በትግራይ ክልል የተከሰተው ጦርነት ወደ አጎራባቹ አማራ ክልል መዛመቱን ተከትሎ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ከመኖሪያቸው አፈናቅሏል።
በርካቶችም ከፍተኛ የምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸውን ሴቶችና ሕፃናትን የሚያሳዩ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት ተጋርተዋል። ነገር ግን እነዚህን ምስሎች በምንመረምርበት ወቅት አንዳንዶቹ ከሌሎች ስፍራዎች ከሶማሊያ፣ ከትግራይ አልፎ ተርፎም በ1977 ከተከሰተው አስከፊ ረሃብ የተወሰዱ መሆናቸውን የቢቢሲ ሪያሊቲ ቼክ ተመልክቷል።
በአማራ የምግብ እጥረት ምን ያህል አሳሳቢ ነው?
የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ባወጣው መረጃ በአማራ ክልል በተዛመተው ጦርነት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ 500 ሺህ በላይ መድረሱን ያስታወቀ ሲሆን በክልሉ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነው ብሏል።
በተወሰነ መልኩ የምግብ ዕርዳታ ወደ ክልሉ ቢደርስም ነገር ግን በከፍተኛ ሁኔታ በምግብ እጥረት ተጠቅቷል በተባለው ሰሜን ወሎ ያሉ ነዋሪዎችን ለመድረስ ችግር እንደሆነና በተቃዋሚ ኃይሎች “ክልከላ ገጥሞታል” ተብሏል።
“ህወሃት የረድዔት ድርጅቶች ለተቸገረው ህዝብ እርዳታ እንዳያደርሱ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱ ሁኔታውን እያባባሰው ነው” በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ አቀባይ ቢልለኔ ስዩም ተናግረዋል።

ህወሃት በዚህ አይስማማም በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች የመገናኛ ዘዴዎችንና መብራት በማቋረጥ ከበባ ፈፅሟል በማለት መንግሥትን ተጠያቂ አድርጓል። የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የምግብ እጥረት ቢያጋየጥማቸውም “በዚህ ወቅት በሰሜን ወሎ ረሃብ ስለመከሰቱ ምንም ማስረጃ የለንም” ብሏል።
“ነገር ግን ጦርነቱ በዚህ ከቀጠለ ባለው ውጊያ ምክንያት በርካታ ስፍራዎች ተደራሽ ሳይሆኑ ስለሚቀሩ የምግብ ዋስትናውም አደጋ ውስጥ ይገባል” ብሏል የዓለም ምግብ ፕሮግራም።
አሳሳች ምስሎች
በአማራ ክልል ሰብአዊ ሁኔታ ላይ ትኩረት እንዲደረግ በተያዘው የዘመቻ እንቅስቃሴ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ በርካታ አሳሳች ምስሎችን አግኝተናል። ከዚህ በታች ያለው ቀጣዩ ምስል በሰፊው በትዊተር ተጋርቷል ነገር ግን ከአማራ ክልል አይደለም። ምስሉ በአውሮፓውያኑ 2011 በሶማሌ ክልል ከተከሰተው ድርቅ ጋር ተያይዞ በወጡ ዜናዎች ላይ መውጣቱን ተመልክተናል።


በቀጣዩም ትዊት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ምስሎች እንዲሁ አሳሳች ናቸው። በግራ በኩል ያለው ፎቶ የተወሰደው በአውሮፓውያኑ 2011 በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ በስተደቡብ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ነው። ተኝቶ የሚታየው ህፃን በባለፈው ዓመት በግንቦት ወር በትግራይ ክልል መዲና መቀለ ከሚገኝ ሆስፒታል የተወሰደ ነው።
ሦስተኛው ምስል ግን የአማራን ምስል በቅርቡ የሚያሳይ ይመስላል። የአማራ መገናኛ ብዙኃን ኮርፖሬሽን በዚህ ወር መጀመሪያ ካወጣቸው ቪዲዮዎች የተወሰደ ሲሆን በሰሜን ወሎ የተፈናቀለች ሴት መሆኗንም የምስሉ መግለጫ ያሳያል። ትዊቱ እራሱ ከ 10 ሺህ ጊዜ በላይ ተጋርቷል።

ከዚህ በታች የተመለከትነው በትዊተር ገፅ ላይ የተያያዘው ምስል ከአማራ ክልል የመጡ ሴቶች እና ሕፃናት ናቸው ይላል። ሆኖም ምስሉ መጀመሪያ ላይ የወጣው በግንቦት ወር በትግራይ ክልል በወጡ ፅሁፎች ላይ ነው። ከጦርነት ሸሽተው በመቀለ በሚገኝ ትምህርት ቤት ተጠልለው የሚገኙ ነዋሪዎችን ያሳያል።

በአማራ ክልል ውስጥ የምግብ እጥረትን ያሳያል በሚል በመጨረሻም በስፋት በትዊተር ከተጋሩት መካከል ውስጥ ቀጣዩ ምስል ነው። ነገር ግን በ1977 ከተከሰተው አስከፊ ረሃብ የተወሰደ ሲሆን ምስሉም ጥቁር እና ነጭ ነው። በዚህ ረሃብ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አልቀዋል።
