የህወሓት አማጺያን ራያ ቆቦ አካባቢ ባሉ ነዋሪዎች ላይ ከአንድ ሳምንት በፊት በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ከስፍራው ሸሽተው የወጡ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ሲናገሩ ኢሰመኮ ደግሞ ስለጥቃቱ ሪፖርቶች እንደደረሱት አመለከተ።

ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመ ነው ያሉት ጥቃት የከባድ መሳሪያ ድብደባና ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳ መሆኑን ነዋሪዎቹ ጠቅሰው፤ በርካቶች መሞታቸውን ነገር ግን ስለደረሰው ጉዳት አሃዝ በትክክል ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል። ቢቢሲ ያናገራቸው ግለሰቦች ጥቃቱ ሲፈጸም በስፈራው እንደነበሩና በአሁኑ ወቅት ደሴ ከተማ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል። የራያ ቆቦ አካባቢ ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ አሁን ድረስ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ቅዳሜ ዕለት ጥቃቱን በተመለከተ ባወጣው አጭር መግለጫ “በቆቦ ከተማና በዙሪያው ካሉ የገጠር ከተሞች በህወሓት ኃይሎች እንደተፈጸመ የሚነገረው ሲቪሎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በእጅጉ የሚያሳስበው” መሆኑን አመልክቷል። ኮሚሽኑ ደረሱኝ ባላቸው ሪፖርቶች ጥቃቶች “በመኖሪያ አካባቢዎች፣ የቤት ለቤት አሰሳና ግድያ፣ ዝርፊያ እንዲሁም የሲቪል መሰረተ ልማቶች” ላይ መፈጸማቸውን ጠቅሶ ምርመራ እንደሚያደርግ ገልጿል።

አካባቢው በቁጥጥሩ ስር የሚገኘውና በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በቆቦና በአካባቢው ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት አስካሁን ያለው ነገር የለም። የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ስለክስተቱ ከዘገቡት ውጪ የክልሉ መስተዳደርም ሆነ የፌደራል መንግሥቱ የሰጡት ማብራሪያ የለም።

በራያ ቆቦ ተፈፀመ ስለተባለው ጥቃት ነዋሪዎች ምን አሉ?

የራያ ቆቦ በተለይም ደግሞ በቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙንና በርካታ ሰዎች መገደላቸውን በተመለከተ ሪፖርቶች ሲወጡ ቀናት የተቆጠሩ ቢሆንም አካባቢው በህወሓት ቁጥጥር ሥር ከዋለ ጊዜ ጀምሮ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል። በአካባቢው ተፈጸመ የተባለውን “ጭፍጨፋ” ተከትሎ በወቅቱ በቦታው የነበሩ፣ ነገር ግን ከጥቃቱ በኋላ ከአካባቢው ሸሽተው መውጣታቸውን የተናገሩ የዓይን እማኞችን ቢቢሲ አግኝቶ ስለክስተቱ ጠይቋል።

ህወሓት አካባቢውን ከተቆጣጠረ ጊዜ ጀምሮ ከቆቦ ከተማ ወጥተው እንደማያውቁ የሚናገሩትና በቅርቡ ከተከሰተውና በርካታ ሰዎች ተገድለውበታል ካሉት ጥቃት አምልጠው ደሴ መግባት የቻሉት አቶ አለሙ አበበ እና ከድር አሊ* በወቅቱ በስፍራው እንደነበሩ ይናገራሉ። በንግድ ሥራ ይተዳደር የነበረው ከድር፣ የህወሓት ኃይሎች ወደ አካባቢው “ከገቡ ጊዜ ጀምሮ የመንግሥት እና የግለሰብ ቤትን ከመዝረፍ እና ከማውደም በዘለለ ለአንድ ወር ያህል በሰው ላይ ብዙም እንግልት አልደረሰም ነበር” ይላል።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቋረጡ ነዋሪው እህል አስፈጭቶ ለመመገብ ተቸግሮ ስለነበር ቆቦ ጊራና ከሚባለው ፕሮጀክት ጀኔሬተር በማስነሳት ወፍጮዎች አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ሰዉን መመገብ ጀምረው እንደነበርም ያስታውሳል። ከድር እንደሚለው ግን ይህ አገልግሎት የቆየው ለአምስት ቀናት ብቻ ነበር። እንደ አቶ ከድር ገለጻ ከሆነ ከአምስት ቀናት በኋላ ወደ ቆቦ ተቀይሮ የመጣው የአማጺያኑ አመራር “ጀኔሬተሩን ነቅሎ ወሰደው” የሚለው ከድር።

