የሕወሓት ታጣቂዎች በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ጭና ተክለ ሃይማኖት ቀበሌ፣ በርካታ ንፁኃን ዜጎችን መጨፍጨፋቸውን የአማራ ክልል አስታወቀ፡፡ ምንም እንኳ የሟቾች ቁጥር እየተጣራ ቢሆንም፣ ከ100 በላይ ንፁኃን ዜጎች ሳይገደሉ እዳልቀረ ከዓይን እማኞች መረዳት መቻሉን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹በጀግኖቻችን የተቀናጀ ጥቃት ሲፈጸምበት በየጫካው እየተፋለሙት ያሉትን  መቋቋም ያልቻለው ወራሪ በየቤታቸው የነበሩ አዛውንቶችን፣ ሕፃናትንና እናቶችን በያሉበት መንደርና ሠፈር በመግባት፣ ቀሳውስትን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብቶ የፊጥኝ በማሰር ጨፍጭፏቸዋል፤›› ሲሉ የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት በድረ ገጹ አስታውቋል፡፡

የሕወሓት ኃይሎች በሰሜን ወሎና በአፋር ክልል የፈጸሙትን ዓይነት ዘግናኝ ጭፍጨፋ፣ በሰሜን ጎንደር በዳባት ወረዳ በጭና ተክለ ሃይማኖት ቀበሌ በድጋሚ መፈጸማቸውን ጽሕፈት ቤቱ አክሎ ገልጿል፡፡ በተመሳሳይ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ዘ ቴሌግራፍ የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ በሐምሌ 2013 ዓ.ም. መጨረሻ የሕወሓት ታጣቂዎች በአማራ ክልል ቆቦ ውስጥ፣ አጋምሳ በሚበል አካባቢ፣ በከባድ መሣሪያ ድብደባ በርካታ ቤቶችን በማቃጠል የጅምላ ጥቃት መፈጸማቸውንና በርካቶችም አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን መዘገቡ ይታወሳል፡፡

‹‹የሚዲያ ተቋማት ይኼንን እውነት ዓለም እንዲያውቀውና ከወራሪውና ከጨፍጫፊው ጋር በምናደርገው ትግል አብረውን እንዲቆሙ፣ ድርጊቱንም እንዲያወግዙትና በፍጥነት ቦታው ድረስ በመሄድም ሁኔታውን  እንዲዘገቡ፤›› ሲል ጽሕፈት ቤቱ ጥሪ አቀርቧል፡፡

ከአንድ ቀን በፊት በደሴ ከተማ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ከነዋሪዎች ጋር ምክክር ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ‹‹የሕወሓት ወራሪ ኃይል ዳግም የአገሪቱ ሥጋት በማይሆን ደረጃ በጋራ መከላከልና ህልውናን ማስቀጠል የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳ ሆኖ እየተከናወነ ነው፤›› ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *