በኢትዮጵያ የቅርብ ዓመታት ታሪክ ውስጥ በአገር ውስጥ ጉዳይ እና በውጪ ጫናዎች እጅግ ፈታኝ ሊባል የሚችለው ዓመትን አሳልፋለች።
በህወሓት እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል የተጀመረው ጦርነት እና ተከትሎ የመጣው ሰብዓዊ ቀውስ፣ የረሃብ አደጋ፣ የንጹኀን ዜጎች ግድያ፣ የሕዳሴ ግድብ ድርድር፣ ከሱዳን ጋር የተገባው የድንበር ይገባኛል ውዝግብ፣ አገራዊ ምርጫ እና ‘ኦነግ ሸኔ’ የኢትዮጵያ የ2013 ዋና አጀንዳዎች ነበሩ።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት
ከ10 ወራት በፊት በፌደራሉ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስን አስከትሏል። በዚህም የተነሳ በሺዎቹ የሚቆጠሩ ዜጎች ሞተዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ለረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል። በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ቁጥራቸው በውል በማይታወቁት ላይ ደግሞ የተለያየ መጠን እና ዓይነት ያላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል።

የህወሓት አማጺያን በአገር መከላከያ ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንሰትር ዐቢይ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው መከላከያው በህወሓት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ማዘዛቸውን ተናገሩ። ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰላም ኖቤል ሽልማት ከወሰዱ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ ጦርነት ገቡ ተብለው በምዕራባውያን ተብጠለጠሉ። ግጭቱም በአስቸኳይ እንዲቆም አገራት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድምጻቸውን ማሰማት ጀመሩ።
ኢትዮጵያ ግን “የሕግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃ” ባለችው ወታደራዊ እርምጃ ፀንታ ቀጠለች። የኤርትራን ሠራዊት ከጎኑ ያሰለፈው የፌደራሉ መንግሥት፣ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የትግራይ መዲናን መቀለን መቆጣጠር ቻለ። ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ዘመቻው ተጠናቀቀ አለ።
ከመቀለ ወጥተው በረሃ የወረዱ የህወሓት ኃይሎች ግን መከላከያን መፋለም ቀጠሉ። በዚህ መካከል የፌደራሉ መንግሥት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን መስርቶ ክልሉን ለማስተዳደር ያደረገው ጥረት የተፈለገውን ውጤት ሳያመጣ ቀረ።

ከወራት ቆይታ በኋላ መንግሥት ሳይጠበቅ የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ የትግራይ ክልል አካባቢዎችን ጥሎ ወጣ። መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ያደረገው አርሶ አደሩ የእርሻ ስራውን እንዲያከናውን እንዲሁም የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ እድል ለመስጠት መሆኑን በወቅቱ ገልጾ ነበር። የፌደራሉ መንግሥት ከትግራይ መውጣትን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች ባካሄዷቸው ዘመቻዎች ከክልሉ አልፎ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ተሻግረው የተለያዩ ስፍራዎችን መቆጣጠር ችለዋል።
አማጺ ቡድኑ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ዘልቀው መግባታቸውን ተከትሎ፣ ሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ልዩ ኃይሎቻቸውን በመላክ “የሕልውና ጦርነት” ተብሎ ወደተሰየመው ጦርነት ገቡ። የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው የፌደራሉን መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ለመቀበል ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀመጡ።
ራሳቸውን የትግራይ መከላከያ ኃይል ብለው የሚጠሩት የህወሓት አማጺያን፤ ካስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ባንክ፣ ቴሌኮም እና የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች ይጀምሩ፣ የፌደራል መንግሥቱ በጀት ይልቀቅ፣ ከመቀለ ቀጥታ በረራዎች ይጀምሩ የሚሉት ይገኙበታል።

የሱዳን እና ኢትዮጵያ የድንበር ውዝግብ
2013 ዓ.ም. ኢትዮጵያ እና ሱዳን በድንበር ውዝግብ ምክንያት ጦር ሊማዘዙ ይችላሉ የሚል ስጋት የተፈጠረበት ዓመት ሆኖ አልፏል። በስልጣን ላይ ያለው የሱዳን የሽግግር መንግሥት ወደ ስልጣን እንዲመጣ የተለያዩ አካላትን በማደራደር ከፍተኛ ድርሻ የነበራት ኢትዮጵያ፤ ዛሬ ላይ ከአገሪቱ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግነኙነት የሻከረ ነው። ሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ይገባኛል በሚሉት የድንበር ቦታ እንዲሁም በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት በመካከላቸው ያለው ውጥረት እየተባባሰ መጥቷል።
ኢትዮጵያ የትግራዩ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ በአልፋሽጋ የነበራትን ጦር ማንቀሳቀሷ የፈጠረውን ክፍተት ተከትሎ ሱዳን ይገባኛል ያለችውን የድንበር ቦታ ተቆጣጥራ ትገኛለች። የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ አጋጣሚዎች ሱዳን የያዘችውን መሬት ለቅቃ እንድትወጣ ሲጠይቅ ቢቆይም የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግን መሬቱ የሱዳን እንደሆነ በመግለጽ እንደማይወጡ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
በዚህ ብቻ ሳይገደቡም ሱዳኖች በዚህ ለእርሻ ምቹ እና ለም በሚባለው የድንበር ስፍራ አካባቢ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች ገንብተው አስመርቀዋል። በሕዳሴ ግድብ ጉዳይም ዙሪያም ሱዳን ከግብጽ ጋር ወዳጅነቷን በማጠናከር ከዚህ ቀደም የነበራትን አቋም ቀይራለች።

የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት
በ2013 ዓ.ም. ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ሐሴትን ከፈጠሩ ጉዳዮች አንዱ፤ የሁለተኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት መከናወኑ ነው። ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የግድቡን ውሃ ሙሌት “በተሳካ ሁኔታ” ማከናወኗ፤ ግብጽ እና ሱዳንን አስቆጥቶ ነበር። ሁለቱ አገራት ከወዳጅ አገራት ጋር በመሆን የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲቀርብ ያደረጉትም በዚሁ ዓመት ነው።
ተመድ በጉዳዩ ላይ መፍትሄ እንዲገኝ በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ሥር ውይይት እንዲደረግ አቅጣጫ ሰጥቶ ነበር። ይኹን እንጂ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የሚደረጉት ውድድሮች እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ማምጣት አልቻሉም። የቀድሞ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግድቡን የተመለከተ አወዛጋቢ አስተያየትም የተሰማው እየተገባደደ ባለው ዓመት ነበር። በዚህ ሁሉ መካከል ግን ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ማስከተል ችያለሁ ስትል ተናግራለች።
ኦነግ ‘ሸኔ’
በተለያዩ የኦሮሚያ እና አጎራባች ክልሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ንፁኀን ዜጎች ተገድለዋል፤ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ለዚህ ደግሞ ተጠያቂ ሲሆን የቆየው፤ መንግሥት “ሸኔ” የሚለው እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን ነው። ከህውሓት ጋር አሸባሪ ተብሎ በዚህ ዓመት የተፈረጀው ታጣቂው ቡድን፤ ከህወሓት ጋር ጸረ መንግሥት እንቅስቃሴ ለማድረግ ከስምምነት መድረሱም የተሰማው በዚሁ ዓመት ነበር።
ይህ ቡድን በስፋት እንደሚንቀሳቀስ በሚነገርባቸው ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ጉጂ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ውስጥ የመንግሥት ባለስልጣናትን ጨምሮ በዜጎች ላይ ግድያ እና ማፈናቀል ሲፈጽም እንደቆየ ባለስልጣናት ይናገራሉ።

ጥቃት እና ግድያዎች
ከትግራዩ ጦርነት ጋር በተያያዘ በማይካድራ፣ አክሱም፣ ጋሊኮማ እና ጭና ተብለው በሚጠሩ ስፍራዎች ከተፈጸሙት የጅምላ ግድያዎች በተጨማሪ በቤኒሻንጉል እና ምዕራብ ኦሮሚያ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ንፁኀን ዜጎች ላይ ግድያዎች ተፈጽመዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ በአንድ ጀንበር ከ200 በላይ ዜጎች በታጣቂዎች የተገደሉት በዚሁ ዓመት ነው።
በቤኒሻንጉል የኦሮሞ፣ አማራ እና ሺናሻ ብሔር ተወላጆችን ዒላማ በሚያደርጉ ጥቃቶች በርካቶች ሞተዋል። ለእነዚህ ግድያዎች ደግሞ የጉሙዝ ታጣቂዎች ተጠያቂ ይደረጋሉ። ከቤኒሻንጉል ውጪ መንግሥት ሸኔ በማለት የሚጠራው ቡድን በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ እንደ ጉሊሶ፣ አቤ ዶንጎሮ፣ አሙሩ፣ አባይ ጮመን፣ ኪራሙ . . . ተብለው በሚጠሩ ወረዳዎች ውስጥ የሚኖሩ በርካታ የአማራ ብሄር ተወላጆች በማንነታቸው ምክንያት ተገድለዋል።
በአማራ ክልል አጣዬ ከተማ ላይ በተሰነዘረ ጥቃትም በርካቶች አልቀዋል። ከተማው ወድሟል። የአፋር እና የሱማሌ ክልሎች ይገባኛል በሚሉት ስፍራ በደረሰ ጥቃት እንዲሁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስለመሞታቸው የተዘገበው በዚሁ በ2013 ዓ.ም. ነበር።
ምርጫ 2013
ኢትዮጵያ ጦርነት እና ስጋት ውስጥ ሆና በርካታ ታዛቢዎች “ተዓማኒ” ያሉትን አገራዊ ምርጫ አካሂዳለች። ዘንድሮ በተካሄደው ምርጫ በበርካታ ቦታዎች ድምጽ ሰጪዎች በደህንነት እጦት እና በሎጂስቲክስ ችግር ድምጻቸውን ሳይሰጡ ቀርተዋል። ከምርጫው መካሄድ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የደህንንት ስጋት ተደቅኖ የነበረ ቢሆንም ከጥቂት ስፍራዎች ውጪ ምርጫው በሰላም ተጠናቋል። ገዢው ፓርቲም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር ይዟል።

የኢትዮጵያ የውጪ ግንኙነት
2013 ዓ.ም. በተለይ ከትግራዩ ግጭት ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ የውጪ ግንኙነት የተፈተነበት እና በምስራቅ አፍሪካ የነበራት ተጽእኖ ፈጣሪነት ያጎደለበት ዓመት ሆኖ አልፏል። የትግራዩ ሰብዓዊ ቀውስ፣ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሁም ከሱዳን ጋር የተገባው የድንበር ውዝግብ የኢትዮጵያን የውጪ ዲፕሎማሲ የፈተኑ ጉዳዮች ነበሩ። በተለይ በትግራዩ ግጭት የአውሮፓ ሕብረት እና አሜሪካ መልዕክተኞቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እንዲልኩ አድርጓል።
አሜሪካም በትግራይ ጦርነት ተሳታፊ በሆኑ የጦር እና ሲቪል አመራሮች ላይ እቀባ ጥላለች። ከዚህ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ታደርግ የነበረውን የደህንንት እና ኢኮኖሚ ድጋፍ ማቋረጧን አስታወቃለች። የተባበሩት መንግሥታት በትግራይ ጉዳይ ለስምንት ያክል ጊዜ መምከሩም ይታወሳል።