በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ ውስጥ በአንድ ቀላል ተሽከርካሪ ላይ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ በሰዎች ላይ የሞትና የመቁሰል ጉዳት መድረሱን የአካባቢው ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ገለጹ።

ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ጥቃቶች በሚፈጸሙበት የክልሉ መተከል ዞን ውስጥ ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 25/2013 ዓ.ም በቡለን ወረዳ በባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) ላይ በተፈጸመው ጥቃት አምስት ሰዎች ሲገደሉ ሁለት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። ጥቃቱ በቡለን ወረዳ ከዶቢ ቀበሌ ወደ ቡለን ከተማ ሲጓዙ በነበሩ ባጃጅ ላይ ታጣቂዎች ተኩስ በመክፈት ግድያውን መፈጸማቸውንና በክስተቱ ላይ ተጨማሪ መረጃ እያሰባሰቡ እንደሆን የመተከል ዞን የፖሊስ መምሪያ ኃላፊ አብዲ ጎረና ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በታጣቂዎቹ በተከፈተው ተኩስ ቆስለው የተረፉት ሁለት ሰዎች ለህክምና እርዳታ ወደ ቡለን ሆስፒታል መወሰዳቸውም ተነግሯል። ቢቢሲ በአካባቢው ካለ ሆስፒታል ምንጭ ማረጋገጥ እንደቻለው በጥቃቱ የቆሰሉት ሁለት ሰዎች ህክምና እያገኙ መሆናቸውንና “አንደኛው በሦስት ጥይት የተለያየ ቦታ የተመታ ሲሆን ሌላኛው በጀርባው በኩል ተመትቶ” መቁሰሉን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የህክምና በለሙያ ተናገረዋል።

በተጨማሪም በጥቃቱ የተገደሉት የአምስቱ ሰዎች አስከሬን ወደ ዶቢ መመለሱን የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል። ጉዳት ደርሶባቸው ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሌላ ሆስፒታል መላክ ያለባቸው ሁለቱ ሰዎች አምቡላንስ ባለመኖሩ ምክንያት እስካሁን በሆስፒታሉ እንደቆዩ በቡለን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚሰሩ ባለሞያ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከጥቃቱ ከተረፉት ሰዎች መካከል የሆኑትና ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንደኛው ግለሰብ እንዳሉት ጥቃቱን የፈጸሙት የአካባቢው ታጣቂዎች ናቸው።

ዛሬ ማክሰኞ ጠዋት ሁለት ሰዓት አካባቢ “ታጣቂዎቹ መንገድ ላይ አድፍጠው ጠብቀው ስንጓዝበት በነበረው ባጃጅ ላይ ተኩስ ከፍተው ግድያውን ፈጽመዋል” ሲሉ ከጥቃቱ ቆስለው የተረፉት ግለሰብ ተናግረዋል። በጥቃቱ በተፈጸመበት ባጃጅ ላይ በጠቃላይ ሰባት ሰዎች ተሳፍረው ወደ ቡለን ከተማ ሲጓዙ የነበረ ሲሆን የተገደሉት ሁሉም አዋቂ ወንዶች መሆናቸው ተገልጿል። በጥቃቱ የባጃጁ ሹፌርን ጨምሮ አምስት ሰዎች በጥቃቱ ስፍራ ወዲያውኑ ሲሞቱ ሁለቱ በሕይወት መትረፋቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። በምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኘው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ታጣቂዎች በሚፈጽሙት ጥቃቶች እጅግ በርካታ ሰዎች መገደላቸው በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል።

በተለይ በመተከል ዞን ውስጥ ባሉ አካባቢዎች የሚፈጸሙት ጥቃቶች የተደጋጋሙ ሲሆን የፌደራል መንግሥቱና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በሚወስዷቸው የአጸፋ እርምጃዎች በርካታ ታጣቂዎች መገደላቸውና መያዛቸው ተዘግቧል። ከሱዳን ጋር በሚዋሰነው በዚህ ክልል ውስጥ ባለው የመተከል ዞን ውስጥ በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ጥቃቶች የተነሳ ከፌደራል መንግሥትና ከክልሉ በተወጣጣ የጸጥታ ኃይል የሚመራ የዕዝ ማዕከል [ኮማንድ ፖስት] ስር እንዲሆን መደረጉ ይታወሳል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *