የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ኃላፊ ሰማንታ ፓወርና የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ የመጀመሪያ ውይይታት አደረጉ።
ሰማንታ ፓወር በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳስታወቁት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተባባሰ በመጣው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ላሉት አስቸኳይነት የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል። ሰማንታ ፓወር በዚሁ መልዕክታቸውም ላይ ከቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ጋር መገናኘታቸው በጣም ጥሩ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው ተሰየሙት ኦባሳንጆ በቀጠናው የሚገኙ ዋነኛ ተዋናዮችና የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር እንደሚሠሩ ተጠቁሟል። የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ ልምድ እና በአፍሪካ መርነት (ፓን አፍሪካኒዝም) ላይ የተመሠረተ አስተሳሰብ እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በቀጠናው ስላለው ሁኔታ ያላቸው ከፍተኛ እውቀት ደግሞ ወሳኝ ነው ተብሏል።
ከፍተኛ ተወካዩም በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ወደ አካባቢው እንደሚመጡ ይጠበቃል። በትግራይ ኃይሎችና በፌደራሉ መንግሥት መካከል የተነሳው ጦርነት አስረኛ ወሩን ያስቆጠረ ሲሆን ወደ አጎራባቾቹ አፋርና አማራ ክልሎች ተዛምቶ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን አፈናቅሏል። በአፋር ክልል ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ112 ሺህ በላይ መድረሱን የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ አስታውቋል።
በትግራይ ወደ 900 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በረሃብ አፋፍ ላይ የሚገኙ ሲሆን ሌሎች 5 ሚሊየን የሚሆኑት የክልሉ ነዋሪዎች ደግሞ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ገልጿል። የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ ባደረጉት ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ተዋጊዎች ተገድለዋል።
ከወራት በፊት የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ወታደሮቹን ከመዲናዋ መቀለ እንዳስወጣ ቢገልፅም ህወሓት በበኩሉ መቀለን በኃይል እንደተቆጣጠረ ተናግሯል። የፌደራሉ መንግሥት የተኩስ አቁም በማወጅ ከትግራይ ለቆ ከወጣበት ምክንያቶች መካከል አብዛኛዎቹ የህወሓት የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎች በመገደላቸውና በመታሰራቸው እንዲሁም የቀሩትን ጥቂት የህወሓት አመራሮች ለመያዝ ሲባል ጦርነቱን መቀጠል አስፈላጊ ባለመሆኑ ነው ተብሏል።
በክልሉ ያሉ ነዋሪዎች የግብርና ወቅታቸውን እንዳይስተጓጎል፣ የረድዔት ድርጅቶች የበርካቶችን ህይወት እንዲያድኑ እድል ለመስጠት ነው የሚል መሆኑንም አስታውቋል። ህወሓት በስምምነት ላይ የተደረሰ የተኩስ አቁም እንደሚቀበል ያስታወቀ ሲሆን ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ከክልሉ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል ኃይሎች ወጥተው ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቀው ይገኝበታል።
ባለፉት ወራት ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን እንዲመረመሩ እንዲሁም ቴሌኮም፣ መብራትና የአውሮፕላን በረራን ጨምሮ የተቋረጡ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲጀመሩም ጠይቋል። በአሁኑ ወቅት የጦርነት ክተት ጥሪ በየቦታው በሚቀርብበት በዚህ ወቅት ግጭቱ ወደ አዲስ እና ይበልጥ ደም አፋሳሽ ወደ ሆነ ምዕራፍ ሊያመራ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
ምንጭ – ቢቢሲ