የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች በአጠቃላይ እስከ 7 ሚሊዮን ሕዝብ ለረሃብ ቀውስ ሊጋለጡ ይችላሉ አለ።

ድርጅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት በአማራ እና አፋር ክልሎች ወደ 1.7 ሚሊዮን ሰዎችን ለረሃብ አደጋ ሲያጋልጥ ወደ 300ሺህ የሚጠጋ ሕዝብን ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬው አፈናቅሏል ይላል። በትግራይ ደግሞ ወደ 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲል ድርጅቱ አስታውሷል። በቅርቡ 3500 ሜትሪክ ቶን የጫኑ 100 ተሸካርካሪዎች ትግራይ መግባታቸውን በማስታወስ፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ማይክል ደንፎርድ የፌደራል እና የአፋር ክልል ባለስልጣናት ተሸርካሪዎቹ ትግራይ እንዲሰርሱ ላደረጉት ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ዳይሬክተሩ በርካቶች ለከፋ ረሃብ እንዳይጋለጡ ተጨማሪ ትብብር እና ሥራ መሰራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል። ድርጅቱ በዚህ ዓመት ለ12 ሚሊዮን ሕዝብ ድጋፍ መቅረብ አለበት ያለ ሲሆን ለዚህም የገጠመውን የ426 ሚሊዮን ዶላር የበጀት እጥረት ለመሙላት ጥረት ላይ መሆኑን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከፌደራል እና ከክልል መንግሥታት ጋር በመቀናጀት በትግራይ ክልል የምግብ እርዳታ እያቀረበ መሆኑን በመጥቀስ፤ በአፋር ለ530ሺህ ሕዝብ እንዲሁም በአማራ ክልል ደግሞ ለ250ሺህ ሕዝብ በአስቸኳይ ለመድረስ እቅድ ይዣለሁ ብሏል።

ህወሓት ዓለም አቀፍ ማሕብረሰብን ለማሳሳት የሰብዓዊ ቀውስን እንደ ምክንያት ማቆም አለበት

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌደራሉ መንግሥት ህወሓት ዓለም አቀፍ ማሕብረሰብን ለማሳሳት የሰብዓዊ ቀውስ ጉዳይን እንደ ምክንያት መጠቀም ማቆም አለበት ብሏል። የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ከሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች ጋር በመቀናጀት መንግሥት ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ የሰብዓዊ እርዳታዎችን ሲያደርስ ቆይቷል ብሏል። የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ አካባቢዎች ከወጣ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምግብ፣ ነዳጅ እና የእርሻ ግብዓቶችን የተለያዩ ቁሳቁሶችን የጫኑ ተሸርካሪዎች ሲገቡ ቆይቷል ሲል አስታውሷል።

ከዚህ በተጨማሪም የፍተሻ ጣቢያዎችን ቁጥር መቀነሱን እና የተራድኦ ድርጅት ሰራተኞች ወደ ክልሉ ይዘው ይገቡ የነበረውን ጥሬ ገንዘብ መጠን ከፍ እንዲል ማስረጉን ጨምሮ በመግለጫው አስነብቧል። ህወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ላይ ወረራ መፈጸሙን፣ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት መጋዘኖችን ዘርፏል መባሉን፣ የህወሓት ታጣቂዊችን ለእርዳታ ወደ ክልሉ የገቡ ኃይል ሰጪ ብስኩቶቹን ይዘው መገኘታቸውን እና ሌሎች ጉዳዮችን በመጥቀስ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ክልሉ እንዳይገባ እንቅፋት የሆነው ህውሓት እንጂ የፌደራሉ መንግሥት አይደለም ብሏል።

ህወሓት የሰብዓዊ እርዳታ ትግራይ ለለመድረሳቸው የፌደራል መንግሥትን ተጠያቂ ማድረጉ አግባብ አይደለም ብሏል። ይህ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር መግለጫ የተሰማው ትግራይን እያስተዳደረ ያለው ህውሓት እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ትግራይ ውስጥ በረሃብ ምክንያት ሰዎች እየሞቱ ነው ማለታቸው ከተሰማ በኋላ ነው። የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፎ አትንኩት መዝገቦ (ዶ/ር)ሰዎች እና እንስሳት በረሃብ እና በመሠረታዊ የህክምና እንክብካቤ እጥረት እየሞቱ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ህወሓትም ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ የክልሉን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኤጀንሲን ዋቢ አድርጎ በነሐሴ ወር 150 ሰዎች በረሃብ መሞታቸው ተመዝግቧል ብሏል። እንደ ህወሓት መግለጫ ከሆነ ረሃቡ የተከሰተው ማይ ቅኔጣል፣ ቆላ ተምቤን፣ ሃውዜን፣ በማዕከላዊ ዞን ታንኳ ምላሽ እንዲሁም ሽረ ውስጥ ባለ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ውስጥ እንደሆነም ተመልክቷል። የግብርና ኃላፊው ዶ/ር አትንኩት መዝገቦ እንደሚናገሩት በምግብ ዕርዳታ ዕጥረት ምክንያት ረሃብ በመላው ክልሉ እየተስፋፋ ነው።

“ከዚህ ቀደም ነዋሪዎች የነበረቻቸውን ይቋደሱ ነበር ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የሚበሉት የላቸውም” ብለዋል። ለዚህም ደግሞ ነዳጅ አቅርቦት አለመኖሩ እንዲሁም የባንክ አገልግሎትና መብራት መቋረጥ ችግሩን በዋነኝነት እንዳባባሰው ያስረዳሉ።

ምንጭ – ቢቢሲ