ወደ አስራ አንደኛ ወሩ እየተሻገረ ያለው ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ከመዛመቱ ጋር ተያይዞ በአፍሪካ ቀንድ የመዛመት አደጋን ደቅኗል ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሸል ባችሌት በትናንትናው ዕለት አስጠነቀቁ።

ኮሚሽነሯ በትግራይ ክልል ስላለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታን በተመለከተ ጄኔቫ ላይ በነበረው 48ኛው የድርጅቱ የሰብዓዊ መብቶች ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ነው ይህንን የተናገሩት። በትግራይ ክልል የተነሳው ጦርነት ወደ አጎራባቾቹ አፋርና አማራ ክልሎች መዛመቱና በአገሪቱ ካለው የእርስ በርስ ግጭቶች ጋር ተዳምሮ በአፍሪካ ቀንድ እንዳይስፋፋ ስጋት እንዳለ አስታውቀዋል። ኮሚሽነሯ ባለፉት ጥቂት ወራት እየተፈጸሙ ያሉ ሁኔታዎችን ባስረዱበት ወቅት በትግራይ ተወላጆች ላይ የጅምላ እስር፣ ግድያ፣ ስልታዊ ዝርፊያ እና ወሲባዊ ጥቃቶች ቀጥለዋል ብለዋል።

ይህም ሁኔታ በነዋሪዎቹ ላይ የፍርሃት ድባብ እንደፈጠረባቸውና በርካቶችንም በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲፈናቀሉ አድርጓቸዋል ብለዋል። በሲቪል ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ መጠነ ሰፊ ነው ያሉት ኮሚሽነሯ ሥርዓት አልበኝነትም ሰፍኗል በማለት ተናግረዋል። ከጦርነቱም ጋር መስፋፋትና መዛመት በርካታ የሰብዓዊ መብትና የተፈናቃዮችን መብት ጥሰቶች በሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት እየደረሱ እንደሆነ የሚያመለክቱ በርካታና አስከፊ ሪፖርቶች ደርሰውናል ብለዋል።

የተመድና ኢሰመኮ የጋራ ምርመራ

ኮሚሽነሯ በዚህ ወቅትም የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋር በጥምረት በትግራይ ውስጥ ስለደረሱ የሰብዓዊ መብቶች እና የጦርነት ሕግጋት ጥሰቶች ምርመራን በተመለከተ የደረሱበትን አብራርተዋል። የመጀመሪያዎቹ ሁለት የመስክ ሥራዎች በታቀደው መሰረት ወደ መቀለ፣ ምሥራቅ እና ደቡብ ትግራይ መጓዝ መቻሉን ሆኖም በመቶዎች በሚቆጠሩ ነዋሪዎች አስከፊ ጭፍጨፋ ተፈፅሞባታል ወደተባለችው የአክሱም ከተማ ቡድኑ መሰማራት አልቻለም ብለዋል። ከአክሱም በተጨማሪ ወደ ምሥራቅ እና ማዕከላዊ ትግራይ ተይዞ የነበረው ጉዞ ያልተሳካ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ቡድኑ በማካይድራ የነበረውን ቆይታ ማሳጠር እንደነበረበት አስረድተዋል።

ኮሚሽነሯ ለዚህም እንደ ምክንያትነት ያስቀመጡት በጸጥታው ሁኔታ በተፈጠረው ድንገተኛ ለውጥና የጦርነቱም መልክ በመለወጡ ነው ብለዋል። የጋራ ሪፖርቱ ከግኝቶቹ እና አስተያየቶቹ ጋር ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ እንደሚወጣ እንደሚጠበቅም ተገልጿል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው ለጉባኤው ባደረጉት ንግግር በአሁኑ ወቅት ጥምር ቡድኑ የሰበሰበውን መረጃ በማጠናቀርና በመተንተን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ሁለቱም ተቋማት በተፈራረሟቸው የመግባቢያ ሰነዶች መሰረት አሁን በዚህ ደረጃ ምንም አይነት ውጤት ይፋ እንደማይደረግ ተናግረዋል።

ኮሚሽነሯም በዚሁ ወቅት በሪፖርቱ እየመረመሯቸው ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አስረድተዋል። በክልሉ በርካታ በንፁሃን ላይ የደረሱ ጭፍጨፋዎች፣ ያለ ፍርድ ግድያ፣ ማሰቃየቶችና ስወራን ጨምሮ አስከፊ ጥሰቶች ለመፈጸማቸው ግልፅ ያሉ መረጃዎች አሉ ብለዋል። በዚህ ጦርነት ላይ ወሲባዊና ፆታዊ ጥቃቶች በአሰቃቂ ጭካኔ የተሞሉ እንደሆኑም መረጃዎች ተለይተዋል። በደቦ የሚደረግ መደፈርን ጨምሮ፣ በብሔር ላይ ያነጣጠረ ወሲባዊ ጥቃት፣ ባርነትና ሌሎች ግፎች መፈፀማቸውም ተመዝግበዋል ብለዋል። ኮሚሽነሯ የኢትዮጵያ መንግሥት ወሲባዊ ጥቃቶችን የተፈጸሙ ሰዎችን ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ ያለውን ተግባር እውቅና ሰጥተው ስለተወሰዱ እርምጃዎችም ለመስማት እጠብቃለሁ ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ ሐሳባቸውን ለካውንስሉ አባላት በንግግር ያካፈሉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የተባበሩትን መንግሥታት ሰብአዊ መብት ቢሮና በኢትዯጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በጥምረት እየተደረገ ያለውን ምርመራ መንግሥታቸው ዋጋ እንደሚሰጠው ጠቅሰው ነገር ግን የመጨረሻ ሪፖርቱ ሲወጣ የተሟላ የሚባል እንደማይሆን አመላክተዋል። “ምርመራ እንዲደረግበት የተወሰነው የጊዜ መስኮት መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት እስካወጀበት ጊዜ የሚይዘውን ነው። ይህም ማለት በአፋርና በአማራ ክልል በህወሓት የተፈጸሙ አሰቃቂ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ልጆችን በውትድርና ማሳተፍ፣ በጋሊኮማና ጨና የተፈጸሙትን በሙሉ የሪፖርቱ አካል አይደረጉም። ይህም የጥምረቱን ውጤን ያልተሟላ ያደርገዋል” ብለዋል።

ዶ/ር ጌዲዮን የጥምረቱን ጥረት ካደነቁና መንግሥታቸው የሚደግፈው መሆኑን ካወሱ በኋላ የተለመዱ አሰራሮችን ገድፏል ያሉትን የአፍሪካ ሕብረት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ወቅሰዋል። “ከተለመደው አሰራር ባፈነገጠ መልኩ የአፍሪካ ኮሚሽን ነጻና ገለልተኛ ባልሆነ ሁኔታ የራሱን የተናጥል ምርመራ ለማካሄድ መርጧል። ይህ በኢትዮጵያ መንግሥት ተቀባይነት አይኖረውም” ብለዋል።

ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)

ኮሚሽነሯ በተጨማሪ ምን አሉ?

ኮሚሽነሯ በክልሉ በቅርቡ እየተፈፀሙ ነው ስለተባሉ ጉዳዮችም ለጉባኤው ማብራሪያ ሰጥተዋል። የመንግሥት ኃይሎችና አጋሮቻቸው በርካታ ጥሰቶችን በመፈጸማቸው ቀጥለዋል የሚሉ ሪፖርቶች እየወጡ እንደሆነ ጠቁመው በቅርቡም የሚረብሹ ሪፖርቶች ደርሰውናል ብለዋል። በርካታ አስከሬኖች በምዕራብ ትግራይና በሱዳን መካከል በሚሻገረው ወንዝ ዳር በአካባቢው አሳ አጥማጆች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል። አንዳንዶቹ በጥይት የቆሰሉና እጃቸው ወደኋላ ተጠፍረው የታሰሩ መሆናቸውን ገልጸው ይህም ከመገደላቸው በፊት ስቃይና እንግልት እንደደረሰባቸው አመላካች ነው ብለዋል።

በምዕራብ ትግራይ ይፋ ባልተደረጉ ስፍራዎች መጠነ ሰፊ የሆነ የዘፈቀደ እስራት በትግራይ ተወላጆች ላይ እየተፈፀመ መሆኑንም አውስተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ የትግራይ ተወላጆች በብሔራቸው እየተለዩ በፀጥታ ኃይሎች ለእስር መዳረጋቸውን ጠቅሰዋል። ከነዚህም ውስጥ በመቶዎች የሚሆኑት በቅርቡ በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በርካታ የንግድ ስፍራዎቻቸውም መዘጋታቸው መረጃዎች ደርሰውናል ብለዋል።

ከሰሞኑም ኢሰመኮ በአዲስ አበባ በወንጀል ጉዳይ ተጠርጥረዋል በሚል በቁጥጥር ስር ስለዋሉ የትግራይ ተወላጆች እና የንግድ ቤቶች መዘጋት በርካታ አቤቱታዎች ደርሰውኛል ብሏል። በቁጥጥር ስር ያሉት የትግራይ ተወላጆች የተወሰኑት በአዲስ አበባ ከተማ እና አፋር ክልል ወደሚገኙ ወታደራዊና የፖሊስ ካምፖች መወሰዳቸውንና ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከጠበቆቻቸው ጋር ያልተገናኙና ፍርድ ቤትም ያልቀረቡ እንዳሉ ለማወቅ እንደቻለም ገልጿል። በትግራይ ተወላጆች ላይ በተጨማሪ በጥላቻ እና በአድሏዊነት የተሞሉ ትርክቶች መሰማታቸውን መቀጠላቸው ገልጸው እንዲህ አይነት ትርክቶች ምን አይነት አደጋ ሊያስከትሉ እንደሚችሉም ከታሪክ ልንማር እንደሚገባም አሳስበዋል።

በትግራይ ከልል ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈፅመዋል ለተባሉትም የኤርትራ ሠራዊትም ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጥሪያቸውን ለኤርትራ መንግሥት አቅርበዋል። ኮሚሽነሯ በተጨማሪ የትግራይ ኃይሎች ወደ አጎራባቾቹ ክልሎች መግባታቸውን ተከትሎ የሰብብዓዊ መብት ጥሰቶች አድርሰዋል የሚሉ ሪፖርቶች አንደደረሳቸው ለጉባኤው አስረድተዋል። የትግራይ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እንዲሁም ለተፈፀሙ ግድያዎች ተጠያቂ ናቸው ተብሏል። በተዛመተው ጦርነት ምክንያት ከአማራ ክልል 76 ሺህ 500 የተፈናቀሉ ሲሆን ከአፋር ክልል ደግሞ ወደ 200 ሺህ ተፈናቅለዋል።

በቅርቡም በነበረው ግጭት 200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከነዚህም ህፃናት ይገኙበታል ተብሏል። በሐምሌ ወር መጨረሻ በአፋር ክልል ጋሊኮማ ቀበሌ የትግራይ ኃይሎች በአብዛኛው ሴቶች፣ ህፃናትና የእድሜ ባለፀጎች በሚገኙበት የመጠለያ ካምፕ ጥቃትና ግድያ ስለመፈፀማቸው ሪፖርት ተደርጓል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም አቀፉ ሕግ ዘንድ የተከለከለ በትግራይ ኃይሎች ዘንድ ህፃናትን ለጦርነት የመመልመል ተግባር በስፋት ሪፖርቶችም እንደደረሳቸው ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ በቅርብ ጊዜ ስለተከሰቱት ሁኔታዎች

ኮሚሽነሩም የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም  ካወጀ በኋላ በክልሉ ያሉ የሰብዓዊ መብትና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችንና የቅርብ ጊዜ ለውጦችን አስረድተዋል። በወቅቱ የነበረው የተኩስ አቁምና የወታደራዊ ሁኔታው መገታት ለሰብዓዊ እርዳታ መሻሻልና የሰላምን መንገድ በማመልከት ተስፋን ፈንጥቆ ነበር ብለዋል። በዚያን ወቅት ስለነበረው የሰብዓዊ ሁኔታ ተደራሽነትም ሲያስረዱ በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻልን ያሳየ ነበር ያሉ ሲሆን “75 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የእርዳታ ሥራዎች በሚከናወኑባቸው [አካባቢዎች] ውስጥ ይኖሩ ነበር” ብለዋል።

ነገር ግን ከሦስት ሳምንት ባላነሰ ጊዜ ወቅት ጉልህ ተግዳሮቶች ተከሰቱ ብለዋል ኮሚሽነሩ። ኮሚሽነሩ እንደ ተግዳሮትም የሚያነሱት ህወሓት የተኩስ አቁሙን ለመቀበል ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጡና በአጎራባች ክልልሎች ላይ ወታደራዊ ጥቃት ጀምሯል በማለት ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ የእርዳታ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸውን ጠቅሰዋል። በአጎራባች ክልሎች ውስጥ ያሉ ኃይሎችን ማሰባሰብ ጀምሮ ለጦርነቱ ብሔራዊ ስምሪት እንዲሁም ወታደራዊ አጸፋ መሰጠት ተጀመረ ይላሉ።

ከጦርነቱ መባባስ ጋር ተያይዞም የግንኙነት መስመሮችን ጨምሮ ሌሎች የሕዝብ መሰረታዊ አገልግሎቶች እንደሚጎዱ ግልፅ መሆኑንም አስምረዋል። ስለዚህ በባለፉት ወራት የተከሰተውን የጦርነት መስፋፋትም አንስተው የትግራይ ግጭት የሚለው የተሳሳተ ስም ሆኗል ይላሉ። በአጎራባቾቹ አፋር እና አማራ ክልሎች ጦርነቱ ገብቷል፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን በመጥቀስ ይህም በትግራይና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ መፈናቀልን ጨምሮ ችግሩን ተደራራቢ አድርጎታል ይላሉ። እነዚህ ወታደራዊ ውጊያዎች በሲቪሎች፣ በትራንስፖርትና፣ በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የክረምት ወቅትና አርሶ አደሩ ምርት የሚያመርትበት ወቅት ቢሆንም ከሚጠበቀው አንፃር የምጣኔ ሀብቱ መስተጓጉሉንም አስረድተዋል። ዶ/ር ዳንኤል ከዚህ ጨምረው እንደገለጹት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የነገሮችን ውስብስብነት ለመረዳት እንዲሞክርም አስገንዝበዋል። “የሸንጎው አባላት ልብ ልትሉት የሚገባው በእነዚህ ግጭቶች የሚታየው የሰብአዊ መብት ሁኔታ እንደሚታሰበው ጥቁርና ነጭ አለመሆኑን ነው። እጅግ የተወሳሰበና በግጭቱ የሚሳተፉ ሁሉም አካላት ወታደሮቻቸውና ደጋፊዎቻቸው በሰብአዊ መብት ጥሰትና ቁሳዊ ውድመት እጃቸው እንዳለበት መረጃዎች አሉ። ይህም የወሲብ ጥቃትና ልጆችን በውትድርና መልምሎ ማሳተፍ ወንጀልን ይጨምራል” ብለዋል።

የተቀመጡ መፍትሄዎች

ኮሚሽነሩ በዚህ ንግግራቸው ወቅት የአገሪቷ ብሔራዊ፣ ሕጋዊ እና ተቋማት ሲለኩ ፍፁም ባይባሉም በሁሉም መልኩ የአገሪቱን ሰብአዊ መብት ቀውስን ለመፍታት እና የጦርነቱን ዘላቂነትን መፍትሄ ለማበጀትና እንደሚችሉም በግጭቱ ውስጥ ያሉ ወገኖችም ሆኑ ዓለም አቀፍ አጋሮች ይህንን ሊረዱት እንደሚገባም አሳስበዋል። በአሁኑ ወቅት አዝጋሚ ቢሆንም ሁለቱም ወገኖች ወደ ድርድር መዞርና እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የቀረቡ አንዳንድ ተነሳሽነቶች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው ሆኖም የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ቀውስ ለመፍታት የሚሞክሩት ዓለም አቀፍ አጋሮች ትርጉም ያለው እና ገንቢ ሚና እንዲኖራቸው ከፈለጉ ሁልጊዜ የዚህን ውስብስብ የፖለቲካ ቀውስ ታሪክ እና አውድ ሙሉ ግንዛቤ ይዘው መስራት እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል። “የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና የዚህ ምክር ቤት አባላት ሊገነዘቡ የሚገባው በዚህ ሁሉ ምስቅልቅል የመጀመርያ ተጎጂዎቹ የኢትዮጵያውያን ናቸው። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትርጉም ያለውና ገንቢ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችለው የዚህን ቀውስ ታሪክና አውዱን መረዳት ሲችሉ ነው” በማለት ዶ/ር ዳንኤል ተናግረዋል።

ሚሸልል ባችሌት በበኩላቸው በክልሉ አጠቃላይ ያለው የቴሌኮምዩኒኬሽንና ኢንተርኔት እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን መቋረጥ አስታውሰው፤ አሁንም ቢሆን የዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ብሔራዊ የሰብዓዊ መብትና እርዳታ አካሎች ያልተገደበ ተደራሽነት ሊኖራቸው ይገባል በማለት አስረድተዋል። ከትግራይ ባሻገር ያለውን የእርስ በርስ ግጭት ለማስቆም ተጨማሪ ጥረት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ምላሹ ወታደራዊ ሊሆን አይችልምም ብለዋል። በትግራይ ለተፈጠረው ግጭት መፍትሔው ሊገኝ የሚችለው በፖለቲካ ሂደትና ውይይት ብቻ ነው በማለትም ሁሉም ወገኖች ግጭቶችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲያቆሙ እና ለዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደራደሩ ጥሪያቸውን እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል።

ዘላቂ ሰላም የሚመጣው በተጠያቂነት፣ በእውነተኛ አካታች ውይይት እና በብሔራዊ እርቅ ሂደት ብቻ መሆኑን ጠቁመው በዚህ ረገድ የአፍሪካ ሕብረት የሽምግልና ጥረቶችን እንደሚያደንቁ አስረድተዋል። “ኢትዮጵያ የምትበታተንበትን ሁኔታ ለማስወገድ ትርጉም ባለው የሰላም ግንባታ እና የእርቅ ጥረቶች ቅሬታዎች መፈታት አለባቸው፣ ይህም ለአገሪቱ እና ለተቀረው የአፍሪካ ቀንድ ጥልቅ ትርጉም አለው” ብለዋል። “በመንግሥትና በሕዝቦቹ መካከል ያለውን ማኅበራዊ ውል ለማደስ በየአቅጣጫው የበለጠ ተጨባጭ ጥረቶች መደረግ አለባቸው። ኢትዮጵያውያኑ መሠረታዊ መብቶቻቸውን እና ነፃነቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ ለመደሰት የሚችሉት ይህ አንዴ ከተገኘ ብቻ ነው” በማለትም አክለዋል።