“የተቀየረው የህወሓት ኃይል አመራርም አርብ መጥቶ ቅዳሜ ነሐሴ 22 አራሞ እና ገደመዩ ወደሚባሉ የገጠር ቀበሌዎች በማምራት “መሳሪያ አምጡ” በማለት ተኩስ ከፈቱ” በማለት አካባቢው በህወሓት ቁጥጥር ሥር ከዋለ ከአንድ ወር በኋላ በራያ ቆቦ ዳግም ስለተቀሰቀሰው ጦርነት ያብራራል። ጦርነቱ ወደ አማራ ክልል መዛመቱን ተከትሎ ከዚህ ቀደም ርዕሰ መስተዳደሩ የክልሉ ነዋሪ በሙሉ እራሱንና አካበቢውን እንዲጠብቅ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በዚህ ጥቃትም መሳሪያ አምጣ በማለት ካሳ ከበደ የሚባል የአራሞ ቀበሌ ነዋሪ መገደሉንና አጠገቡ የነበረው የ13 ዓመት ታዳጊም አባቴን ብሎ ወደአባቱ አስከሬን ሲቀርብ መገደሉን ከድር ይናገራል። “በተመሳሳይ ግድያ ሌሎች አርሶ አደሮች ላይም መሳሪያ አምጡ በሚል ሰበብ ተፈጽሟል [ስም ይጠቅሳል]” የሚለው ከድር፣ “እንደዚህ መግደል ሲጀምሩ አርሶ አደሩ ራሱን ለመከላከል መልስ መስጠት ጀመረ” ይላል።

በእዚሁ ዕለት [ነሐሴ 22/2013 ዓ.ም] ጥቃት የተከፈተባቸው የገጠር ቀበሌ አርሶ አደሮች ራሳቸውን እያጠናከሩ እና ኃይል እየጨመሩ “የህወሓት ታጣቂዎችን ከገጠሩ አካባቢ አስወጥተው ወደ ከተማው [ቆቦ] አደረሷቸው” ነገር ግን አርሶ አደሮቹ ወደ ከተማው ሳይገቡ ወደ መጡበት እንደተመለሱ ዓለሙ ለቢቢሲ ተናግሯል። ከዚህ ቀን በኋላ ለአምስት ቀናት በገጠሩም ሆነ በከተማው ተጨማሪ ጥቃት አለመፈጸሙን ዓለሙ እና ከድር ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

መሳሪያ አምጡ

በአምስተኛው ቀን ነሐሴ 27/2013 ዓ.ም ግን የህወሓት ኃይሎች የቆቦ ከተማን ከብበው “መሳሪያ አምጡ” እያሉ ነዋሪውን መደብደባቸውን ያስታውሳሉ። “መሳሪያ ያለው ሰጠ፣ የሌለው ደግሞ የለኝም በማለቱ ከፍተኛ ድብደባ ይፈጽሙበት ነበር” ብለዋል። ሦስተኛውና ከፍተኛ የሰው ሕይወት ያለቀበት ጥቃት የተፈጸመው በጳጉሜ አራት መሆኑን ሁለቱም ምንጮቻችን ይናገራሉ። በነሐሴ 27 ‘መሳሪያ አምጡ’ እያሉ የከተማውን ሕዝብ ከደበደቡ በኋላ ጳጉሜ 4 ደግሞ ኃይላቸውን አጠናክረው የገጠሩ ነዋሪ ጋር ጦርነት መግጠማቸውን ገልጸዋል።

“በዚህም ከቆቦ ከተማ በስተምሥራቅ በምትገኘው ገደመዩ ከተባለች የገጠር ቀበሌ ላይ የህወሓት ታጣቂዎች ከባድ ጦርነት ከፍተው ውጊያ ተካሄደ” ይላሉ። በዕለቱ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት የጀመረው ውጊያ ለረጅም ሰዓታት መቆየቱን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ “አርሶ አደሩ ከሁሉም አቅጣጫ ኃይሉን አጠናክሮ የህወሓት ታጣቂዎችን ላይ በመበርታቱ ከ10 ኪሎሜትር በላይ ገፍቶ ውጊያው አስከ ቆቦ ከተማ ድረስ ደረሰ” ሲሉ ይናገራሉ።

በዚህ ጦርነትም የህወሓት ኃይሎችን ከከተማው ከአብዛኛው አካባቢ በማስወጣት የአማጺው የጥይት ማስቀመጫን ይዘው የሚፈልጉትን ወስደዋል። አመሻሽ 11፡00 ሰዓት ሲሆን አርሶ አደሮቹ ከተማውን ለቀው በዙሪያዋ ወደ ሚገኙት ገጠር መንደሮቻቸው እንደተመለሱ ከድርና አለሙ ገልጸዋል።

“የበቀል ጥቃት”

ነገር ግን አርሶ አደሮቹ ወደ አካባቢያቸው መሄዳቸውን ተከትሎ የህወሓት ታጣቂዎች ተመልሰው ወደ ከተማው በመግባት “ለደረሰባቸው ጥቃት በቀላቸውን በንጹኀኑ እና በጦርነቱ ባልተሳተፉ ሰዎች ላይ አሳርፈዋል” ይላል አለሙ። “በየቤቱ ጦርነቱን ፈርቶ የተቀመጠውን ሰው ሁሉ ቤት ለቤት እየዞሩ ገደሉ። ከዚያ ውጪ በእርሻ ቦታዎች አረም ሲያርም ውሎ ወደ ቤቱ የሚገባውን ሰው ሁሉ መንገድ ላይ እየጠበቁ ገደሉት” ብሏል ከድር።

ተመሳሳይ ክስተት ማስተዋሉን የሚናገረው አለሙ “የከተማው ሰው ምንም ዓይነት ጥቃት አልከፈተም፤ የበቀል መወጣጫ ነው ያደረጉት” ብሏል። በግድያው በተለይ ወጣቶች ዒላማ እንደነበሩም አለሙ ተናግሯል። እርሱም በወቅቱ መጠነኛ የመቁሰል አደጋ እንዳጋጠመው የሚናገረው ከድር “ከሴት እና ሕጻናት ውጪ ያገኙትን ሰው ሁሉ አጥቅተዋል፤ በብዛት ደግሞ የገበሬ መታወቂያ ያለው እና ሽርጥ የታጠቀውን የከተማውን ገበሬ ነው የጨረሱት። ሴቶችና ሕጻናት ግን በተባራሪ ጥይት ካልሆነ በስተቀር ታስቦበት ጥቃት ሲፈጸም አላየሁም” ብሏል።

በጥቃቱ ብዙ ሰው እንደተገደለ ሁለቱም ምንጮቻችን ይስማማሉ። ነገር ግን የሟቾች መጠን ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ እንደሚቸገሩ ገልጸዋል። “ጭፍጨፋው እጅግ የከፋ ነበር” የሚለው ከድር “የከተማው አርሶ አደር በብዛት ነው የተጎዳው። ነገር ግን በወቅቱ ቆስዬ ስለነበረ ለቀብር ስላልወጣሁ የሞተውን የሰው ቁጥር ይህንን ያህል ይሆናል ለማለት ይቸግረኛል” በማለት የሟቾች ቁጥር በመቶዎች ሊሆን እንደሚችል ይገምታል።

ወንድሞቹንና ጓደኞቹን ቀብሮ መስከረም 02/2014 ዓ.ም ከስፍራው በመውጣት ወደ ደሴ መግባት የቻለው ዓለሙ ደግሞ “የሞተውን ሰው ብዛት ለመናገር ይከብደናል። አርብ እና ቅዳሜ [ጳጉሜ 5 እና መስከረም 1] ከአንድ ጉድጓድ ሦስትም አራትም እያደርግን ነው የቀበርነው። በቆቦ ከተማ ውስጥ አምስት አብያተ ክርስቲያናት እና አንድ የሙስሊም መቃብር ቦታ አለ። በስድስቱም ቦታዎች ቀብረናል። በእኛ ቤተ ክርስቲያን (ጊዮርጊስ) ብቻ በሁለቱ ቀናት ከ50 ሰው በላይ ቀብረናል” ብሏል።

በተመሳሳይ ቀን አካባቢውን ለቅቆ የወጣው ከድርም የህወሓት ታጣቂዎች ጳጉሜ አራት የከተማው ነዋሪ ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ኃይል ሲጨምሩ አድረው በማግስቱ አርብ “በከተማው ዙሪያ የሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችን በከባድ መሳሪያ እንደደበደቧቸው” ተናግሯል። በዚሁ ጥቃትም “አራሞ፣ ገደመዩ፣ አራዱም፣ ዳልቻ፣ ቀዩ ጋሪያ፣ ቀመሌ፣ ጮሪ፣ መንደፈራ፣ ጎለሻ እና ጮቢ በር የተባሉ የገጠር ቀበሌዎች ተድብድበዋል” ብሏል።

አማጺያኑ መስከረም አንድ [ቅዳሜ] ምንም አላደረጉም ያለው ከድር እሁድ በከባድ መሳሪያ የተወሰኑ ቀበሌዎችን ሲደበድቡ መዋላቸውን ገልጿል። እንደዚያም ሆኖ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱት በከተማው ነዋሪ ላይ እንደሆነ “እኔ ከቆቦ ከተማ በወጣሁበት አካባቢ [በተለምዶ ዞብል መውጫ] በርካታ ከብቶችና የጋማ እንስሳት ተገድለው ተመልክቻለሁ” ብሏል ከድር።

“ዘረፋና የንብረት ውድመት”

የገጠሩ አርሶ አደር በተፈጸመው ጥቃት ምክንያት ቤት ንበረቱንና ማሳውን ለቆ ጫካ እንደገባና የአርሶ አደሩ ማሳም ያለተንከባካቢ መተዉን ይናገራል። ከዚህ በተጨማሪ በቆቦ ከተማ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ሙሉ በሙሉ መዘረፋቸውን የሚናገረው ከድር፣ የግለሰብ ንብረትም በተመሳሳይ ተዘርፏል ብሏል። የእርሱ የማከፋፈያ ሱቁም እንደተዘረፈ የተናገረው ከድር፣ ይህንንም በአካባቢው መሪ ሆኖ ለመጣው የህወሓት ታጣቂ ቢያመለክትም “እኔ የምመራው ጦሩን ነው፣ ይህ ጉዳይ የሚመለከተው መሪ ሌላ ስለሆነ መሆኒ ሄደህ አመልክት” እንደተባለ እና ተስፋ ቆርጦ እንደቀረ ተናግሯል።

አለሙ እንደሚለው ደግሞ ዘረፋው ከመንግሥት ተቋማት እና ከግለሰብ ንብረት የዘለለ ነው። “እንኳን የሱቅ እቃ ሰው ያልገባባቸው የማኅበር ቤቶች ቆርቆሮ እየተገነጠሉ ተወስደዋል” ብሏል። ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የጀመረው የትግራይ ጦርነት ለወራት ከቆየ በኋላ ሰኔ ላይ የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ገልጾ ከክልሉ ሲወጣ የህወሓት ኃይሎች አብዛኛውን የትግራይ አካባቢዎች መቆጣጠራቸው ይታወሳል።

በማስከተልም የህወሓት ኃይሎች ወደ ፊት በመግፋት ወደ አፋርና አማራ ክልል ገብተው ጥቃት በማድረስ ጦርነቱ ከትግራይ ክልል ባሻገር ወደ አጎራባቾቹ ክልሎች ተስፋፍቶ አሁን ድረስ እየተካሄደ መሆኑ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። በርካታ ቦታዎችን በፌደራል መንግሥቱ ላይ ጫና ለማሳደር አውጆ በአካባቢው ምንም አይነት የግንኙነት መስመር ስለሌለ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት አልተቻለም።

*ቆቦ ለሚገኙት ቤተሰቦቻቸው ደኅንነት ሲሉ ስማቸው እንዲቀየር በጠየቁት መሰረት ተቀይሯል

ምንጭ – ቢቢሲ