የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ዓርብ መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢትዮጵያ፣ በትግራይ ክልል ግጭት በሚሳተፉ ኃይሎች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ያሳለፉት ትዕዛዝ ተግባራዊ እንዳይሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሓት ግጭቱን ለማቆም ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ ሊደርጉ እንደሚገባ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ተጠሪ አስታወቁ፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ያዘዙት ማዕቀብን አስመልክቶ በበይነ መረብ አማካይነት ማክሰኞ መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት ማበራሪያ፣ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ዓርብ የፈረሙት የሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ፣ የሚጣለውን ማዕቀብ የሚያመለክት ዝርዝር ማዕቀፍ እንጂ ማዕቀብ አለመጣሉን አስረድተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የምሥራቅ የአፍሪካና የሱዳን ተጠባባቂ ረዳት ተጠሪ የሆኑት ብሪያን ሃንት፣ ፕሬዚዳንቱ ባስቀመጡት ማዕቀፍ መሠረት ማዕቀቡ እንዳይጣል የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሓት ትርጉም ያለው አንድ ዕርምጃ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ትርጉም ያለው ዕርምጃ በማለት ከጠቀሷቸው መካከልም ሁለቱም ወገኖች የአፍረካ ኅብረት አደራዳሪነትን ሚና መቀበልና የአፍሪካ ኅብረት ለሚያቀርበው የድርድር ጥሪ ያለ ቅድመ ሁኔታ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት የሚጠበቅባቸው መሆኑን ረዳት ተጠሪው ብሪያን ሃንት አስታውቀዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የድርድር ጥሪን ከመቀበል ባሻገር ሁለቱም ወገኖች ተደራዳሪ ቡድኖችን መሰየም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ያልተገደበ የሰብዓዊ አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርስ ማድረግም ሌላኛው ትርጉም ያለው ዕርምጃ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ይህ ከሆነ የአሜሪካ መንግሥት ማዕቀቡን ከመጣል ተቆጥቦ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን መልሶ ለመገንባት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የፋይናንስና ማዕቀብ ጉዳዮች ረዳት ተጠሪ የሆኑት ኤሪክ ውድሐውስ በበኩላቸው፣ ‹‹ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ማዕቀብ አልጣሉም፡፡ እንደዚያ እንዳይሆንም ተስፋ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

ይህ እንዳይሆን ግን ሁለቱም ወገኖች ግጭቱን ለማቆም ተጨባጭ የሆነ ዕርምጃ መውሰድ አለባቸው፣ የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መውጣት አለበት፣ ያልተገደበ ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ክልሉ እንዲደርስ የኢትዮጰያ መንግሥት ማድረግ አለበት፣ የሕወሓት ኃይሎችም ከትግራይ ክልል ውጪ የሚያደርጉትን የውጊያ እንቅስቃሴ ማቆም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ በግጭቱ እየተሳተፉ ያሉ አካላት የተገለጹትን ዕርምጃዎች እንዲተገብሩ የአሜሪካ መንግሥት የጊዜ ገደብ አስቀምጦ እንደሆነ የተጠየቁ የሥራ ኃላፊዎቹ ጥያቄውን በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ ሁለቱም በፍጥነት ተጨባጭ ዕርምጃ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ዓርብ ማዕቀብ እንዲጣል የፈረሙት የሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ‹‹ግልጽ ደብዳቤ ለፕሬዚዳነት ጆ ባይደን›› በሚል ርዕስ ባወጡት መልዕክት መንግሥታቸውም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጭ ጫና እንደ እንደማይንበረከኩ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ ሕወሓት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ማዕቀብ እንዲጣል ያሳለፉትን የሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ እንዲሚደግፍ አስታውቋል፡፡

ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ ደግሞ የአፍሪካ ኅብረትን አደራዳሪነት ለመቀበል እንዲሚቸገር መግለጹ ይታወሳል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *