ከትግራይ ወደ ሱዳን የሸሹ ዜጎች ተጠልለው ከሚገኙባቸው መንደሮች አንዷ የሆነችው ኡማ ራኩባ።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) በሱዳን በሚገኙ ካምፖች ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር ቢቀንስም እነዚህ ስደተኞች የት እንዳሉ ግን እንደማያውቅ ገለጸ።

ድርጅቱ ይህን ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት በሱዳን ለስደተኞች የሚሰጥ መታወቂያን የያዙ ግለሰቦች ከህወሓት ወገን ተሰልፈው እየተዋጉ ነው ማለቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ነው። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ዩኤንኤችሲአር የሚሰጠውን የስደተኞች መለያ መታወቂያ የያዙ ታጣቂዎች ከሱዳን ድንበር ተሻግረው ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንዲሁም ወደ አማራ ክልል ገብተዋል ሲል ወንጅሏል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ለዚሁ ምላሽ ባወጣው መግለጫ፤ ከስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚወጡት ስደተኞች የት እንደሚሄዱ የሚያረጋግጥበት መንገድ እንደሌለው አስታውቋል። ባለፉት ጥቂት ወራት በሱዳን የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር በተወሰነ ደረጃ እንደቀነሰ ገልጾ፤ “ዩኤንኤችሲአር ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱ ስደተኞችን ጨምሮ ከስደተኞች መጠለያ የወጡ ግለሰቦች የት እንዳሉ ማረጋገጥ አይችልም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ሱዳን ውስጥ የመዘገባቸው አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በጦርነት ስለመሳተፋቸው በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን መዘገቡን እንደሚያውቅም ዩኤንኤችሲአር አመልክቷል። የፈረንሳይ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን “የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ድንበር ላይ ጥገኝነት የሚጠይቁ ታጣቂዎችን ከሲቪሎች የምንለይበት አሠራር ዘርግተናል” እንዳሉ ዘግቧል።

ከዚህ በተጨማሪም በሱዳን የስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ “ወታደራዊ ስልጠና እየተሰጠ ነው” የሚል ክስ እንዳለና ይህ ግን የተሳሳተ እንደሆነ ባልሥልጣኑ መናገራቸውን ጨምሮ ዘግቧል። የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ “ህወሓት የሱዳንን ድንበር በማቋረጥ ግጭቱን ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና አማራ ክልሎች ለማስፋፋት ሞክሯል” ብሏል። “የዩኤንኤችሲአር መለያ መታወቂያ የያዙ ጥቂት የህወሓት ወታደሮች ከሱዳን በኩል ሲገቡ ተይዘዋል” ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ይህም ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ለስደተኞች የሚሰጠውን ከለላ መርህ እንደሚጣረስ ተናግሯል።

ዩኤንኤችሲአር በምላሹ፤ የመዘገባቸው እና መታወቂያ የሰጣቸው ግለሰቦች በስደተኞች ማቆያ ካምፕ ውስጥ የሰብዓዊ እርዳታ መውሰዳቸውን አረጋግጦ ለዚህም ምዝገባ የሚሆን የራሱ አሠራር እንዳለው ገልጿል። አያይዞም “ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦች ስደተኛ ተደርገው አይወሰዱም” ሲልም አሠራሩን አብራርቷል። ስደተኛ የሚለው መለያ፤ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ ለሆነ ሰው እንደማይሰጥም ድርጅቱ አክሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን እንዳለው፤ የስደተኞች መጠለያዎች ሰብዓዊ እርዳታ መስጫ ሆነው መቀጠል አለባቸው። “በግጭት ወቅት የስደተኞች ማቆያዎችን ሰብዓዊ መዳረሻ አድርጎ ማስቀጠል ከባድ ቢሆንም ከሱዳን መንግሥት ጋር በመተባበር ይህንን መርኅ ለመጠበቅ አንሠራለን” ብሏል። ድርጅቱ ይህንን መርህ ለማስጠበቅ ሲልም በስደተኞች መጠለያዎች ታጣቂዎችን ከሲቪሎች እንደሚለይ አስታውቋል። በሱዳን ያሉት የስደተኞች መጠለያዎች ለኢትዮጵያ አማጺያን መሸሸጊያ እንዲሆኑ እንደማይፈቅድም ገልጿል።

በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ከአስር ወራት በፊት ጦርነት መነሳቱን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሱዳን መሸሻቸው ይታወሳል። ይህም በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ውጥረት እንዲፈጠር ካደረጉ ነገሮች አንዱ ነው። ኢትዮጵያ እና ሱዳን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሁም የሁለቱ አገሮች ድንበር ጉዳይም ያወዛግባቸዋል።