጡት የሥራ መስክ እንዲሰማሩ የተለዩ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚቀርብላቸው ስምምነቱ ያስረዳል። በተጨማሪም ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ባለው መዋቅር ውስጥ የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎችን እንደሚያገኙ እንደሚደረግ ተገልጿል። በፀጥታው ዘርፍም ልምድ ያላቸው የቡድኑ አባላት ሰልጥነው የክልሉን ኃይል እንዲቀላቀሉ የሚያስችል ስምምነት ላይም ተደርሷል።

በዚህም “ትልቁ እና በእነሱ በኩል የሚጠበቀው የሰላም ጥሪውን ተቀብለው መሳሪያቸውን ማውረዳ ነው” ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ አቢዮት አልቦሮ ያብራራሉ። “ትጥቁን ፈትቶ የመጣው ኃይል ለዜጎች ሞት እና መፈናቀል ምክንያት መሆን የለበትም የሚለው ትኩረት የተሰጠው ዋነኛው የስምምነቱ አካል ነበር።” ኃላፊው እንደሚሉት በመንግሥት በኩል ደግሞ ታጣቂዎቹ ሰላማዊ ኑሮን ሲቀላቀሉ በኢኮኖሚ የማደራጀት እና የማቋቋም ሥራ የመስራት ግዴታ አለበት።

ለዚህም የተመረጡት ዘርፎች እርሻ፣ ማዕድን ማውጣት፣ የመስኖ ሥራ፣ የእንስሳት እርባታ እንዲሁም በተለይ ሴቶችን በጥቃቅን እና አነስተኛ ዘርፎች አደራጅቶ ወደ ሥራ ማስገባት የሚሉት እንደሆኑም ይናገራሉ። የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የመንሥት ስልጣን አግኝተው ከነበሩ የታጣቂ ቡድኑ አባላት መካከል የነበሩና አሁን ከነበሩበት የኃላፊነት ቦታ የለቀቁ አንድ ግለሰብን ቢቢሲ አነጋግሯቸዋል። ስለ ስምምነቱ ሲናገሩም “ተፈርሞ የነበረው ስምምነት በልዩ ኃይሉ፣ በንግዱ፣ በመከላከያው፣ በፖሊስም ሆነ በአመራር ውስጥ የሥራ (የስልጣን) ምድብ ማግኘት ላይ ያተኮረ ነበር” ሲሉ ይናገራሉ።

የስምምነቱ አተገባባር ምን ይመስላል?

የቤኒሻንጉል ክልል የሰላም እና የደኅንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አቢዮት እንደሚሉት እስካሁን ድረስ በሁለት ዙር ከ2500 በላይ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደዋል። እንዲሁም ይህንን ጉዳይ የሚያስፈጽም ጽህፈት ቤት ተቋቁሟል። በተጨማሪም እርሳቸው የሚመሩት ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ አፈጻጸሙን እየመራ መሆኑንም ይናገራሉ። “በመንግሥት በኩል አብዛኛው ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል። የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን በተመለከተ ግን ፍላጎታቸው ተወስዶ የአስፈላጊ መሳሪያዎች ግዢ በመንግሥት በኩል እንዲፈጸም ቀርቦ በሂደት ላይ ነው” ሲሉ አቶ አቢዮት ያስረዳሉ። ከስምምነቱ በኋላ ተመልሰው ወደ ጫካ የገቡት የታጣቂ ቡድኑ አባል በዚህ አይስማሙም። በሚያዚያ ወር የመጀመሪያውን ዙር የተሃድሶ ስልጠና መውሰዳቸውን ይናገራሉ።

“መንግሥት ጨዋታ ነው የያዘው” ሲሉ ሂደቱን በብርቱ በመተቸት “የግልገል በለስ ወረዳ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ነበርኩ። ከዚያ ሰዎች ሲገደሉ ስንመለከት ተመልሰን ወደ ጫካ ገባን” ይላሉ። ለዚህም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዳልሆነ በመግለጽ “እስካሁን በእኛ ወረዳ አራት ሰው ብቻ ነው የተሾመው። ለእኛ ቃል የተገባው በሙሉ እንዲሰጥ ነው የምንፈልገው። የክልሉ መንግሥት የሚሰጠው መልስ ግን “በኋላ በኋላ” የሚል ነው” በማለት ቅሬታቸውን ይገልጻሉ። የክልሉ የፀጥታ ኃላፊ የሆኑት አቶ አቢዮት በተለይም ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ለማስፈጸም ከፍተኛ በጀት እንደሚጠይቅ እና በክልሉ በጀት ብቻ የሚቻል አለመሆኑን ይናገራሉ።

በዚህም ምክንያት ፕሮጀክት ተቀርጾ የፌደራል መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ ቀርቦ ስምምነቱ ወደ መሬት እንዲወርድ መንግትሥት ሥራዎችን እያከናወነ ነው ሲሉም ያስረዳሉ። እነዚህን ፕሮጀክቶች ለማሳካትም በግርድፉ ከ300 እስከ 500 ሚሊዮን ብር እንደሚጠይቅ አቶ አቢዮት ለቢቢሲ ተናግረዋል። “የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ከመጡ በኋላ መንግሥት ቃሉን አልፈጸመም እና ተመልሰን ጫካ እንመለሳለን የሚል ካለ ድምዳሜው የሚሆነው ሽፍትነትን ስለሚፈልግ ነው የሚል ነው የሚሆነው” ይላሉ አቶ አቢዮት። “በአጭር ጊዜ የተከናወኑ ሥራዎች አሉ እንዲሁም ጊዜ የሚጠይቁ ሥራዎችም አሉ። ይህም እየተገመገመ ይገኛል” ሲሉ አክለዋል። ወደ ጫካ የተመለሱት ግለሰብ ከስምምነቱ ተግባራዊ አለመሆን በተጨማሪ የደኅንነት ስጋትን እንደአንድ ምክንያት ያነሳሉ። ለዚህም ሸሪፎ አደም እና ግዱ ዳኘው የተባሉ ግለሰቦችን እንደ ምሳሌ በማንሳትም የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ኃላፊነት ካገኙ በኋላ መገደላቸውን ይጠቅሳሉ።

አቶ አቢዮት “ግድያ አልተፈጸመም። በፍጹም እንክብካቤ ወደየአካባቢያቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ነው። ነገር ግን ከሄዱ በኋላ ወደ ሽፍትነት ተመልሰው ንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ካሉ መንግሥት እርምጃ የማይወስድበት ምክንያት የለም” ሲሉ ተናግረዋል። ቢቢሲ ሁለት የቡለን ከተማ ነዋሪዎችንም የሰላም ስምምነቱን ውጤት እንዴት ትመለከቱታላችሁ ሲል ጠይቋል። ግድያዎቹ አሁንም መቀጠላቸውን እና አንዳንድ በሹመት የመጡ ታጣቂዎች ከዚህ ቀደም ታዋቂ ሰዎችን ጨምር ግድያ መፈጸማቸው ቅሬታ እንዲገባቸው እንዳደረገ ይናገራሉ።

“አሁን ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ለመናገር እንፈራለን። ለመከላከያም ለመናገር እንፈራለን። በየቀኑ አሁንም ሰው ይሞታል። እናንተ የምትሰሙት 10 ወይ 20 ሰው ሲሞት ነው። እኛ እራሳችን ዛሬ እንሙት ነገ አናውቅም” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። በቡለን ወረዳ አራት የታጣቂው ቡድን አባላት የሚሊሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊ፣ የትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የወረዳው ምክር ቤት አፈጉባኤ እንዲሁም የከተማው ማዘጋጀ ቤት አፈጉባኤን ሹመት አግኝተው እንደነበር አንድ በመንግሥት ሥራ ውስጥ ያሉ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል። አሁን ግን አራቱም ተመልሰው ወደ ጫካ መግባታቸውን የገለጹ ሲሆን ቢቢሲ ይህንን ከመተከል ዞን አስተዳዳሪ ለማጣራት ቢሞክርም ምላሽ አላገኘም።

ክልሉን በማረጋጋት የሌሎች ክልሎች ተሳትፎ

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት እስካሁን ከሦስት ክልሎች ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ፈርሟል። እነሱም የጋምቤላ እና የኦሮሚያ ክልሎች ሲሆኑ በቅርቡ ደግሞ ከአማራ ክልል ጋር ተመሳሳይ ስምምነት መደረሱ በይፋ ተገልጿል። የስምምነቶቹ ይዘት ምን እንደሚመስል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የፀጥታ ቢሮ ኃላፊው አቶ አቢዮት “ከአጎራባች ክልሎች ጋር በጋራ የመልማት፣ በወንድማማችነት የሰላሙን ስራ በጋራ የመስራት ብሎም የቀጠናው ሕዝቦች ዘላቂ ሰላም አግኝተው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ያለመ ነው” ይላሉ። እነዚህን ስምምነቶች የሚያስፈጽሙ ጽህፈት ቤቶች በሁሉም ክልሎች ተቋቁመው በሰላም ብሎም በጋራ የልማት ተጠቃሚነት ዙሪያ ይሰራሉም ይላሉ ኃላፊው።

በተጨማሪም ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ከአማራ ክልል በተጨማሪ የጋምቤላ፣ የሲዳማ እንዲሁም የደቡብ ክልል ልዩ ኃይሎች በክልሉ ውስጥ መሰማራታቸውን ገልጸዋል። እነዚህ ኃይሎችም በክልሉ በተቋቋመው የዕዝ ማዕከል (ኮማንድ ፖስት) የሚታዘዙ እና በቀጠናው ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ከግምት ያስገባ ነውም ይላሉ። “ይህ የሆነውም አካባቢው የሕዳሴው ግድብ መገኛ ብሎም አሸባሪው ህወሓት በሱዳን በኩል ሰርጎ እየገባ በዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽመበት በመሆኑ ነው” ሲሉ አቶ አቢዮት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቀጣይ ስጋቶች

የክልሉ መንግሥት ስምምነቱ አንጻራዊ ሰላምን አምጥቷል ብሎ ያምናል። ታጣቂዎች መሳሪያቸውን ጥለው በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩ ማስቻል ግን አንደኛው አማራጭ እንጂ ብቸኛው አይደለም የሚል አቋም አለው። “ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሰላም ጥሪውን ባልተቀበሉ አካላት ላይ ወታደራዊ እርምጃ በመውሰድ አካባቢውን ከፀረ ሰላም ኃይል ማጽዳት እና ሰላማዊ ማድረግ” ሌላ አማራጭ መሆኑን የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል። “እኛ ሰላምን ነው የምንፈልገው” የሚሉትና ወደ ታጣቂው ቡድኑ የተመለሱት ግለሰብ “መንግሥት ለሰላም ብዙ ሚሊዮን ብር እያወጣ ይገኛል። እኛም ሰላምን ተቀብለናል” በማለት ጥቃት እንደሚፈጸምባቸውና አድሏዊ አሰራር መኖሩን ይገልጻሉ።

በተደጋጋሚ የጉምዝ ታጣቂዎች ከክልሉ በተለይም ከሌሎች አካባቢዎች በሰፈራ የሄዱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የማስወጣት አላማ አለው የሚል ክስ እንደሚቀርብ በማንሳት “የታጣቂ ቡድኑ አላማ ምንድነው?” የሚል ጥያቄ አቅርበንላቸዋል። “የእኛ ሃሳብ አድሎአዊ አሰራር እንዲቆም ነው። እኛ ማንም ከቤኒሻንጉል ይውጣ የሚል ሃሳብ የለንም። አብረን እንድንሰራ እና ሁላችንም እኩል ተጠቃሚ እንድንሆን ነው የምንፈልገው። ሥራ እንድንሰራ፣ ግጭት እንዳኖር ብሎም ሰላም እንዲመጣ ነው ፍላጎታችን። አብረን ሥራ ብንሰራ ወንጀል ነው እንዴ?” ሲሉ ክሱን ያስተባብላሉ።

አምስት ወራትን ያስቆጠረው ስምምነት በተለይም ለነዋሪዎች የታሰበውን ያህል ለውጥ አላመጣም። ቢቢሲ ያናገራቸው በአሶሳ እና ቡለን ከተማ የሚኖሩ ግለሰቦች እንደሚሉት የፀጥታ ችግሩ በአካል እና በሕይወት ላይ ከሚያስከትለው ስጋት ባለፈ የኑሮ ውድነትን አስከትሏል ይላሉ። ወደ ክልሉ የሚወስዱ መንገዶች ላይ ባለው የፀጥታ ችግር ሳይታጀቡ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ መነገድም ሆነ መንቀሳቀስ ያለመቻሉ እንደ አገር ካለው የኑሮ ጫና ጋር ተደምሮ የለት ተለት ኑሯቸው ላይ ዕክል መፍጠር መጀመሩንም ይናገራሉ። በቀጣይ ወራት ይህ ስምምነት የሚሄድበት መንገድ እና ይዞት የሚመጣው ለውጥ ካለ ለማየት በተስፋ እንደሚጠብቁም ይናገራሉ።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *