ገለልተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አጣሪ ጉባኤ የማቋቋም ተሞክሮዎች

በኢትዮጵያ ገለልተኛ አጣሪ ጉባኤን በተመለከተ ሁለት የቅርብ ተሞክሮዎች አሉ።  ይሁን እንጅ ከነዚህ በፊትም በደርግ ጊዜ 15 አባላት የነበሩት አጣሪ ኮሚቴ ነበር፡፡ይህ አጣሪ ኮሚቴ በንጉሱ ጊዜ የነበሩ ከ150 በላይ የሚደርሱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ፈፅመውታል የተባሉ ወንጀሎችን ለማጣራት በደርግ ወታደራዊ መንግስት የተቋቋመ ነው፡፡ ወታደራዊ መንግስቱ ይህንን አጣሪ ኮሚቴ አቋቁሙ የነበረ ቢሆንም የኮሚቴው ሪፖርት ለህዝብ ይፋ አልተደረገም፡፡

ከዚህ በመቀጠል ከሁለቱ የቅርብ ተሞክሮዎች የመጀመሪያው በጋምቤላ ብሄራዊ ክልል በ1996 የተከሰተውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማጣራት በአዋጅ ቁጥር 398/1996 የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን ነው። ይህ ኮሚሽን ምንም እንኳን በአዋጅ ቢቋቋምም ሪፖርቱ ለህዝብ ይፋ ያልተደረገ እና ገለልተኛ ያልነበረ በገዢው ፓርቲ ተፅዕኖ ስር የወደቀ ኮሚሽን ነበር። ሁለተኛው የአጣሪ ኮሚሽን ማቋቋም ተሞክሮ ከ1997 ምርጫ በኋላ የተፈፀሙ ከፍተኛ ግድያዎችን ወይም የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት በታህሳስ 1998 በአዋጅ ቁ. 478/2005 የተቋቋመው አጣሪ ጉባኤ ነው፡፡ ይህ ገለልተኛ አጣሪ ጉባኤ መንግስት ከምርጫ በኋላ የወሰዳቸውን እርምጃዎች ተመጣጣኝነት እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ለማጣራት የተቋቋመ ነው፡፡ አጣሪ ጉባኤው በመንግስት ተፅዕኖ ሲደረግበት የነበረ ሲሆን አብዝሃኞቹ አባላት በያዙት ገለልተኛ አቋም ችግር ደርሶባቸዋል። አጣሪ ጉባኤው በሪፖርቱ መንግስት የወሰዳቸው እርምጃዎች ተመጣጣኝ አለመሆናቸውን ከአስር የኮሚቴው አባላት ስምንቱ ደግፈውት ውሳኔው ተላልፏል። ይህ ሪፖርት ፖርላማው ከአመታዊ መዝጊያ ቀናት በፊት በመበተኑ ሪፖርቱ እንዳይሰማ የተደረገ ሲሆን የአጣሪ ኮሚሽን አባላቱም ያሳለፉትን ውሳኔ እንዲቀይሩ በመንግሥት ጫና እና ማሥፈራሪያ ሲደረግባቸው ነበር። በዚህም የተነሳ የአጣሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ እና አንድ አባል በምስል የተደገፈ ማሥረጃውን በመያዝ ከሀገር ተሰደዋል

ይህ ይሁን እንጅ መንግስት ሌሎች ገለልተኛ ያልሆኑ ሰዎችን በመምረጥ ውሳኔው ተቀልብሶ መንግስት የወሰዳቸው እርምጃዎች ተመጣጣኝ ናቸው በሚል በመቀየር በጥቅምት 1999 ለፖርላማ እንዲቀርብ ተደርጓል፡ ስለሆነም እነዚህን የሀገር ውስጥ ተሞክሮዎች ከገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን አመሰራረትና አሰራር መርሆች አንፃር ብቁ እና ገለልተኛ ነበሩ ለማለት አያስችልም።

ለዚህም በዋና ማሳያነት ስንመለከት፦

1ኛ አባላቱ ምንም እንኳን የህግ ሙያ እና ልምድ ያላቸው ጥቂት አባላት ቢኖሩም አብዛኞቹ አባላት ከእምነት ተቋማት እና ሌሎች ቦታዎች የተመረጡ በመሆኑ ማጣራቱ በሚፈልገው የሙያ ችሎታ ላይ ግንዛቤ እና ልዩ የምርመራ ብቃት (expertise) የሌላቸው ነበሩ። ይህም የማጣራቱ ሂደት በሚጠይቀው የሙያ ሂደት (የሰብአዊ መብቶች እውቀት) ሳይኖራቸው አባላቶች ድምፅ እንድሰጡ ያደረገ እና የአጣሪ ኮሚሽን መርህን ያልተከተለ ነበር። 2ተኛ የ1997 ምርጫን ተከትሎ የተቋቋመውን ስንመለከት የመንግስት ግልፅ ጣልቃ ገብነት እና የኮሚሽኑ አባላት ገለልተኛ ሆነው ስራቸውን እንዳያከናውኑ የተደረገበት እና ያስተላለፉት ውሳኔ የተቀለበሰበት ነበር። 3ተኛ ጋምቤላ ላይ ለተከሰተው የሰብአዊ መብት ጥሰት የተቋቋመው መርማሪ ኮሚሽን የመንግስት ቁርጠኝነት የሌለበት የነበረ ሲሆን ሪፖርቱም እንዳይወጣ ተደርጓል።

ከእነዚህ ተሞክሮዎች ልምድ መውሰድ እንደሚቻለው ለሚቋቋሙ ኮሚሽኖች መንግስት ቁርጠኛ፣ ገለልተኛ እና የአጣሪ ኮሚሽን ውሳኔዎችን የሚቀበል መሆን እንዳለበት ፤ በሚፈለገው የሙያ ችሎታቸው ላቅ ያሉ አባላትን ማካተት እና የአባላቱን ነፃነት እና ገለልተኝነት ማክበር መቻል እንዳለበት ነው። በመሰረቱ እነዚህ የተቋቋሙ ሁለት ኮሚሽኖች መንግስት ከወሰዳቸው እርምጃዎች እና ከፈፀማቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በቀጥታ የተገናኙና የመንግሥትን እርምጃዎችን ለማጣራት የተቋቋሙ ናቸው ብለን ልንወስዳቸው እንችላለን። ለዚህም ነው በአባላቱ ላይ የማሥፈራራት፣ የማሳደድ እና ሪፖርቶቻቸው እንዲቀለበሱ እና እንዳይወጡ የተደረጉት። ይህ ይሁን እንጅ መንግስት እራሱ በግልፅ እና በቀጥታ የፈፀማቸውን ጥሰቶች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ አጣሪ ኮሚሽን ማቋቋሙ እንደ አንድ አዎንታዊ እንቅሥቃሴ ሊወሰድ ይችላል።

ከዚህ አንፃር የአሁን ጊዜ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት ያለውን ቁርጠኝነት ስንመለከት በመንግሥት በኩል ከ1997 እና 1996 ከተቋቋሙት በተሻለ ቁርጠኝነት አለ ለማለት አያስደፍርም። ይህም ሲባል ለምሳሌ የበፊት ተሞክሮዎችን ስንመለከት ቀጥታ መንግስት የወሰዳቸው እርምጃዎችን መንግስት ደፍሮ ለማጣራት አንድ እርምጃ በመንቀሳቀስ አጣሪ ኮሚሽኖችን አቋቁሟል። ነገር ግን በአሁን ጊዜ የሚፈፀሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በአይነት እና ባህሪ ለየት ያሉ አለፍ ሲልም በአብዝሃኛው መንግስታዊ ባልሆኑ አካላት የሚፈፀሙ ሆነው እያለ ከመንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ባለመኖሩ አጣሪ ጉባኤዎችን ማቋቋም አልተቻለም። ይህ ሆኖ እያለ ምንም እንኳን እየተከሰቱ ባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ መንግስት ከተጠያቂነት ማምለጥ የሚችልበት ሁኔታ ባይኖርም ከቅርብ ጊዜ ወድህ እንደ መተከል እና በመሳሰሉት የሀገሪቱ አካባቢዎች ለተከሰቱ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መንግስት ገለልተኛ አጣሪ በማቋቋም ለዜጎች ሰብአዊ መብት መከበር ቁርጠኛ መሆኑን ማሳየት ይገባዋል።

የገለልተኛ አጣሪ ጉባኤ አስፈላጊነት ከየት እስከ የት ላለው ጥሰት?

