የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ቁሳቁስ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል ከገቡ በኋላ ሳይመለሱ የሚቀሩ ከባድ የጭነት ተሸከርካሪዎች ጉዳይ አሳስቦኛል አለ።
በኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት ጽህፈት ቤት በትዊተር ገጹ ላይ እንደገለጸው ባለፈው ሳምንት መቀለ ከደረሱ 149 ተሽከርካሪዎች መካከል አንዳቸውም አልተመሱም። ከሐምሌ 05/2013 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ትግራይ ክልል የእርዳታ ቁሶችን ይዘው ከገቡ 466 ከባድ የጭነት መኪኖች መካከል 38ቱ ብቻ መመለሳቸውን ድርጅቱ አስታውቋል። የተሽከርካሪዎቹ ከክልሉ አለመመለስ ያሳሰበው የመንግሥታቱ ድርጅት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚያስፈልገውን ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ የጭነት ተሽከርካሪዎቹ ያስፈልጉኛል ብሏል።
በተመሳሳይ የመንግሥታቱ ድርጅት ያጋጠመውን ከመግለጹ ቀደም ብሎ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ሐሙስ መስከረም 06/2014 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ትግራይ ከገቡ ተሸከርካሪዎች 428ቱ ከክልሉ አለመውጣቸው ገልጸዋል።በተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት አማካኝነት ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁሶችን የጫኑ 590 ከባድ ተሽከርካሪዎች ከሰመራ ወደ መቀለ መጓጓዛቸውን ቢልለኔ ተናግረዋል።
በአንድ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት አማካኝነት የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲያደርሱ ከገቡ 466 ከባድ የጭነት ተሸከርካሪዎች መካከል 428 የሚሆኑት እስካሁን ከክልሉ አለመውጣታቸውን አስረድተዋል። ቢልለኔ መግለጫቸው ከክልሉ ሳይወጡ የቀሩት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎቹ በክልሉ ውስጥ ለምን አገልግሎት እየዋሉ እንደሆነ ግልጽ ባለመሆኑ በመንግሥት ዘንድ ጥርጣሬን መፍጠሩን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የሰላም ሚኒስቴር ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ ጭነው የገቡ ተሸከርካሪዎች በተቀመጠው የአሰራር ሥርዓት መሠረት ተመልሰው መውጣት ሲገባቸው አለመመለሳቸው ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢ እና ጥርጣሬ እንዲፈጠር እንዳደረገ ገልጾ ነበር።ሚኒስቴሩ፤ “በተጨባጭ ከአላማቸው [ተሸከርካሪዎቹ] ውጪ ተሰማርተው ላለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሰጥ አካል አልተገኘም” ብሎ ነበር ጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ላይ።
ቢልለኔ ወደ ትግራይ የሚደረጉ የአየር እና የየብስ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ጉዞዎች እንደቀጠሉ መሆናቸውን አመልክተው፤ የአውሮፓ ሕብረት የሰብዓዊ እርዳታ በረራም ከአንድ ሳምንት በፊት መጀመሩን ተናግረዋል።እስከ መስከረም 04/2014 ዓ.ም. ድረስ 32 ተቋማት ለሰብዓዊ ሥራቸው 144 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ወደ መቀለ መውሰዳቸውንም ጠቅሰዋል። ከምግብ ውጪ፤ ወደ 760 ሺህ ሊትር የሚጠጋ ነዳጅ እና ከ1ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የግብርና ግብዓቶች ወደ ክልሉ መጓጓዙን አመላክተዋል።

እስከ መስከረም 4 ድረስ እንቅስቃሴያቸው ተስተጓጉሎ የቆሙ ተሸከርካሪዎች የሉም ያሉት ብልለኔ፤ መንግሥት የእርዳታ ቁሳቁሶች ወደ ክልሉ በፍጥነት እንዲገቡ ለማቀላጠፍ ሰባት የነበሩትን የፍተሻ ጣቢያዎች ወደ ሁለት ቀንሷል ብለዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ በአማራ ክልል
ቃል አቀባይዋ ጨማረውም በአማራ እና በአፋር ክልል በህወሓት አማጺያን ጥቃት ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ በርካታ ዜጎች አሉ ብለዋል።በአማራ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ500 ሺህ መሻገሩን እና አብዛኛው ሕዝብ የተፈናቀለው ከዋግ ኽምራ፣ ከሠሜን ጎንደር፣ ከደቡብ ጎንደር፣ ከሠሜን ወሎ እና ከደቡብ ወሎ መሆኑን ተናግረዋል።ከሠሜን ወሎ ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ተጠልለው የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ወደ 270ሺህ እንደሚጠጋም አመልክተዋል።
ከቀያቸው ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ለሚገኙ ዜጎች መንግሥት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን እስከ መስከረም 4/2014 ድረስ 27ሺህ ኩንታል እህል አቅርቧል። 2600 በላይ ኩንታል እህል ደግሞ በዋግ ኽምራ ዞን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ተልኳል።ይሁን እንጂ በህወሓት አማጺያን ቁጥጥር ሥር በሚገኙ የሠሜን ወሎ ወረዳዎች የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶችን ማቅረብ አልተቻለም ብለዋል ቢልለኔ።
ወትሮም ቢሆን የምግብ እጥረት ባለበት ሠሜን ወሎ፤ ህወሓት የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች እርዳታ እንዳያደርሱ እክል መሆኑ ሁኔታዎችን ያባብሳል ብለዋል።መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለትግራይ ክልል የሰጡትን ትኩረት ለአማራ እና ለአፋር ክልል ተጎጂዎችም እንዲሰጡ መንግሥት ማሳሰቡንም ተናግረዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