በ1997 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ መንግሥት በሕግ ብሎም በአስተዳደራዊ ጫናዎች አዳክሞት የቆየው የሲቪል ማኅበራት እንቅስቃሴ ባለፈው ሁለት ዓመት መሻሻል ማሳየቱ በርካቶች ይናገራሉ።

ለዚህም መሠረታዊ ተብለው ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል ከሁለት ዓመታት በፊት የተሻሻለው የሲቪል ማኅበራትን የሚያስተዳድረው ሕግ ይገኝበታል። እንዲሁም መንግሥት የሲቪል ማኅበረሰቡን ከጠላትነት ይልቅ በአጋርነት የመመልከት የፖለቲካ አቋም ለውጥ ማድረጉ በዘርፉ ለታየው መሻሻል አስተዋጽኦ መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል። ታዲያ እነዚህን መሻሻሎች እንዳይቀለብሱ ያሰጉ አዳዲስ መመሪያዎች እየወጡ መሆኑን ተከትሎ በሲቪል ማኅበረሰቡ ዘንድ ቁጣን ብሎም ስጋትን ተፈጥሯል።

አዋጁን ለማስፈጸም ይጸድቃሉ ተብለው የሚጠበቁት አጠቃላይ መመሪያዎች ቁጥር 17 ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አራቱ ከሁለት ሳምንት በፊት ጸድቀዋል። እነዚህ አወዛጋቢ መመሪያዎች የእናት ሕጉን መንፈስ፣ ዓላማ ብሎም ግልጽ ድንጋጌዎችን የሚቃረኑ እንዲሁም የመጽደቅ ሂደታቸውም ሕግን ያልተከተለ ነው ሲሉ ጉዳዩን በቅርብ ሲከታተሉ የነበሩት የሕግ ባለሙያው ደበበ ኃይለገብርኤል ይተቻሉ። ከ50 ዓመታት በላይ በተደረገ ግፊት፣ ከወራት በፊት የጸደቀው አስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕጉን የጣሱ አካሄዶችም መታየታቸውን ለአብነት ይጠቅሳሉ።

“በአስተዳደር ሕጉ መሰረት ማንኛውም ሕግ ከመጽደቁ በፊት በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ድረ-ገጽ ላይ ለአስተያየት ይፋ ማደረግ ይገባው ነበር” ሲሉም በሲቪል ማኅበራት አዋጁ ማርቀቅ ሂደት ላይ የተሳተፉት አቶ ደበበ ይናገራሉ። የሲቪል ማኅበራት አዋጁ በኢትዮጵያ ከሦስት ዓመት በፊት ተከስቶ የነበረውን ለውጥ ተከትሎ ከተደረጉ የሕግ ማሻሻያዎች ውስጥ አንዱ ነው። አዋጁ ለዓመታት የሲቪል ማኅበራቱ አብዛኛው የሀብት ምንጭ ከአገር ውስጥ እንዲያሰባስቡ አስቀምጦት የነበረውን ግዴታ ማሻሻሉ በዘርፉ መነቃቃትን ፈጥሯል።

አዲሱ አዋጅ የሲቪል ማኅበራት ለሥራቸው የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ከየትኛውም ሕጋዊ የፋይናንስ ምንጭ እንዲያገኙ ያስቻለ ሕግ እንደሆነ አቶ ደበበ ይናገራሉ። ይህ በሰው ኃይል ጥራት ብሎም የሲቪል ማኅበራቱ መብቶች እና ዴሞክራሲ ላይ ለመስራት እንዳስቻላቸውም ጠቅሰዋል። ይህ ሕግ ከመውጣቱ በፊት በሥራ ላይ የነበሩ የሲቪል ማኅበራት ቁጥር 1 ሺህ 800 ሲሆን አሁን ይህ ቁጥር ወደ 3 ሺህ 500 ከፍ ብሎ በአዲሱ አዋጅ መሰረት ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ይህ አዋጅ በፌደራል ደረጃ ይውጣ እንጂ ክልሎች ተመሳሳይ ሕጎችን አለማውጣታቸው መሻሻሉ ከታሰበው በላይ እንዳይሄድ እንቅፋት መሆኑን አቶ ደበበ ይናገራሉ። ግንዛቤ ባለመኖር በተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች ዘንድ ባለው የአረዳድ ችግር አስተዳደራዊ ችግሮች እንደሚያጋጥሙም ተናግረዋል። ይህንን መሻሻል ወደ ኋላ ይመልሳሉ የተባሉት እኚህ አዳዲስ መመሪዎች ባሉበት የሚጸድቁ ከሆነ ከፍተኛ ስጋት የሚደቅኑ እንደሆነ የሕግ ባለሙያው ጨምረው ይናገራሉ።

“አንዳንድ ድርጅቶች ስጋት ስላላቸው ባልጸደቁት መመሪያዎች ላይ ውይይት ለማድረግ ማሰባቸውን ተረድቻለሁ። እንዲሁም በአስተዳደር አዋጁ መሰረት እስከ ፍርድ ቤት ድረስ የመሄድ እድል እንዳለ የሚያመላክቱ ነገሮች አሉ። አንዳንድ ድንጋጌዎች በዚሁ ከቀጠሉ አስከ ፍርድ ቤት ክርክር ድረስ የመሄድ እድል አለው” ሲሉ አቶ ደበበ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለመሆኑ መመሪያዎቹ ምን ይላሉ?

