በአማራ ክልል በሕወሓት ታጣቂዎች በቁጥጥር ሥር በዋሉ የሰሜን ወሎ፣ የዋግ ህምራና የሰሜን ጎንደር አካባቢዎች በችግር ውስጥ ለሚገኙ በርካታ ዜጎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዕርዳታ እንዲያቀርቡ የአማራ ክልል ጠየቀ፡፡ ከተጠቀሱት አካባቢዎች ተፈናቅለው አንፃራዊ ሰላም ወዳለባቸው አቅራቢያ ከተሞችና በፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ መጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች በአመዛኙ ዕርዳታ እየቀረበላቸው ቢሆንም፣ በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ለሚገኙ አካባቢዎች ግን ምንም ዓይነት ዕርዳታ ለማቅረብ አለመቻሉን የአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ባሉ ከተሞች አገሪቱ እ.ኤ.አ. በ2020 በፈረመችው የካምፓላ የተፈናቃዮች ስምምነት መሠረት ተፈናቃዮች ማግኘት የሚገባቸውን የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶቹ በትግራይ ክልል እያደረጉት ባለው አግባብ ልክ ለእነዚህ አካባቢዎች ተገቢውን ዕርዳታ ማድረግ እንዳለባቸው ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ በአማራ ክልል በአጠቃላይ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች እንዳሉ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ከ550 ሺሕ በላይ የሚሆኑት በሕወሓት ታጣቂዎች አማካይነት ከሰሜን ወሎ፣ ከዋግ ህምራና ከሰሜን ጎንደር አካባቢዎች የተፈናቀሉ መሆናቸውን አቶ እያሱ ገልጸዋል፡፡

በተጠቀሱት አካባቢዎች ያሉ ዜጎች ሀብትና ንብረት መዘረፉን፣ መውደሙን፣ እንዲሁም መጀመርያ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት የደሃ ደሃ ተብለው የሴፍቲኔት ዕርዳታ ያገኙ የነበሩ ዜጎች ቁጥር በርካታ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ችግሩን የባሰ እንዳደረገው አክለዋል፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት ከዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ጋር የዕርዳታ ድጋፍ በሚደርስበት ሁኔታ ላይ ውይይት ማድረጉን የገለጹት ኃላፊው፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ ድርጅቶቹ ሥራ መጀመራቸውን ለማየት እየጠበቅን ነው፤›› ብለዋል፡፡ የተከሰተው ችግር ወደ የከፋ የረሃብ አደጋ ሳይለወጥ ድርጅቶቹ ዕገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የደቡብ ወሎ ቅርንጫፍ የአደጋ ሥጋት ቅነሳ ክፍል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን ዘውዴ በበኩላቸው፣ በሕወሓት ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ለሚገኙ አካባቢዎች በቀይ መስቀል በኩል ምንም ዓይነት ድጋፍ ማድረግ አለመቻሉንና ለአብነትም በታጣቂዎች ሥር ባለው ወልዲያ ከተማ ድጋፍ ለማድረስ ሲፈለግ፣ ወደ ከተማው ለመድረስ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ብቻ በመሄድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ስለሆነም ለሚፈጠሩ ችግሮች ኃላፊነት ሊወስድ የሚችል አካል ባለመኖሩና ከዚህ በፊት በቆቦ ከተማ አንድ የቀይ መስቀል አምቡላንስ በመዘረፉ ምክንያት፣ የጦር ቀጣና ውስጥ ገብቶ አስፈላጊውን ዕርዳታ ለማድረግ ከባድ እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን አቶ ደበበ ዘውዴ ለሰሜን ወሎ፣ ለሰሜን ጎንደር፣ ለዋግ ህምራና ለአፋር አካባቢዎች ከዕርዳታ ድርጅቶች ጋር በመሆን በክልሎቹ እየተጠየቀ ያለው ዕርዳታ ለተፈናቃዮች እየቀረበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *