በትግራይ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙ ኃይሎች ተደፍረዋል፣ ታስረዋል እንዲሁም ተገድለዋል ሲል የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች አስታወቀ።

እነዚህ ጥሰቶች የተፈፀሙት በክልሉ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር በተሰለፉት የኤርትራ ሠራዊት እንዲሁም በትግራይ ተዋጊዎች መሆኑን ድርጅቱ ተናግሯል።በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ስደተኞች በትግራይ ውስጥ በሚገኙ የስደተኛ መጠለያ ካምፖች ውስጥ ይኖራሉ። “በትግራይ ክልል በኤርትራ ስደተኞች ላይ ላይ የተፈጸመው ዘግናኝ ግድያ፣ መድፈር እና ዘረፋ ግልጽ የጦር ወንጀሎች ናቸው” በማለት የሂውማን ራይትሰ ዋች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላይቲሻ ባዴር ተናግረዋል።

ኤርትራ ስለእነዚህ የቅርብ ጊዜ ክሶች አስተያየት ባትሰጥም ነገር ግን ቀደም ሲል በሠራዊቷ ደረሰ የተባለውን ጥሰት ሁሉ አስተባብላለች። የህወሓት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው መለዮ የለበሱ ኃይሎች የትግራይ ኃይሎች በቅርቡ ወደ አካባቢው መምጣታቸውን ገልፀው ነገር ግን በአካባቢው ሚሊሻዎች ጥቃቶች ተፈፅሞ ሊሆን ይችላል በማለት ለሮይተርስ ተናግረዋል።

“የእኛ ወታደሮች ወደዚህ አካባቢ የመጡት ባለፈው ወር ነው። በቦታው በርካታ የኤርትራ ጦር ሰፍሮ ነበር። በወቅቱ የተደራጁ ቡድኖች ጥቃት አድርሰው ሊሆን ይችላል” ያሉት አቶ ጌታቸው ዓለም አቀፍ መርማሪዎች አካባቢውን ለመጎብኘት ተፈቅዶላቸዋል ብለዋል። ወደ አስራ አንደኛ ወሩ በተጠጋው የትግራይ ጦርነት ውስጥ የሚዋጉ ወታደሮች ቀደም ሲል የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፈፀም ተከሰዋል። በዚህ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል እንዲሁም የምግብ እርዳታ በመታገዱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው።

ምንጭ – ቢቢሲ