በጋምቤላ ክልል ባለፈው ሳምንት ተከስቶ ለአምስት ሰዎች ሞት ምክንያት ከሆነው ግጭት ጀርባ፣ በክልሉ በተካሄደው ምርጫ ተሳታፊ የነበረውና ራሱን የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) በሚል ስያሜ መጥራት የጀመረው፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ፍትሕ ለሰላምና ልማት ዴሞክራቲክ ንቅናቄ እንደሚገኝበት ተገለጸ፡፡ የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡመድ ኡጁሉ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በጋምቤላ ባለፈው ሳምንት የተከሰተው ግጭት መንስዔ፣ በክልሉ በተካሄደው ምርጫ ተሳታፊ የነበረው የጋምቤላ ሕዝቦች ፍትሕ ለሰላምና ልማት ዴሞክራቲክ ንቅናቄ (ጋሕፍሰልዴን) ነው፡፡ ፓርቲው በምርጫው ከተሸነፈ በኋላ ወደ ጫካ በመግባት ራሱን የጋምቤላ ነፃነት ግንባር ብሎ በማወጅ ለሽብር መንቀሳቀስ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ጨምረው እንዳስታወቁት፣ ፓርቲው ከምርጫው በኋላ ሽብር ለመፈጸም እንዲመቸው በአሸባሪነት ከተፈረጁት የሕወሓትና የሸኔ ቡድኖች ጋር በመተባባር የተለያዩ አፍራሽ ድርጊቶችን እያከናወኑ ናቸው፡፡ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ በተደጋጋሚ በግጭት የሚታወቁትን ሁለቱን ብሔረሰቦች ማለትም አኙዋክና ንዌር፣ እንዲሁም በክልሉ የሚገኙትን አምስቱን ብሔረሰቦችና ሌሎች ብሔረሰቦችን ለማጋጨት ጥረት ማድረጋቸው እንደ ተስተዋለ ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ቡድኑ ባለፈው ሳምንት እሑድ ነሐሴ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀጀቤ በሚባለው አካባቢ በወጣቶች ላይ ጥቃት ፈጽሞ የአንድ ሰው ሕይወት ወዲያው እንደጠፋ፣ በዚህም ሳቢያ ሌሎች ሥርዓተ አልበኞች ድንጋይ ውርወራ በመጀመራቸው የአራት ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፤›› ሲሉ አቶ ኡመድ አስረድተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በክልሉ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የአምስት ሰዎች ሕይወት እንደጠፋ ተናግረዋል፡፡

ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የክልሉ መንግሥት አፋጣኝ ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩንና የፈጠሩት አካላት በቀጥታ ባይገኙም፣ ከተማ ውስጥ ሆነው የድርጊቱ ተባባሪ የነበሩትን አካላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል፡፡ ድርጊቱ ‹‹ከብሔር ግጭት ጋር እንደማይያያዝ በማኅበረሰብ ውይይቶች የተረጋገጠ ነው›› ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ በቀጥታ የጥፋቱ ተባባሪ ናቸው በተባሉት ላይ የማያዳግም ዕርምጃ ይወሰዳል በተባለው መሠረት ዕርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ወደ ጋምቤላ ክልል የተመደቡ አዳዲስ የፌደራል አባላትና የክልል የፀጥታ አካላት ድርጊቱ በተፈጸመበት ዕለት የሥጋት ቀጣና በተባሉት አካባቢዎች ቀኑን ሙሉ ቅኝት ሲያደርጉ መዋላቸውን፣ ይህንን አከናውነው አመሻሹን ወደ ከተማ በሚመለሱበት ጊዜ ጥቃቱ እንደተፈጸመ የተናገሩት አቶ ኡመድ፣ ጥቃቱን የፈጸሙት ብዛት እንደሌላቸውና በቅር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚደመሰሱ ተናግረዋል፡፡

በጥቃት ፈጻሚነት የተፈረጀው ፓርቲ የምርጫ ውጤት በፀጋ ሳይቀበል ወደ ሽብር ድርጊት መግባቱ ተገልጾ፣ ወጣቱ ኃይል የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የተነሳውን ኃይል ጫካ በመግባት መቀላቀል እንደማይገባውና ተታለው ለእኩይ ተግባር የተሠለፉ ወጣቶችን ትምህርት ሰጥቶ ወደ ኅብረተሰቡ የመቀላቀል ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ጥቃት ጀርባ ያለው ዋነኛ ድርጅት አገር ውስጥ እንደሌለና ሰሜን ሱዳን ካርቱም ውስጥ እንደሚገኝ አቶ ኦሞድ ጠቁመው፣ ድርጅቱ ሱዳን ተቀምጦ አቅጣጫዎች እየሰጠ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ እየሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በመደበኛነት ባይሆንም በሽብር የተፈረጀው ሕወሓት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በከተማዋ ውስጥ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ ማንኛውም ዓይነት የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ መከልከሉን፣ ከተማዋ በፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገላት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ኅብረተሰቡን የማረጋጋት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ የተጣለው የተሽከርካሪ ሰዓት ገደብ እንደሚነሳ አስታውቀዋል፡፡

ሪፖርተር በጋምቤላ ከተማ ባደረገው ቅኝት የከተማዋ የንግድና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በጊዜ የሚዘጉ ሲሆን፣ በአውራ ጎዳናዎችና በመጋቢ መንገዶች የነዋሪዎች እንቅስቃሴ በተለይም ከምሽት 12 ሰዓት በኋላ አነስተኛ ነው፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *