የሱዳን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ካርቱም የገቡት የጦር መሳሪያዎችን የያዙ ከ70 በላይ ሳጥኖች ሕጋዊ ናቸው ሲል አረጋገጠ።
ቅዳሜ በካርቱም አየር ማረፊያ የጉምሩክ ባለሥልጣናት በሕገ ወጥነት መያዛቸው የተዘገበው የጦር መሳሪያዎች ሕጋዊ ፈቃድ ባለው የጦር መሳሪያ ነጋዴ የመጡ መሆናቸውን የሱዳን መንግሥት መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል። የሱዳን መንግሥት የዜና ወኪል የሆነው ሱና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓጉዘው ሱዳን የገቡት የጦር መሳሪያዎች “[በሱዳን] መንግሥት ላይ ወንጀል ለመፈጸም” ጥቅም ላይ ሊውሉ ነበር የሚል ጥርጣሬ አለ ሲል ዘግቦ ነበር።
መነሻውን ከአዲስ አበባ አድርጎ ቅዳሜ ምሽት ካርቱም ባረፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ ተጭነው የነበሩት የጦር መሳሪያዎች በሱዳን ጉምሩክ ባለሥልጣናት እንደተያዙ ሱና በዘገባው አመልክቷል። ሱዳን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ካርቱም ከገቡ በኋላ ተይዘዋል ስላለቻቸው የጦር መሳሪዎች ምርመራ እያደረኩ ነው ስትል አስታውቃ ነበር።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ ሱዳን ካርቱም ያጓጓዛቸው የጦር መሳሪያዎች ሕጋዊ ናቸው ሲል ሰኞ ረፋድ ላይ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቶ ነበር። አየር መንገዱ እንዳለው መሳሪያዎቹ ወታደራዊ ሳይሆኑ ለአደን አገልግሎት የሚውሉ ከመሆናቸው በተጨማሪ አስፈላጊው ሕጋዊ የመጓጓዣ ሰነድ ያላቸው ናቸውም ብሏል። ሰኞ አመሻሽ ላይ የሱዳን የአገር ውስጥ ሚኒስቴርም መሳሪያዎቹ ‘ዋኤል ሻምስ ኤልዲን’ በተባለ ፈቃድ ባለው የመሳሪያ ነጋዴ ድርጅት አማካይነት በሕጋዊ መንገድ የገቡ መሆናቸውን አረጋግጧል።
አየር መንገዱ ምን አለ?
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሱና ላይ የወጣውን ዘገባ የተሳሳት ነው ያለ ሲሆን፤ ወደ ካርቱም ያጓጓዛቸው የአደን ጦር መሳሪያዎች ሕጋዊ ሰነድ እንዳላቸው ገልጿል። አየር መንገዱ “ወደ ሱዳን የተጓጓዙት ጦር መሳሪያዎች ሕጋዊ እንዲሁም ከተቀባይና ከላኪ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች ያሉት የንግድ ለአደን የሚውሉ ጦር መሳሪያ ትራንስፖርት ነው” ብሏል ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ።
ሱና የጦር መሳሪያዎቹን ጉዳይ እንዲያጣራ የተቋቋመው ኮሚቴ ጦር መሳሪያዎቹ ከሩሲያ ሞስኮ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ ለሁለት ዓመታት ተቀምጠው ለሱዳን መንግሥት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ በሲቪል አውሮፕላን ወደ ካርቱም እንዲጫኑ አዲስ አበባ ፈቅዳለች ማለቱን አስነብቦ ነበር። ኮሚቴው ጨምሮም ጦር መሳሪያዎች በ72 ሣጥኖች መጓጓዛቸውን እና በውስጡም ከጦር መሳሪያዎች በተጨማሪ በጨለማ መመልከት የሚያስችሉ መነጽሮች ይገኙበታል ብሏል።
አየር መንገዱ በበኩሉ የጦር መሳሪያዎቹ አዲስ አበባ በሚገኙ የደኅንነት ባለስልጣናት ለረዥም ጊዜ የማጣራት ሥራ ሲከናወንባቸው ቆይቷል ይላል። በዚህም የተነሳ የጦር መሳሪያው ተቀባይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሳሪያዎችን እንዲልክ አልያም ወደ 250 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ካሳ እንዲከፈለው በሱዳን ፍርድ ቤት አየር መንገዱን መክሰሱን ገልጿል።
አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ደኅንነት ኃላፊዎች የማጣራት ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ጦር መሳሪያውን ለማጓጓዝ ፍቃድ ማግኘቱን ተከትሎ በሱዳን ለሚገኘው ተቀባይ ጦር መሳሪያውን አጓጉዘናል ብሏል። አየር መንገዱ ከዚህ በተጨማሪም የመሳሪያው መጓጓዝ ሕጋዊነትን የሚያረጋግጥ ከሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የተጻፈ ደብዳቤ አለኝ ብሏል።
የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነት መሻከር
ኢትዮጵያ እና ሱዳን ይገባኛል በሚሉት የድንበር ቦታ እና በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት በመካከላቸው ያለው ውጥረት እየተባባሰ መጥቷል። ኢትዮጵያ የትግራዩ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ በአልፈሽጋ የነበራትን ጦር ካንቀሳቀሰች በኋላ ሱዳን የድንበር ቦታውን ተቆጣጥራ ትገኛለች። የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ አጋጣሚዎች ሱዳን የያዘችውን መሬት ለቅቃ እንድትወጣ ሲጠይቅ ቢቆይም የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግን መሬቱ የሱዳን እንደሆነ በመግለጽ ለቀው እንደማይወጡ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊትም የሱዳን መሪዎች በአልፋሽጋ አካባቢ የገነቧቸውን መሠረተ ልማቶች አስመርቀው ነበር። በሌላ በኩል ከሦስት ቀናት በፊት ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ከሱዳን ሰርጎ ለመግባት የሞከረ የህወሓት ቅጥረኛ ኃይልን ደመሰስኩ ማለቷ ይታወሳል። የአገር መከላከያ ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ኮሎኔል ሰይፈ ኢንጊ፣ በሰዱን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገባ የተባለው ኃይል የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ጥቃት ለመሰንዘር እንደነበር አመልክተዋል። ጨምረውም ቡድኑ የተለያዩ ፀረ ሰው እና ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂዎችን ለማጥመድ ሞክሮ ነበር ስለማለታቸው የአገር መከላከያ ሠራዊት አስታውቆ ነበር።
ምንጭ – ቢቢሲ