በክፍል ስድስት ውስጥ የቀረቡት አስተያየቶች ጋዜጠኞች የተለያዩ ግጭቶችን በሚዘግቡበት ወቅት ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ የተለያዩ ዘዴዎችን ያገኛሉ የሚል ተስፋ አለን። የዚህ ማጣቀሻ መጽሐፍ የመጨረሻው ወሳኝ ክፍል ጋዜጠኞች ከግጭት ጋር በተያያዘ ዘገባ ሲሠሩ የሚጠቀሟቸው በርካታ ተግባራዊ ጉዳዮችን ያነሳል። በዚህ ክፍል ውስጥ የተካተቱት አብዛኛዎቹ ነጥቦች የዝግጅት ክፍሉ አባላት በግጭት ዘገባ ላይ ባገኙት ልምድ ተመሥርተው ያንፀባረቁት ምልከታ ነው። የአንዱ ሰው ሐሳብ የሌላውን ሰው ሐሳብ እየወለደ እነዚህ ሐሳቦች በውይይቶች ወቅት የፈለቁ ናቸው። ክፍል ሰባት በቡድን ውይይታችን ወቅት የተሠሩ ጥቂት ነገር ግን በጣም ጠቃሚ ነጥቦችን በማንሳት ይጀምራል። የግጭቱን አጠቃላይ ሽፋን በተመለከተ ከዝግጅት ክፍል ጋር የሚኖር ትብብር አስፈላጊነት ላይ ከማተኮራችን በፊት በግጭት ዘገባ ወቅት የቃለ መጠይቅን ሚና እና አስፈላጊነት አንዳንድ ሐሳቦችን እንመረምራለን። ግጭትን በሚዘግቡበት ጊዜ እንዴት ደኅንነትዎን መጠበቅ እንደሚችሉ ጥቂት ሐሳቦችን በመስጠት ክፍል ሰባት ይጠናቀቃል።
7.1 ለግጭት አዘጋገብ የተግባር ጥቆማዎች
የአርትኦት ቡድኑ አባላት ለተለያዩ ሚዲያ ተቋማት የተለያየ ዓይነት ግጭቶችን በመዘገብ ሰፊ ልምዶችን ይጋራሉ። ይህ አጭር የምክሮች ዝርዝር በቀጥታ ከልምዶቻቸው የተወሰደ ነው። ብዙዎቹ እነዚህ ሐሳቦች እርስበርሳቸው የተያያዙ ናቸው። በዘገባዎቻችሁ ላይ ከነዚህ ውስጥ ብዙዎቹን እየተጠቀማችሁባቸው ይሆናል። ካልሆነ ግን መመልከቱ ይጠቅማል።
ቀድመው ይዘጋጁ
የዝግጅት ቡድኑ ጋዜጠኞች ቁጭ ብለው ግጭቶች እሰኪነሱ ድረስ መጠበቅ እንደሌለባቸው ይሥማማሉ። ይልቁንም የምንሠራበት አካባቢ ያሉ ማኅበረሰቦችን መከታተል እና ግጭት ቀስቃሸ ምልክቶችን ማስተዋል ይኖርብናል (ክፍል 1.3 – የግጭት ዕድገት ደረጃዎችን፣ ይመልከቱ)
ግጭት ከእምቅ ወደ አፍላነት የሚሸጋገር መሆኑን የሚጠቁሙ ምልክቶችን እንዳስተዋልን ወዲያውኑ ስለተፈጠረው ነገር በተቻለ መጠን ከብዙ አቅጣጫ ያሉ ሐሳቦችን ለማግኘት መሬት ላይ ሰዎችን ማነጋገር መጀመር አለብን። ይህም ግጭቱን በተመለከተ ዋና ባለድርሻ አካላትን በምናናግርበት ጊዜ የተሟላ መረጃ እንዳለን ያረጋግጣል። ጀምስ ምፋንዴ ጋዜጠኞች ምላሽ ሰጪነተትን መተው አለባቸው ሲሉ የሚከተለውን ይናገራሉ:
ቃል አቀባዮች ወደ እኛ እስኪመጡ የምንጠብቅ ከሆነ እነሱ በአቀዱት አጀንዳ ተገድበናል ማለት ነው። ነገር ግን በጥንቃቄ በተዘጋጁ ጥያቄዎች አማካኝነት ንቁ ሆነን ካነጋገርናቸው እየተካሔደ ስላለው ነገር ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት እንችላለን።
ምንጮችን ማሳደግ
ጋዜጠኞች ንቁ መሆን የሚችሉት መሬት ላይ ያለውን ነገር ከተከታተሉ እና በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ምን እየሆነ እንዳለ ከሚያውቁ ሰዎች ጋር ሲነጋገሩ ብቻ ነው።
ይህ ሊሆን የሚችልበት ብቸኛ መንገድ ደግሞ ጋዜጠኞች ከቢሯቸው ወጥተው ከማኅበረሰቡ ጋር ሲነጋገሩ እና ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ሲኖራቸው ነው። በአከባቢዎ ስለሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ማኅበረሰብ ዐቀፍ ድርጅቶች ይወቁ። ከአነስተኛ የንግድ ሥራ ባለቤቶች ጋር ይነጋገሩ እንዲሁም ከአካባቢው አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶች እና ቤተ እምነቶች ጋር ግንኙነት ይፍጠሩ። ከሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት፣ ከማኅበራዊ ጉዳይ አራማጆች እና ከሙያ ማኅበራት ጋር ራስዎን ለማስተዋወቅ ጊዜ ይስጡ። ከሕዝብ ግንኙነቶች ጋር ብቻ ሳይሆን ከተራ ግለሰቦች ጋር ግንኙነት አዳብሩ።
የፖሊስ እንዲሁም የአካባቢው ምክር ቤቶች የተለያዩ ክፍሎች አድራሻ ይኑራችሁ። ከነዚህ ሰዎች ጋር በቋሚነት መረጃ ተቀያየሩ። በየሳምንቱ ወይም በየሁለት ሳምንቱ የሚደረግ የስልክ ጥሪ ወጪው አነስተኛ ነው፤ ነገር ግን ከተለያዩ መደበኛ ምንጮች ጋር መገናኘት ብዙውን ጊዜ ጥሩ ታሪኮችን እንድትሰሩ ይረዳል። እነዚህ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ውጥረቶች በሚነግሱበት ጊዜ እና በማኅበረሰቡ ወደ ግጭት የሚያመመሩ ሁኔታዎች በሚከሰቱበት ወቅት የሚጠቁሟችሁ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ግጭቶች ከመቀስቀሳቸው በፊት ጥቆማውን ታገኙና የምትሠሩት ታሪክ ግጭቱ ከመቀስቀሱ በፊት ለመከላከል የሚጠቅም ይሆናል።
ግጭቶች በከፍተኛ ሁኔታ የተባባሱ ሲሆን እና የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመንቀሳቀስ አደገኛ አካባቢዎች በሚሆኑበት ወይም በቀላሉ ብዙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመጎብኘት ጊዜ ከሌላችሁ ከተለያዩ ሰዎች ጋር የመሠረታችሁት ግንኙነት ወሳኝ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች ምን እየተከሰተ እንዳለ ጠቃሚ መረጃ ይሰጧችኋል፤ ምን እንዳጋጠማቸው ይገልጹላችኋል እንዲሁም በተሳታፊ ቡድኖች፣ በባለሥልጣናት እና ባለድርሻ አካላት የሚነሳውን ጥያቄ እንድታረጋግጡ ይረዷችኋል።
የነውጥ መነሳትን በሬዲዮ ጣቢያዎች በምንዘግብበት ወቅት እነዚህ ምንጮች አመፁ የት እንደሚካሔድ እና የትኞቹ አካባቢዎች መንቀሳቀስ እንደሌለባቸው ለተደራሾቻችን ማሳወቅ እንድትችሉ ይረዷችኋል።
ማስታወሻ መያዝ
ባርባራ አሞንግ ጋዜጠኞች ግጭቱን በሚዘግቡበት ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉንም አስፈላጊ መረጃዎች የያዘ የመረጃ ቋት እንዲያዘጋጁ ይመክራሉ። ይህ ከዚህ ቀደም ስለተከሰቱ ግጭቶች ቀናት፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ሥም እና አቋም መረጃን ሊያካትት ይችላል። እንዲሁም በግጭቱ ወቅት በተለያዩ መሪዎች ስለተደረጉት ቁልፍ ሥምምነቶች መረጃን ሊያካትትም ይችላል። ይህ የመረጃ ቋት በቋሚነት መስተካከል አለበት። ባርባራ የራሳቸውን አቀራረብ በተመለከተ እንዲህ ገልጸውታል፦
የሰሜን ኡጋንዳውን ግጭት በቋሚነት በምዘገብበት ጊዜ ሁኔታዎችን የምመዘግብበት፣ ቀኑን እና ሰዓቱን፣ ምን እንደተከሰተ እና የተሳተፉትን ሰዎች የማሰፍርበት አንድ አነስተኛ ማስታወሻ ደብተር ነበረኝ። ደብተሩን በጥንቃቄ ስላኖርኩት ቀደም ሲል የተከናወኑ ሁኔታዎችን ለመጥቀስ ቀላል ነበር። ምክንያቱም መቼ ምን እንደተከሰተ በትክክል አውቅ ነበር። የራሴን የመረጃ ቋት ስለፈጠርኩ ታሪኮችን ለመጻፍ ስፈለግ ሁሉም መረጃ አለኝ።
እንደዚህ ያለ “የመረጃ ቋት” መኖር ማለት ከቦታው ሆነው የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ስለ ግጭቱ ዐውዱን ባገናዘበ መልኩ የሚሠሩ ታሪኮችን ለማቅረብ ብቁ ናቸው ማለት ነው። በተለይም ቀጥታ ዘገባውን ለሚያቀርቡ የብሮድካስት ጋዜጠኞች ጠቃሚ ነው።
የትርጉም ግድፈት
በብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች ውስጥ ለሚሠሩ ጋዜጠኞች ሰዎች የተናገሩትን መሠረታዊ ነገር ሊያዛባ የሚችል የትርጉም ግድፈት አደጋ ሁልጊዜ አለ። ጋዜጠኞች ሰዎች የተናገሩትን ንግግር ወደ ሌላ ቋንቋ ሲተረጉሙ በተቻለ መጠን በጥንቃቄ መሆን ይኖርበታል። እንዲሁም ሁሉንም ነገር ደግሞ ማጣራት አስፈላጊ ነው።
ሆኖም፤ ምንም እንኳን አንድ ትርጉም በቀጥታ ሲታይ ትክክል ቢሆንም እንኳን ግለሰቡ ሊናገር የፈለገውን ነገር ላንረዳው እንችላለን። የሚቻል ከሆነ በቀጥታ አንድ ሰው የተናገረውን ቃል በቃል ከመጥቀስ ይልቅ ሌላ ቃላት ተጠቅሞ የተናገረውን ሐሳብ መግለጽ ይመከራል። እንደ አማራጭ ጋዜጠኞች የጠቀሱትን ንግግር ትርጉም መሆኑን መግለጽ ይችላሉ። ለምሳሌ፡ ‘አቶ እከሌ በኢሲዙሉኛ እንደተናገረው፦ “የተተረጎመ ንግግር” በማለት ማቅረብ። ይህ ትርጓሜው አቶ እከሌ የተናገረውን ሙሉ በሙሉ ሊያንፀባርቅ እንደማይችል ለአንባቢው ያስጠነቅቃል። ለሬዲዮ፣ ዋናውን ንግግር በማስቀደም ድምፁ ሳይጠፋ ትርጉሙን የማቅረብ ዘዴ ተመሳሳይ ውጤት ያስገኛል።
ጋዜጠኞች የግጭት አከባቢዎች ለመግባት የሌሎች ሰዎችን ዕርዳታ መጠየቅ የሚኖርባቸውባቸው ጊዜያቶች አሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ዘገባ ሲሠሩ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ግልጽ ሊሆንላቸው ይገባል። ከወታደሮች ወይም ከፖሊሶች ጋር ወደ ግጭት ቀጠናዎች የሚጓዙ ጋዜጠኞች ብዙውን ጊዜ የተወሰኑ ሰዎችን እንዳያነጋግሩ ወይም የተወሰኑ ቦታዎችን እንዳይጎበኙ በሚከለክሉ “ጠባቂዎች” ይታጀባሉ። በእነዚህ ሁኔታዎች ጋዜጠኞች መሬት ላይ እየተከናወነ ያለውን ነገር ለማንፀባረቅ የማይቻላቸው መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ጋዜጠኞች ከዕርዳታ ድርጅቶች ወይም ከአምባሳደር ልዑካን ጋር ወደ ቦታው ሲሔዱም ተመሳሳይ ነው። እነዚህ የዕርዳታ ድርጅቶች በዜና ማሰራጫ መተላለፍ ያለበትን ለመቆጣጠር ልክ እንደ ጦር ኃይሉ ሁሉ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ሲሆኑ፥ ጋዜጠኞችም ከእነዚህ ቡድኖች የሚያገኙት ድጋፍ በሚፈቅድላቸው መጠን ግልጽ መሆን አለባቸው። ወይም ዕርዳታ ማግኘት አለማግኘታቸውንም መግለጽ አለባቸው።