በረቂቅ ደረጃ ካሉት መመሪያዎች መካከል በሁለቱ ላይ አይሲኤንኤል የተሰኘ ዓለም አቀፍ በሲቪል ማኅበራት ጉዳይ ላይ የሚሰራ ተቋም ያዘጋጀውን ትንተና ቢቢሲ ተመልከቷል። ይህም የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማቱን ምዝገባ አስተዳደር እንዲሁም ስለሚደረጉ ክትትል፣ ቁጥጥር እና ምርመራ የሚመለከቱትን ሁለት መመሪያዎች የተመለከተ ነው።

የመንግት ቁጥጥር

ማኅበራቱን ለመቆጣጠር የወጣው መመሪያ ዓላማ ተብለው ከተቀመጡት ነጥቦች መካከል “የድርጅቶቹ አሰራር ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለበት እንዲሁም ለኅብረተሰቡ የላቀ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን ማረጋገጥ” የሚለው አንዱ ነው። በዚህ ድንጋጌ ላይ በተለይም “የላቀ ጥቅም” ለትርጉም የተጋለጠ ለሲቪል ማኅበራቱ እንዲሁም ለኤጀንሲው ለክትትል እንዲሁም ለልኬት የሚያስቸግር አገላለጽ መሆኑን ሰነዱ ያሰረዳል። እንዲሁም ሕጎች ግልጽ በሆነ ቋንቋ መጻፍ እንዳለባቸው የሚደነግጉ ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን ከግምት ያላስገባ ነው ሲልም ይተቻል።

“ኤጀንሲው ድርጅቶች ሥራቸውን በሕግ መሠረት ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው በማናቸውም መንገድ በመደበኛነት ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይችላል” ሲል የቁጥጥር መመሪያው በአንቀጽ 6 ስር ይደነግጋል። በተለይም “በማናቸውም መንገድ” የሚለው ሐረግ ለኤጀንሲው እጅግ የተለጠጠ እና ለትርጉም ክፍት የሆነ ስልጣን የሚሰጥ እና ለሕገወጥ አካሄዶች በር ከፋች ነው ሲል ሰነዱ ያትታል።

እንዲሁም ለክትትልና ቁጥጥር ዓላማ ሲባል ኤጀንሲው የተለያዩ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ የቁጥጥር እና የክትትል እቅድ እንደሚያወጣ ይደነግጋል። ከ3 ሺህ 500 በላይ የሲቪል ማኅበራትን ለሚቆጣጠረው ለኤጀንሲው ይህ አዲስ አሰራር ጫና የሚፈጥር ነው ሲልም ይሄው በአይሲኤንኤል የተዘጋጀው ሰነድ ያስረዳል። መመሪያው ሰነዶች ስለሚገኙባቸው ምንጮች “ሌሎች ከድርጅቱ፣ ከመንግሥት፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እና ከሦስተኛ ወገኖች በተለያዩ መንገዶች የሚገኙ ሰነዶችና መረጃዎች መሠረት በማድረግ ይከናወናል” ሲል ገልጿል። ይህም ኤጀንሲው የሕግ ሥነ ሥርዓትን ያልተከተሉ ወይም ሕገወጥ አካሄዶችን በመከተል ጭምር የሚያገኛቸውን ማስረጃዎች እንዲጠቀም በር የሚከፍት፣ ዓለም አቀፍ ብሎም የአገሪቱን ሕግ ያልተከተለ አካሄድ ነው ሲል ሰነዱ ይተቻል።

“ምርመራ እንደሚካሄድ ይፋ ማድረጉ የምርመራውን ሂደት ያደናቅፈዋል ብሎ ኤጀንሲው ካመነ ጉዳዩን በምስጢር በመያዝ ድንገተኛ ምርመራ ማከናወን ይችላል” የሚለው የመመሪያው ክፍልም አግባብነት ከሌላቸው ድንጋጌዎች መካከል ተመድቧል። በተለይም የአፍሪካ የሰብዓዊ እና የሕዝቦች መብቶች ቻርተርን ድንጋጌ ይቃረናል ሲል ሰነዱ ወቅሷል። ዋና አዋጁ ምዝገባን በተመለከተ በዝርዝር መስፈርቶችን ማስቀመጡን አቶ ደበበ ይናገራሉ። እነዚህ መመሪያዎች በተለይም ክልከላ የሚመስሉ እና ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጣቸውን ያክላሉ። አንዳንዶቹ ከአዋጁ ጋር እስከመቃረን የሚደርሱ እንደሆነ እና ይህም አሳሳቢ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለዚህም በምሳሌነት ከቀረቡት መካከል ምዝገባን በሚመለከተው መመሪያ አንቀጽ አምስት ንዑስ ቁጥር ሦስት ስር ለምዝገባ አስፈላጊ ስለሆኑ ሰነዶች የሚደነግገው አንቀጽ ይጠቀሳል። ለምዝገባ መቅረብ ስላለበት ቃለ ጉባኤ የሚደነግገው ይህ ድንጋጌ “ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ያካተተ ሆኖ” መቅረብ አለበት የሚለው አግባብ ያልሆነ ቅድመ ሁኔታ እንደሆነ ሕግ ባለሙያው አቶ ደበበ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በእናት ሕጉ ላይ ያልተደነገጉ አዳዲስ ቅድመ ሁኔታዎችን እነዚሁ መመሪያዎች ይዘው መምጣታቸውንም የሕግ ባለሞያው ይናገራሉ። ምዝገባን በሚመለከተው መመሪያ ውስጥ ራዕይ፣ አላማ እና ግብን የተመለከቱ ድንጋጌዎች የተጨመሩ ሲሆን በዋና አዋጁ ውስጥ ግን ይህንን የተመለከተ ነገር እንደሌለም ገልጸዋል።

ኤጀንሲው ምን ይላል?

የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላው ኤጀንሲው መመሪያዎቹ ከመጽደቃቸው በፊት የተለያዩ ውይይቶችን እያካሄደ እንደሚገኝ እና የቀረቡ ቅሬታዎችንም እንደሚያስተናግድ ተናግረዋል። እስካሁን ድረስ አራት መመሪያዎች የጸደቁ ሲሆን አንድ መመሪያ ቦርዱ እንዲያጸድቀው መቅረቡን ተናግረዋል። የአስተዳደር ወጪን የሚያስተዳድር፣ የሲቪል ማኅበራትን ፈንድ የሚያስተዳድር፣ የሞያ ማኅበራትን የሚያስተዳድር እንዲሁም ሂሳብ፣ ንብረትን እና ግዢን የሚመለከቱት መመሪያዎች መጽደቃቸውን ተናግረዋል።

ሕዝባዊ መዋጮን የሚመለከተው መመሪያንም የኤጀንሲው ቦርድ እንዲያጸድቀው የቀረበ መሆኑን አቶ ፋሲካው ተናግረዋል። እንዲሁም አምስት መመሪያዎች በውይይት ላይ ሲሆኑ ሌሎች ስምንት መመሪያዎች በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም አክለዋል። አቶ ፋሲካው አክለውም ከሃምሳ የሚበልጡ የሲቪል ማኅበራት ጥምረቶችን በመሰብሰብ ረቂቆቹን እንዲመለከቱ ብሎም አስተያየታቸውን ሙሉ ይሰበሰባል። እንዲሁም በእያንዳንዱ መድረክ የሚነሱ ሃሳቦች እንደሚመዘገቡ እና ሁሉንም ለማሻሻል እንደሚሞክሩም ተናግረዋል።

“የማንቀበለው ሃሳብ ካለም በግልጽ እናስቀምጣለን፤ ይህ ሁሉም ተመዝግቦ ወደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንዲላክ ይደረጋል” ሲሉም አቶ ፋሲካው ያክላሉ። መንግሥት በቅርቡ የሦስት የሲቪል ማኅበራትን ፈቃድ አግዷል። የኖርዌይ የስደተኞች ካውንስል፣ የድንበር የለሽ ሃኪሞች የፈረንሳይ ቅርጫፍ እንዲሁም አል ማክቱም የተሰኙት የሲቪል ማኅበራት ፈቃድ ለሦስት ወራት ታግዶ ምርመራ እየተካሄደ ነው።

ይህንን ጨምሮ የተወሰኑ በሲቪል ማኅበራት ላይ የአቋም ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ፍንጮች መታየታቸውን ብሎም ስጋቶች እንዳሉ አቶ ደበበ ይናገራሉ። አቶ ፋሲካው በበኩላቸው መንግሥት የሲቪል ማኅበረሰቡ አሁንም በርካታ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ እንደሚያምን ብሎም የሻከረ ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለ ይናገራሉ። መመሪያዎቹም ምቹ የሥራ ሁኔታ እንዲፈጠር ብሎም በሕግ እና በሥርዓት የሚመራ ዘርፍ እንዲፈጠር በማሰብ እንደሆነ አክለዋል። በመመሪያዎቹ ይህንን የሚቃረን ነገር ተካቶ ከሆነም ከመጽደቃቸው በፊት እንደሚሻሻል ኃለፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *