የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከትግራይ ክልል ቀውስ ጋር በተገናኘ በተመረጡ የኢትዮጵያ አመራሮች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ማዘዛቸውን ተከትሎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ‹‹ግልጽ ደብዳቤ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት›› በሚል ርዕስ በጻፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ለውጭ ተፅዕኖ እንደማትንበረከክ አስታወቁ፡፡ ‹‹ከብዙኃን ደኅንነት ይልቅ ሥልጣንን ያስቀደሙ ግለሰቦች ባቀናበሩት ሴራ ለመጣው የውጭ ግፊት ኢትዮጵያ አትንበረከክም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣  ‹‹ኢትዮጵያዊ ማንነታችንና አፍሪካዊ ማንነታችን ይህ እንዲሆን አይፈቅድም፤›› ብለዋል፡፡

አክለውም ቀደምት የአፍሪካ መንግሥታት ላይ የደረሰው በደልና ግፍ በአሁኑ ወቅት በዚህች ምድር ላይ ሊደገም እንደማይችል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለም ምድር የሆነች ነፃ አገር ሌሎች በርካቶች በትግላቸው ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ ተምሳሌት የሆነች የሆነች አገር ናት፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ የሕወሓት ቡድን የ3,000 ዓመት ታሪክ ያላትን ትልቅ አገር ለማጥፋት የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለና አሁንም ይኸው ቡድን በሰብዓዊነት ስም በፈጠረው ፕሮፓጋንዳ፣ በኢትዮጵያ ላይ የውጭ ጫና እንዲመጣ ማድረጉን ገልጸው፣ የዚህ ቡድን ቅዠት ግን እንደማይሳካ አስታውቀዋል፡፡

አዲሱ የአሜሪካ መንግሥት ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ የሚገኙ በተለይ የአፍሪካ በተለይ የአፍሪካ አገሮች የአሜሪካ መንግሥት ከቀደመው በግለሰብ ተፅዕኖ ሥር ከወደቀ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው ይላቀቃል የሚል  ተስፋ እንደነበራቸውም ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በግለሰብ ፖሊሲ አውጭዎች ተፅዕኖ ሥር ወድቆ መቀጠሉንና እንደ ሕወሓት ባሉ ‹‹አሸባሪ›› ቡድኖች ጭምር ተፅዕኖ የሚያርፍበት መሆኑን በአሉታዊነት አንስተዋል፡፡

የተለያዩ የአሜሪካ መንግሥታት ያልተጠኑ ቅፅበታዊ ውሳኔዎችን በማሳለፍ በሌሎች አገሮች የውስጥ ጉዳይ ላይ ያደረጉት ጣልቃ ገብነት መፍትሔ ከማምጣት ይልቅ፣ ሕዝቦችን ለባሰ ቀውስ ሲደረግ እንደነበር ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ፣ ኢትዮጵያ ግን እንደማትንበረከክ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ይህንን ግልጽ ደብዳቤ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የጻፉት፣ ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ባዘዙ በሰዓታት ውስጥ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዓርብ መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በፈረሙት የሥራ አስፈጻሚ አካል ትዕዛዝ (Executive Order) የትግራይ ክልል ግጭት እንዲራዘም፣ ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳይቀርብ ያስተጓጎሉና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይደረስ እንቅፋት ሆነዋል ባሏቸው ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል ወስነዋል። ማዕቀቡ እንዲጣል ያዘዙትም ከላይ ለተጠቀሱት ጉዳዮች ተጠያቂ ናቸው በተባሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና የአማራ ክልል መስተዳደር ባለሥልጣናት ላይ፣ እንዲሁም በሕወሓትና በኤርትራ መንግሥት አመራሮች ላይ እንደሆነ የአሜሪካ መንግሥት ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።

ተጠያቂ ናቸው የተባሉት የመንግሥት ባለሥልጣናትና የሕወሓት አመራሮች ማንነት ግን ይፋ አልተደረገም። ይሁን እንጂ የአሜሪካ የመንግሥት ግምጃ ቤት ከአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጋር በመተባበር ተጠያቂ መሆን የሚገባቸውን እየለየ፣ ማዕቀቡን ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ማዕቀቡ በተመረጡ ግለሰቦች ላይ ብቻ ተግባራዊ እንደሚደረግና የኢትዮጵያ ሕዝብን በማይጎዳ መንገድ እንደሚተገበር፣ የአገሪቱ መንግሥት ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።

ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ የጉዞ ማዕቀብ በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት አመራሮችና የሕወሓት መሪዎች ላይ መጣሉ ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ይፋ ከሆነ በኋላ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በሰጡት አስተያየት፣ የትግራይ ክልል ቀውስ የሚቆም ከሆነ አሜሪካ ማዕቀቡን እንደምታዘገይ ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ክልል ግጭት እየተሳተፉ ያሉ አካላት ግጭቱን አቁመው ወደ ተኩስ የማቆም ድርድር ያለ ቅድመ ሁኔታ የሚገቡ ከሆነ፣ አሜሪካ ማዕቀብ መጣሉን ልታዘገይና ድርድሩን ልትደግፍ እንደምትችል አስታውቀዋል፡፡

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *