በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በትግራይ ክልል የተጀመረው እና አጎራባች ወደሆኑት አፋር እና አማራ ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት በንጹሃን ዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡ በእነዚህ ክልሎች የተለያዩ ስፍራዎች፤ በተለይም በሰሜን ወሎ እና ዋግ ህምራ አካባቢ ዜጎች መፈናቀላቸውን ተከትሎ ለከፋ የሰብአዊ ቀውስ ተዳርገዋል፡፡ አካባቢው ቀድሞም ቢሆን በተፈጥሮ አደጋ የተጎዳ እና በማገገም ላይ የነበረ መሆኑ ችግሩን በእጅጉ አባብሶታል፡፡

በሽዎች የሚቆጠሩ ህፃናት፣ አዛውንቶች እና ሴቶች እጅግ የከፋ  ቀውስ ውስጥ መሆናቸውን እና አስቸኳይ የምግብ እረዳታ እና ሌሎች የአጣዳፊ ጊዜ ድጋፎች እንደሚያስፈልጋቸው አካባቢው ላይ ካሉ ታማኝ ምንጮች መረዳት ችለናል፡፡ በተጨማሪም የህወሀት ታጣቂ ሃይል በተቆጣጠሯቸው አንዳንድ አካባቢዎች እየፈፀመው ያለው ዝርፊያ እና ንብረት ማውደም ዜጎችን በቂ ምግብ እና የህክምና እርዳታ እንዳያገኙ በማድረጉ ችግሩ እጅግ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል፡፡  ከዚህም ባለፈ ነሐሴ 26 እና 27 ቀን 2013 ዓ.ም ከ200 በላይ የሚሆኑ ንፁኃን ዜጎች በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ በታጣቂዎች መገደላቸው እና በጅምላም መቀበራቸው  መረጋገጡ ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል ሀምሌ 29/2013 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የህውሀት ቡድን በአፋር ክልል በጋሊኮማ  መንደር ውስጥ የሚኖሩ ከ240 በላይ ንጹሀን ላይ ግድያ ፈጽሟል፡፡ ከእነዚህም መካከል 107ቱ  ህጻናት ሲሆኑ ሌሎች ንጹሀንም ንብረታቸው ተዘርፏል  ቤታቸው ተቃጥሏል፡፡ በዚህም ሳብያ ከያሎ፣ ከአውራ እንዲሁም ከጋሊኮማ አካባቢዎች  በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን የተፈናቀሉ መሆኑን እና አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አንዳንድ ዘገባዎች ያስረዳሉ፡፡

በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ነዋሪዎች ጦርነቱን ሸሽተው ወደ ደሴና ሀይቅ ከተሞች፣ ሀብሩ ወረዳ እና ሌሎችም አካባቢዎች ከመምጣታቸውም ቀደም ብሎ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ተፈናቅለው ወደ እነዚህ አካባቢዎች በመምጣት ሰፍረው ይገኙ ስለነበር የተፈናቃዮቹ እና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚፈልጉትን ሰዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል።

ይህም በአካባቢው ያለውን ህይወት አድን ሥራ እና የእርዳታ አቅርቦት እጅግ ፈታኝ እንዲሆን አድርጎታል ፡፡ በዚህም የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በበቂ ምግብ እና ሕክምና እጦት የተነሳ ሕይወታቸው አሳሳቢ ወደ ሆነ ደረጃ ላይ መድረሱን ከአካባቢው የሚመጡ መረጃዎች ያሳያሉ። በመሆኑም ምንም እንኳን መንግስት በብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሚገኝ እሙን ቢሆንም እነዚህ ዜጎች ያሉበት ሁኔታ በቂ ትኩረት ካላገኘ እና አፋጣኝ የሆነ እርምጃም በመንግስት በኩል ካልተወሰደ በሰው ሕይወት ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት እጅግ የከፋ ነው የሚሆነው።

ተፈናቃዮቹ አሁን የሚገኙበት ሁኔታ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ መንግስት ከሌሎች ጉዳዮች ሁሉ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። እንዲሁም ንፁሀን ዜጎችን ከጭፍጨፋ እና ከከፋ ሰብአዊ ቀውስ የመታደግ ኃላፊነት የመንግስት ስለሆነ እነዚህን በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች በአስቸኳይ ሊታደጋቸው ይገባል።እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው የተራድኦ ድርጅቶች አስቸኳይ ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበትን ሁኔታ ሊያመቻች  እና የትብብር ጥሪ ሊያደርግ እንደሚገባ እናሳስባለን፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *