የህወሓት አማጺያን ባለፉት ቅርብ ሳምንታት የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) የሆኑ የእርዳታ መጋዘኖችን መዝረፋቸው ተገለጸ።

የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተልዕኮ ዳሬክተር ሾን ጆንስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት የህወሓት አማጺያን በደረሱባቸው ስፍራዎች የሚገኙ የእርዳታ መጋዘኖችን ዘርፈዋል ብለዋል። የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያ ተልዕኮ ዳይሬክተር ሾን ጆንስ “ወታደሮችና የታጠቁ ሰዎች ከዜጎች ምግብ ሰርቀዋል። በተለይ ህወሓት በገባባቸውና ጦርነት በከፈተባቸው ሁሉም የአማራ አካባቢዎች መጋዘኖችን ዘርፏል፤ ተሽከርካሪዎች ዘርፏል። ውድመት ፈፅሟል” ብለዋል ዳሬክተሩ።

በትግራይ ክልል በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት አማጺያን መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግደሉ እና ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ስለመፍጠሩ ተዘግቧል። የዩኤስኤድ የኢትዮጵያ ተልዕኮ ዳሬክተር ሾን ጆንስ ለኢቢሲ ሲናገሩ፤ “በተለይ የህወሓት ኃይሎች በገቡባቸው የአማራ ክልል አካበቢዎች በርካታ የእርዳታ መጋዘኖቻችን ስለመዝረፋቸው እና መጋዘኖቹ ባዶ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ አለን” ብለዋል።

ዳሬክተሩ አክለውም “ህወሓት ሁኔታዎችን ያለአግባብ እየተጠቀመ እንደሆነ አምናለሁ። ከተረጂዎች ላይ በኃይል እርዳታ እየነጠቀ አንደሆነ ይሰማናል፤ የምናውቀው ሃቅ ግን የህወሓት ኃይሎች በገቡባቸው አካባቢዎች ሁሉ የእርዳታ መጋዘኖቻችን ዘርፈዋል” ብለዋል። ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግሥት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ የአሜሪካ ተወካይ በተመሳሳይ “በአማራ ክልል ውስጥ የእርዳታ መጋዘን በህወሓት ኃይሎች መዘረፉን” ተናግረው ነበር።

በተጨማሪም ከቀናት በፊት ዩኤስኤይድ ለአማጺያኑ የኃይል ሰጪ ምግብ እርዳታ እየሰጠ ነው የሚለውን ክስ ውድቅ ባደረገበት መግለጫው ላይ “በአብዛኛውን ጊዜ በግጭት አካባቢዎች ታጣቂዎች እርዳታ ከሚፈልጉ ሰዎች እንደሚሰርቁ” አመልክቶ ነበር።

ሾን ጆንስ "

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያ ተልዕኮ ዳሬክተር ይህን ማለታቸውን ተከትሎ የህወሓት አመራሮች እና የፌደራሉ መንግሥት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያሉት ነገር የለም። ከዚህ ቀደም የህወሓት አማጺያን እና የፌደራሉ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ፍሰትን በማደናቀፍ በተደጋጋሚ እርስ በርስ ይወቃቀሳሉ።

የፌደራሉ መንግሥት በተደጋጋሚ የህወሓት አማጺያን ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ የሰብዓዊ እርዳታ ቁሶች ወደ ክልሉ እንዳይገቡ እንቅፋት እየሆነ ነው እንዲሁም ዘረፋ ይፈጽማል ሲል ቆይቷል። የህወሓት አመራሮች በበኩላቸው የፌደራሉ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ትግራይ እንዳይደርስ መንገዶችን ዘግቷል ሲሉ ይከሳሉ።

ሾን ጆንስ “ማንኛውም የሰብዓዊ እርዳታ ጣልቃ ገብነት ወይም ስርቆት ተቀባይነት የሌለውና ለተቸገሩ ሰዎች እርዳታ እንዳይደርስ የሚያደርግ ነው” ብለዋል።በትግራይ ወደ 900 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በርሃብ ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ፤ ሌሎች 5 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብሏል የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት።

ባለፉት ሁለት ወራት ወደ አማራና አፋር ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት ምክንያት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተጨማሪ ሰዎች በሁለቱ ክልሎች ውስጥ ተፈናቅለው እርዳታ እንደሚሹ ክልሎቹ መግለጻቸው ይታወቃል። በዘጠኝ ወራቱ የጦርነት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ የእርዳታ ሠራተኞች በሚሊየን ለሚቆጠሩ ሰዎች ለመድረስ የምግብ ክምችት እንደሚያልቅባቸው ባለፈው ሳምንት የዩኤስኤድ ኃላፊ መናገራቸው ይታወሳል።