ባለፉት ሶስት አመታት በኢትዩጵያ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን የማሻሻል አንዳንድ እርምጃዎች ተወስደዋል። ህጎችን በማሻሻል፣ ገለልተኛ ተቋሞችን ለመፍጠር የሚያስችሉ መሰረቶችን በመጣል፣ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር በማድረግ እና ሌሎች  እርምጃዎችን በመውሰድ ጥሩ ምልክቶች ታይተዋል።  ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በነጻነት የሚንቀሳቀሱበትን ምህዳር በማስፋት እና ለአንዳንድ የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ተዘግቶ የቆየውን በር በመክፈት የሚበረታቱ በጎ እርምጃዎች ታይተዋል። ምንም እንኳን እነዚህ በጎ የሚባሉ የለውጥ ምልክቶች ቢታዩም ጎን ለጎን ሀገሪቷ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ቀውሥ ውስጥ የገባችበት እና ዜጎች ለጅምላ ግድያ፤መፈናቀል፣ በማንነት ላይ ላነጣጠሩ ጥቃቶች፣ ለጦርነት እና የደረሱበት አለመታወቅ ወይም ታፍኖ መሰወር የተዳረጉበት በርካታ ክስተቶች ተፈጽመዋል። ባለፉት ጥቂት አመታት በሀገራችን የተከሰቱትን ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች እና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንደሚከተለው በመጠኑ እንመልከት፡፡

የቡራዩ ብሔር ተኮር ጥቃት ሲታወስ

በሀገራችን ህዝባዊ እምቢተኝነትን ተከትሎ የመጣው ለውጥ ከገጠሙት ሰፊ ተግዳሮቶች አንዱ በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎችች እጅግ አሰቃቂ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መፈፀም ነው። ከእነዚህ ክስተቶች መካከል በቡራዩ ከመስከረም 03 ቀን 2011 እስከ መስከረም 05 ቀን 2011 የተፈፀመው የዜጎች እልቂት አንዱ ነው። ይህንን የዜጎች እልቂት በጊዜው “መንግሥት በማጣራት ላይ ነው” የሚል መግለጫዎች የተሰጡ ቢሆንም እስካሁን ጉዳዩ የሚገኝበት ሁኔታን በተመለከተ ለህዝብ የተጣራ እና ግልፅ የሆነ  መልስ  በመንግስት ደረጃ አልተሰጠም።

ሌሎች የከፉ ጥቃቶች በተከታታይ ሲፈጸሙ በመቆየቱ፤ እንዲሁም የመንግስት እና የሕዝብን ቀልብ የሚስቡ ሌሎች በርካታ እና አዳዲስ ሁኔታዎች ያለሟቋረጥ ይከሰቱ ስለነበር የቡራዩን ጉዳይ ተደባብሶ እንዲቀር ምክንያት ሆኗል። አጥፊዎች ተብለው እና ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ስለመኖራቸው በወቅቱ ለሕዝብ ይፋ የተደረገ ቢሆንም የፍትህ ሂደቱ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ፣ የተቀጡም ሰዎች ካሉ ስለ ፍርድ ሂደቱ እና ምን እንደተቀጡ ለሕዝብ የተገለጸ ነገር የለም። ይህም ‘እውነት’ በየቀኑ በሚከሰቱ ሁነቶች ተሸፍና እንድትቀር አድርጓል። ነገር ግን መንግስት እነዚህን ጥሰቶች በአግባቡ የማጣራት ፣ የመመርመር እና ለተጎጂ ዎች ፍትህ የመስጠት ህጋዊ ግደታ አለበት። ስለሆነም የተፈፀሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እውነታውን ለህዝብ በጊዜ እና በተአማኒነት ለማድረስ ተጎጅዎችም እውነታውን የማወቅ እና ፍትህ የማግኘት መብታቸውን ለማስከበር ነፃ እና ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን ማቋቋም አሥፈላጊ ነው።

መተከል

ባለፉት ሶስት አመታት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን እና በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የተከሰቱት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ብዙዎችን ለህልፈት የዳረጉ ከመሆናቸውም በላይ በመቶ ሺ የሚቆጠሩትን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀሉ ክስተቶች ናቸው። በክልሉ ውስጥ ያለውን አሳሳቢ የሆነ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) “መቆምያ ያጣው የንፁሃን እልቂት” በሚል ርዕስ ባወጣው ጠቅለል ያለ ዘገባ  በክልሉ ከነሃሴ 2012 እስከ ታህሳስ 2013 ባሉት 5 ወራት ውስጥ ብቻ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ከ500 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከ100 ሺ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጿል። ይህ የግድያ እና የማፈናቀል እርምጃ በተመለከተ ከመንግስት በተደጋጋሚ እንደሚገለጸው ድርጊቱን የሚፈጽሙት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሸማቂ ኃይሎች መሆኑን ነው። ጥቃቶቹን ተከትሎም መንግስት በእነዚህ አማጺ ኃይሎች ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል። ይሁን እና የመንግስት እርምጃ ጥቃቱ ለማስቆም ባለመቻሉ በርካታ ንፁሃንን ከተደጋጋሚ ጥቃት ሊታደጋቸው ሳይችል ቆይቷል።

ይህ ችግር ለረዥም ጊዜ እልባት ሊያገኝ ያልቻለበትን ምክንያቶች በተመለከተ ብዙ መላምቶች እና ግምቶች ቢኖሩም በዋነኝነት ግን እንደ መንስኤ የሚጠቀሰው እና በመንግሥትም ጭምር እንደ ዋነኛ ችግር የተጠቀሰው በክልሉ ውስጥ በተለያየ የእርከን ደረጃ ላይ የሚገኙ   በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እልቂቱ እንዲከሰት እና እንዲባባስ የሚደግፉ እና የሚያበረታቱ የመንግስት አመራሮች መኖራቸው ነው። ነገር ግን መንግስት ይህንን ጉዳይ ከማመን እና ለተጎጅዎች የእለት ፍጆታ ድጋፍ ከመስጠት በዘለለ ለደረሰባቸው የሰብአዊ መብት ጥሰት ፍትህ  እና ለደረሰባቸውም በገንዘብ የሚተመን ጉዳት ተመጣጣኝ የሚሆን ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ አልተቻለም። በመሆኑም በክልሉ ውስጥ በቅርብ ጊዜ በደረሱት ጥቃቶች ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ፣ ምን ያህል ሰው እንደተፈናቀለ፣ ምን ያህል የንብረት ውድመት እንደደረሰ እና ምን ያህልም ሰው ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰበት መሆኑን በአግባቡ ሰንዶ ሪፖርት የሚያቀርብ፣ ተጎጅዎችን መልሶ ማቋቋም ስለሚቻልበት ሁኔታ በቂ ጥናት አድርጎ ሃሳብ የሚያቀርብ፣ ለተጎጂዎች ተመጣጣኝ የሆነ የጉዳት ካሳ እንዲሰጥ እና አጥፊዎችም ለፍርድ ቀርበው ተጠያቂ የሚሆኑበትን መንገድ የሚያመቻች  ገለልተኛ የሆነ አጣሪ ኮሚሽን ማቋቋም አስፈላጊና ጊዜ የማይሰጠው እንዲሁም ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ የሚችል መንገድ ነው።

በትግራይ ክልል ያሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ጉዳይ

በቅርቡ መንግስት የህግ ማስከበር እርምጃ ነው ባለው በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ በተካሄደ ኦፕሬሽን በርካታ ሰዎች ለተለያዩ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተዳርገዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም በትግራይ ክልል የሚኖሩ ዜጎች እስካሁንም ድረስ በቀጠለ ሁኔታ በአንዳንድ አካባቢዎች የመብራት፣ የኢንተርኔት እንዲሁም የህክምና እና ሌሎች አገልግሎቶችን ማግኘት ያልቻሉ መሆናቸው በተለያዩ ዘገባዎች ሲገለጽ ቆይቷል።  ምንም እንኳን መንግስት በጦርነቱ ለደረሱ አስከፊ ክስተቶች እና ጉዳቶች የሚያደርገው ድጋፍ የሚበረታታ ቢሆንም ተጠያቂነትን ከማሰፈን አንፃር እና በክልሉ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በየጊዜው ግልጽ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በክልሉ ያለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሴቶች ለአሥገድዶ መድፈር ፣ በርካታ ዜጎች ደግሞ ለዝርፊያ እና ግድያ የተዳረጉበት መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል። ስለሆነም መንግስት የተፈፀሙትን ጥሰቶች በማንና እንዴት እንደተፈፀሙ፤ የጉዳቱን  መጠን እንድሁም ተጎጅዎች በገለልተኛ አካል የተጣራ እውነታን እንድያውቁ እና ተገቢውን ካሳ እንድያገኙ ለማስቻል ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን ማቋቋም ያስፈልጋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጋር ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚደረገው የጣምራ ምርመራና ማጣራት የሚበረታታ ነው፡፡

በሌላ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ደግሞ መንግስት በወለጋ-ጉሊሶ፣ በአጣየ እና አካባቢው እንድሁም በማይካድራ የተፈፀሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተለይም ከ700 በላይ የሰው ህይወት የጠፋበትን የማይካድራ ክስተት በትኩረት እንዲጣራ እና ይህንን አለም አቀፍ ወንጀል የፈፀሙ እንድታወቁ ፣ ለፍርድ እንድቀርቡ እና ተጎጅዎች እውነታውን የማወቅ እንድሁም መልሶ የመቋቋም እድል እንድያገኙ ገለልተኛ አጣሪ ጉባኤ በማቋቋም አሥፈላጊውን እንቅሥቃሴ ሊያደርግ ይገባል።

 

የማጠቃለያ ሃሳቦች

መንግስት ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን ሲያቋቁም ልብ ሊላችው የሚገቡ መርሆች አሉ፡፡ ከላይ በተጠቀሱት አስከፊ የመብት ጥሰቶች ዙሪያ ገለልተኛ አካል እንዲያጣራ መንግስት በመጀመሪያ ደረጃ ቁርጠኛ የፖለቲካ ውሳኔ መኖር ማለትም የሚወጡ የአጣሪ ኮሚሽን ሪፖርቶችን ለህዝብ ይፋ የማድረግ እና ውሳኔዎችን መሰረት በማድረግ ተጠያቂነትን የማስፈን ሂደት እና ግንዛቤ መኖር ሲሆን፣ ሁለተኛ: ለአጣሪ ኮሚሽኑ በቂ ሀብት መልቀቅን ይመለከታል። ሶስተኛ: ነፃ ፣ገለልተኛ እና ብቁ ባለሙያዎችን እንድካተቱ ማድረግ እንድሁም የሚቋቋመው ኮሚሽን በመርህም በተግባርም ነፃ እና ገለልተኛ እንድሆን ማድረግ ነው። በመጨረሻ አጣሪ ኮሚሽኑን እንደ መንግስታዊ ተጠያቂነትን የማምለጫ መንገድ አለመጠቀም እና ሌሎችም ናቸው፡፡

በአጠቃላይ በሀገራችን የተከሰቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አይነት፣ መጠንና በሰብአዊ መብቶች ጥሰት የተሳተፉትን ለማወቅ እንድሁም የዜጎችን ሰብአዊ መብት መከበር ለማረጋገጥ ገለልተኛ የሰብአዊ መብት አጣሪ ጉባኤ ማቋቋም ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን፤ ገለልተኛ አጣሪ ጉባኤ በተወሰኑ ቦታዎች ለተከሰቱ ጥሰቶች ወይስ እንደሃገር የተከሰቱትን የሰብአዊ መብቶች ቀውስ በአጠቃላይ ለማጣራት የሚለው ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው::

ምንጭ – ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጲያ  መጽሔት

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *