ክፍል ሰባት ፥ የዘገባ ጥቆማዎች

7.2 የግጭት ተጎጂዎችን ቃለ መጠይቅ ማድረግ

በዚህ ማጣቀሻ ውስጥ እስካሁን ከተወያየንባቸው ነገሮች ቃለ መጠይቅ የግጭት አገናዛቢ ዘገባ አስኳል መሆኑ ግልጽ መሆን አለበት። በግጭቱ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸውን አካላት ባሕሪይ ያለ ጥርጥር መግለጽ አለብን፤ ሆኖም እውነተኛ ፍላጎቶቻቸውን፣ ጥቅሞቻቸውን እና ይህ ነገር ለነርሱ የዚህን ያህል ያስፈለጋቸው ለምን እንደሆነ የምንረዳው ስናገኛቸው ነው። በተመሳሳይ፣ ከንግግሮቻቸው ውስጥ ያለውን ድብቅ መልዕክት መረዳት ስንችል ነው ቡድኖቹ ግጭት ውስጥ ለምን እንደገቡ፣ ፍራቻቸው ምን እንደሆነ እና እንዴት ሊቀረፉ እንደሚችሉ የምንገነዘበው።

ግጭት አገናዛቢ ዘገባ መድረኩ ላይ ከሚታዩት ሰዎች ውጪም ያሉትን ሰዎች ማናገር ይጠይቃል። ግጭት ውስጥ የገቡ አካላትን መሪዎችን ከሌሎች የተለያዩ ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለ ድርሻ አካላት እና የሰላም አስከባሪና ፈጣሪ አካላት ጋር ማነጋገር ይጠበቅብናል። በግጭቱ ውጤት ላይ በጣም አናሳ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ነገር ግን ብዙ የሚያጡ እና የሚከስሩ አካላትንም ማናገር አለብን። በዚህ ክፍል፣ በአርትኦት ቡድኑ የወል ዕውቀት ላይ ተመሥርተን አንዳንድ ልምድ አፈራሽ ጉርሻዎችን በግጭት የተጎዱ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ ስለማድረግ እናጋራችኋለን።

የግጭት አገናዛቢ ቃለ መጠይቅ ጥቂት ጥቅል ጉርሻዎች

  • ጥያቄዎችን በአሸናፊዎች እና ተሸናፊዎች አትቅረጿቸው። ስለ ግብ፣ ዓላማ እና ስልቶች በግጭት ውስጥ ያሉ አካላትን ስትጠይቁ ከዜሮ-ድምር ሐሳቦች ራቁ። ጥያቄዎችን የምንቀርፅበት መንገድ ሰዎች መልስ የሚሰጡበትን መንገድ ይቀይረዋል። “እርስዎን ለማስደሰት ምን ይደረግ?” ብሎ መጠየቅ፣ “ሁሉንም ወገን በሚያስደስት መልኩ ይህ ግጭት እንዴት ሊፈታ ይችላል?” ብሎ ከመጠየቅ ይለያል። የመጀመሪያው ዜሮ ድምር መልስ ያመጣል። የኋለኛው ደግሞ ሰዎችን ሰፋ አድርገው እንዲያስቡ ይጋብዛል። ሁለቱም ፍትሐዊ ጥያቄዎች ናቸው፤ ነገር ግን ሁለተኛው ገንቢ መልስ መስጠት ያስችላል።
  • ተጠያቂዎቹ ሌሎኞቹንም ወገኖች በመልሶቻቸው እንዲያስቡ አበረታቷቸው። ቡድኖቹ ፍላጎታቸውን እና ጥቅማቸውን ብቻ እንዲገልጹ ከመጠየቅ ይልቅ፣ ከአቋም ባሻገር መልስ ለማግኘት መሞከር አለብን። ቡድኖቹ የተቀናቃኞቻቸውን ፍላጎቶችና ጥቅሞችም እንዴት እንደሚመለከቷቸው መጠየቅ አለብን።
  • ተጠያቂዎችን መተቸት የኛ ሥራ አይደለም፣ ሆኖም እነዚህ ቡድኖች የኛን መድረክ ተጠቅመው ግጭቶችን እንዲቆሰቁሱ እና ሌሎችን እንዲያጠቁ መፍቀድ የለብንም። ስድቦችን እና ቆስቋሽ ንግግሮችን ሲናገሩ ለንግግራቸው ኃላፊነት እንዲወስዱ ተከታይ ጥያቄ ማቅረብ ጥሩ ነው። ለምሳሌ፣ ለዚህ ንግግርዎ ከሌላኛው ወገን ምን ዓይነት ምላሽ ይጠብቃሉ? ሌላኛውን ወገን በመስደብ ሊያተርፉ የሚችሉት ግብ ምንድን ነው
  • ቆፍጠን ይበሉ። ግጭት አገናዛቢ መሆን ጋዜጠኞችን በተጠያቂዎቻቸው ላይ የተለሳለሱ አያደርጋቸውም። ለምሳሌ ያክል ተጠያቂዎች እውነት ያልሆኑ ወይም የተጋነኑ ነገሮችን እየተናገሩ ከሆነ ልንሞግታቸው ይገባል። በተመሳሳይ ጥያቄዎቻቸው ወይም ቃል የሚገቡት ነገር ከእውነታው የራቀ ከሆነ፣ ይህ ተግባራዊ ይሆናል ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።
  • በደንብ እያደመጣችሁ  የተናገሩትን  መልሳችሁ  ድገሙላቸው።  በግጭት  ውስጥ  ያሉ ሰዎች የተናገሩትን ነገር አዛብተን ማቅረብ አይገባንም።  ንግግሮችን በትክክል ማጣቀሳችን የሚያስፈልጋቸው ነፍሶች  አሉ።  ምንጫችሁ  የሚነግራችሁን  ነገር  በማረጋገጣችሁ የሚጎድልባችሁ ምንም ነገር የለም። ለምሳሌ ያክል የተጠያቂውን አቋም “አቋምዎ ‘ሀለሐ’ ነው ብዬ ብል ትክክል ነኝ?” ብላችሁ ማረጋገጥ ትችላላችሁ።
  • ለቃለ መጠይቅ በቂ የምርምር ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለባችሁ። ሆኖም የማታውቁት ነገር ከገጠማችሁ አምናችሁ ማብራሪያ መጠየቅ ይጠቅማችኋል። የሁሉንም ሰወው ሐሳብ ግልጽ ማድረግ የእርስዎ ፍላጎት መሆኑን ግልጽ በማድረግ ከተጠያቂዎቻችሁ ማብራሪያ ለመጠየቅ በፍፁም አታመንቱ።
  • ተጠያቂው መልዕክታቸውን  ለመማስተላለፍ  ምርጥ  አጋጣሚ እንደተፈጠረላቸው እንዲሰማቸው አድርጉ። በመድረካችሁ የምታስተላልፉት መልዕክት ተጠያቂው የተናገሩትን መሆኑን እንዲረጋገጥ አድርጉ። ሰዎቹ የሚናገሩትን ነገር አዛብታችሁ ካቀረባችሁ ግጭቶችን እያባባሳችሁ ወይም እያራዘማችሁ መሆኑን ተረዱ።
  • ተናጋሪዎቹን ሐሳብ አትስጧቸው። “እንዲህ፣ እንዲህ ይላሉ እንዴ…?” የመሳሰሉ ተጠያቂዎቹ እንዲናገሩላችሁ የምትፈልጉትን ነገር የሚያናግሩ ጥያቄዎችን አትጠቀሙ። ይልቁንም ሰዓት ወስዳችሁ በትዕግስት አድምጧቸው። ራሳቸውን በራሳቸው ቋንቋ እንዲገልጹ አድርጓቸው።
  • አድሎ የሌለበት አቀራረብ ቅረቧቸው። ለነርሱ አዛኝ መስላችሁ አትቅረቡ፤ ሁሉም የሚሉትን ለመስማት መዘጋጀታችሁን ብቻ ግልጽ አድርጉ።
  • እንደ ጋዜጠኝነታችን አስተያየታቸው ወይም ርዕዮተ ዓለማቸው ለእኛ በጣም የሚያናድድ የሆኑ ሰዎች ጋር ልንነጋር እንችላለን። በዚህ ጊዜ፣ የእናንተ ባሕሪ ቃለ መጠይቁን ምን ዓይነት ተፅዕኖ ሊያሳድርበት እንደሚችል ለማሰብ ጊዜ ውሰዱ። ለተጠያቂው የመደመጥ ዕድል ካልሰጣችሁ በቀር፣ ግጭቱን በመቅረፍ ረገድ ምንም ገንቢ አስተዋፅዖ እንደማይኖራችሁ አስተውሉ።

በግጭቱ የተጎዱ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ  ማድረግ

  • በግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች እያለፉበት ያለውን ስሜት የተረዳችሁ ለመምሰል አትሞክሩ። ቃለ መጠይቁን ቀስ በቀስ በማስኬድ ተጠያቂው ታሪካቸውን እንዲናገሩ አድርጉ። አዘኔታችሁን ማሳየት ችግር የለውም፣ ይህ ግን ለአንዱ ወገን ታደላላችሁ ማለት አይደለም። ሰዎቹ ቀስ በቀስ ግልጽ እንዲሆኑ አድርጓቸው፣ ሰዎቹ እናንተ አስባችሁት የማታውቁትን ነገር በማየታቸው ወይም በማሳለፋቸው ክብር ይኑራችሁ።
  • ጥያቄዎቹን ረጋ ብላችሁ ጀምሩ እና ተጠያቂዎቹ ከባድ ጥያቄ መጠየቅ ከመጀመራችሁ በፊት ምቾት እንዲሰማቸው አድርጉ። ሰዎቹ ቃለ መጠይቁን ጥሩ አድርገው እየሰጡ እንደሆነ እንዲያውቁ አድርጓቸው። ምን ያህል ሊነግሯችሁ እንደሚፈልጉ መወሰን የነርሱ ድርሻ ነው። አወጣጭ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይረዳል፣ ነገር ግን ለተጠያቂዎቹ ስሜታዊ ፍላጎት መጠንቀቅም ያስፈልጋል።  ተጠያቂዎቹ ስሜታዊነት በሚሰማቸው ግዜ ለአንደ፣ ሁለት ቅፅበት በዝምታ መጠበቅ ይረዳል።
  • ክፍት መጨረሻ ያላቸውን ጥያቄዎች መጠየቅ ተጠያቂዎቹ ታሪካቸውን በራሳቸው ቋንቋ እንዲገልጹ ያደርጋቸዋል። “አዎ” ወይም “አይ” የሚሉ መልሶች ያሏቸው ጥያቄዎች ተጠያቂዎቹን በማናገር ፈንታ ጋዜጠኞቹን ብዙ እንዲያስቡ ያስገድዳል።
  • ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች አንደ ለአንድ መጠየቅ የተሻለ ነው። ነገር ግን ሁሉም እንደዛ መሆን የለበትም። አንዳንዴ ተጠያቂዎቹ ሌላም በጎደለ የሚያሟላላቸው ሰው አብሮ መጠየቁን ሊፈልጉት ይችላሉ።  እንደዚህ ዓይነት ቃለ መጠይቆችን ከማድረጋችን በፊት ተጠያቂዎቹ እንዳይደብራቸው ፈቃደኛ መሆናቸውን መጠየቅ ይኖርብናል።
  • የቡድን ቃለ መጠይቆች በሚደረጉበት ሰዓት ያልተጠበቁ ነገሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ዕወቁ። በቡድን የሚደረጉ ቃለ መጠይቆች ላይ ተጠያቂዎቹ ካልተስማሙና እርስ በርስ ንትርክ ውስጥ ከገቡ ቃለ መጠይቅ ማድረግ በጣም ያስቸግራል።
  • ተጠያቂዎቹ የሚናገሩት ነገር በመገናኛ ብዙኃን እንደሚወጣና ሰዎቹ በሥም ለመገለጽ ፈቃደኛ መሆን አለመሆናቸውን በጥብቅ አረጋግጡ።
  • ተናጋሪው የሚሉትን መረዳታችሁን አረጋግጡ። ከቃለ መጠይቁ በኋላ በዘገባችሁ የምታካትቱት የሚመስላችሁን ነጥቦች በማንሳት በትክክል ተረድታችኋቸው እንደሆነ አረጋግጡ። ተናጋሪው ቁልፍ ነገር ዘንግተዋል ብለው ያስቡ እንደሆነ እና እንዳልሆነ ማረጋገጡም ጠቃሚ ነው።
  • በስሜት ተዘጋጁ። ጋዜጠኞች በጊዜ ሒደት እየበረቱ ይሔዳሉ፣ ሆኖም አንዳንድ ቃለ መጠይቆች ወይም ተጠያቂዎች ስሜታችንን በጥልቅ ሊነኩት ይችላሉ። ለዚህ ስሜታዊነት በንቃት መዘጋጀት እና ሲገጥመን ምን ማድረግ እንዳለብን ማወቅ አለብን።.
  • የማትችሉትን ቃል በፍፁም አትግቡ። የመጨረሻ ልናደርግ የምንችለው ነገር ታሪካቸውን በትክክል መናገር እና ተደራሲያን ምን እንደደረሰባቸው እና በምን ዓይነት ፈተና ውስጥ እያለፉ እንደሆነ እንዲረዱላቸው ማድረግ ነው። ዘገባችን ለውጥ ወይም ዓለም ዐቀፍ ድጋፍ ያመጣል ብለን ቃል መግባት አንችልም። ብዙዎቻችን መገናኛ ብዙኃኖቻችን ራሳቸው ይህንን ዘገባችንን እንደሚቀበሉን እርግጠኛ መሆን አንችልም።
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *