ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ በአሁኑ ወቅት ወደ አጎራባች ክልሎች የተዛመተው ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ከባድ ቀውስን በማስከተሉ የአገሪቱን ህልውና ፈተና ላይ ጥሎታል በሚል ስጋታቸውን የሚገልጹ ወገኖች አሉ።
ሌሎች ደግሞ ይህ ቀውስ በአግባቡ ከተያዘና ተገቢው መፍትሔ ከተገኘለት ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ የገጠሟትን የተለያዩ ፈተናዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ዕድልን ይፈጥርላታል ሲሉ ይሞግታሉ። ይህ በፌደራል መንግሥቱና በህወሓት መካከል ለሦስት ዓመታት ያህል ሲብላላ የቆየን አለመግባባት የኮሮናቫይረስ ክስተትን ተከትሎ ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የታሰበው አገራዊ ምርጫ በመራዘሙ ሳቢያ እየተካረረ በመሄድ ከማይመለስበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
በምንም ሁኔታ ውስጥ ምርጫው መካሄድ አለበት ሲል የቆየው ህወሓት፣ በክልሉ ውስጥ ምርጫውን የሚያስፈጽም አካል አደራጅቶ የተናጠል ምርጫ ማካሄዱን ተከትሎ ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር የነበረው ግንኙነት ተቋረጦ የክልሉ አስተዳደር ፍጥጫ ውስጥ ገብቶ ነበር። ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥትን በበላይነት ሲመራ የቆየው ህወሓት፣ በአገሪቱ የለውጥ እንቅስቃሴ ከተጀመረ በኋላ ከማዕከል ከመራቁ በተጨማሪ የሚወስዳቸው እርምጃዎች የተናጠል እንደነበሩ ነዋሪነታቸውን በለንደን ያደረጉት የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አቶ አብዱራህማን ሠይድ ይናገራሉ።
“ባለፉት ሦስት ዓመታት ህወሓት ይወስዳቸው የነበሩ እርምጃዎችና ያሳያቸው የነበሩት ባህሪያት በኢትዮጵያ የፌደራል አስተዳደር ውስጥ ያለ ክልል ሳይሆን የአንድ ነጻ መንግሥት ድርጊቶች ነበሩ” ይላሉ። ለዚህም በሕግ የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ አለመስጠት፣ የመከላከያ ኃይሉን እንቅስቃሴ መገደብና የተናጠል ምርጫ አደራጅቶ ማካሄድን እንደ አብነት ይጠቅሷቸዋል።
“እነዚህና ሌሎችም ሁኔታዎች የጊዜ ሁኔታ እንጂ አሁን ወደ ተከሰተው አውዳሚ ጦርነት እንደሚገባ ይደረጉ የነበሩ ዝግጅቶችን ያመለክቱ ነበር” በማለት በነበረው ሁኔታ ጦርነቱ አይቀሬ እንደነበር በወቅቱ መስተዋሉን አቶ አብዱራህማን ያብራራሉ። ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት በነበሩት ጊዜያት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የታዩት አለመግባባቶች ለይቶላቸው ይፋ መውጣት የጀመሩት፤ ህወሓት በበላይነት ሲመራው የነበረው ኢህአዴግ ከስሞ የብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተ በኋላ ነበር።
የፌደራል መንግሥቱ በመጀመሪያው የለውጥ ወቅት የህወሓት አፈንጋጭነት ለማስተካከል የነበረውን ዕድል አልተጠቀመበትም የሚሉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩና ተመራማሪው ውሂበእግዜር ፈረደ (ዶ/ር) ናቸው። “መንግሥት በለውጡ ጅምሬ ወቅት የነበረውን ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ በመጠቀም የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ችግሩ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ እንዳይደርስ የማድረግ ዕድል ነበረው” ይላሉ።

የጦርነቱ መስፋፋት
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች ትግራይ ውስጥ በነበረው የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ የተቀሰቀሰው ጦርነት በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በመንግሥት ቁጥጥር ስር እንድትገባ ማድረጉ ይታወሳል። ነገር ግን የደፈጣ ጥቃቶችና ውጊያዎች በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ከተሞች ራቅ ባሉ ስፍራዎች ለወራት መካሄዳቸውን ተከትሎ ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል።
ጦርነቱ እየተራዘመና መልኩን እየቀየረ በመጣበት ጊዜ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና አገራት በተለያየ መልኩ ጫና ለማሳደር ሞክረዋል። በተለይም ጉዳዩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ በተደጋጋሚ መነሳቱ አነጋጋሪ እንዲሆን አድርጎታል። በዚህ ሁሉ መካከል በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ መንግሥት በትግራይ ክልል የሚገኙ አርሶ አደሮች ሰላም አግኝተው በክረምቱ ወቅት የግብርና ሥራቸውን እንዲያከናውኑ በሚል የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ቢያስወጣም ጦርነቱ ቀጥሏል።
ለስምንት ወራት ያህል በትግራይ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት የህወሓት አማጺያን በሚፈጽሟቸው ተከታታይ ጥቃቶች የተነሳ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ መልኩን ቀይሯል። የህወሓት ኃይሎች ወደ ሁለቱ ክልሎች ዘልቀው በመግባት የተለያዩ ቦታዎችን እየያዙ ባሉበት ሁኔታ ኃይሎቻቸውና ሕዝቡ አማጺያኑን እንዲከላከሉ በይፋ የክተት ጥሪ አውጀዋል። በተጨማሪም ሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ልዩ ኃይሎቻቸውን ወደ ጦርነቱ ስፍራ ድጋፍ ለመስጠት ልከዋል።
በቅርቡ ከቢቢሲ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የህወሓት ቃል አቀባይ ሁለቱም ጦርነቱን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። አቶ ጌታቸው ረዳ “በትግራይ ላይ የተጣለው ከበባ እስኪነሳ ትግላችን ይቀጥላል” ሲሉ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር) በበኩላቸው “ሕዝባችንን ከታወጀበት ጦርነት መከላከላችንን እንቀጥላለን” ብለዋል። ይህም በአሁኑ ሰዓት ከትግራይ አልፎ በጎረቤት ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት በአጭር ጊዜ የሚቆም አያስመስለውም።
የውስጥና የውጪ ጫና
በትግራይ የጀመረው ጦርነቱ መስፋፋት፣ በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ያለው የአማጺያን እንቅስቃሴ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ የማኅበረሰቦች ግጭቶች ለዓመታት ሲደራረብ የመጣውን ችግር ከፍ ካለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል። በተጨማሪም ምዕራባውያን በጦርነቱ ምክንያት የተከሰቱ አሳሳቢ ሁኔታዎችን መሰረት አድርገው በአገሪቱ መንግሥት ላይ የሚያሳድሩት ጫና እንዲሁም በትግራይ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የሱዳን ሠራዊት አወዛጋቢ የድንበር አካባቢዎችን መቆጣጠራቸው ሌላኛው የአገሪቱ ፈተና ሆኖ ቆይቷል።
በተጨማሪ ደግሞ ላለፉት አስር ዓመታት ከግብፅና ከሱዳን ጋር ከመግባባት ሳይደረስበት የቆየውና ግንባታው ወደ መጠናቀቁ የተቃረበው የሕዳሴ ግድብ ጉዳይም ሌላኛው የኢትዮጵያ መንግሥት የገጠመው ውዝግብ ነው። ይህ ጦርነት በተቀሰቀሰበት ጊዜ ከውስጥም ሆነ ከውጪ የሚመጣው ጫና የሚጠበቅ መሆኑን የፖለተካ ተንታኞቹ ውሂበእግዜር (ዶ/ር) እና አቶ አብዱራህማን ያምናሉ። በአገሪቱ ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮችን ሁሉም ወገን ለራሱ ጥቅም ሊያውለው የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ እንደሆነ ያመለክታሉ።
መስቀለኛ መንገድ?
የጦርነቱ መስፋፋት እና ለረጅም ዓመታት ሞቅ ቀዝቀዝ ሲል የነበረው የብሔር ግጭት እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የሸማቂዎች እንቅስቃሴ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ከፍ ያለ ስጋት ያላቸው ወገኖች ጥቂት አይደሉም። አንዳንዶች እንዲያውም ዩጎዝላቪያን እንደምሳሌ በማንሳት ችግሩ በቶሎ መፍትሔ አግኝቶ አገሪቱ ወደ መረጋጋት መመለስ ካልቻለች መበተን ሊከሰትና ይህም ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን ወደ ቀውስ ሊከተው እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።
የቀድሞው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደርና በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት ቲቦር ናዥ ግን ኢትዮጵያና ዩጎዝላቪያ የተለያየ ታሪክ ያላቸው በመሆኑ የተባለው ነገር አይከሰትም ይላሉ። ናዥ ትዊተር ላይ እንዳሰፈሩት ኢትዮጵያ ልትበተን ትችላለች የሚሉ ሰዎች እንደተሳሳቱ በመግለጽ ለዚህም የሁለቱ አገራትን ታሪክ ያጣቅሳሉ።
“ዩጎዝላቪያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊዎች የተፈጠረች አገር ስትሆን፤ ኢትዮጵያ ግን ከሁለት ሺህ ዓመት በላይ የቆየ ታሪክ ያላትና በርካታ ችግሮችን ያለፈች ናት” ብለዋል። የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ አብዱራህማን በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተከሰተው ቀውስ አገሪቱን መስቀለኛ መንገድ ላይ አቁሟታል ይላሉ። አሁን መደረግ ያለበት አገሪቱን ወደ መፍረስ እንዳትሔድ የሚያደርጉ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሆነም ይመክራሉ።
“ለዚህ ደግሞ የአገሪቱን አንድነት የሚያስጠብቁና አብዛኛውን ሕዝብ ሊያስማሙ የሚችሉ የለውጥ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል” በማለት አስፈላጊም ከሆነ የፌደራል አስተዳደሩን በማጠናከር የሕገ መንግሥት ማሻሻያም ሊደረግ ይችላል ይላሉ። ኢትዮጵያ ህልውናዋ ላይ አደጋን የጋረጡ በርካታ መስቀለኛ ሁኔታዎች እንዳጋጠሟት የሚናገሩት ደግሞ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ውሂበእግዜር ፈረደ (ዶ/ር) የአሁኑ ክስተት ከመስቀለኛ ሁኔታም ያለፈ ነው ይላሉ።
“አገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት ሲባል ረጅም ጊዜ ቆይቷል፤ አሁን ግን ኢትዮጵያ ከመስቀለኛው መንገድ አልፋ አደገኛ ወደ ሆነ እጥፋት (Turning point) አምርታለች” በማለት ግምገማቸውን ያስቀምጣሉ። ጨምረውም ይህ አደገኛ ጉዞ አሁን ተፈጥረዋል በሚሏቸው አንዳንድ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ሊቀለበስ ካልቻለ የአገረ መንግሥት መክሰም ወይም ውድቀት ሊከሰት ይችላል በማለት ስጋታቸውን ውሂበእግዜር (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በአገሪቱ ለዘመናት የዘለቁ በርካታ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ቢኖሩም አብዛኛው ማኅበረሰብም ሆነ ክልል የኢትዮጵያን እንደ አገር መፍረስን የሚፈልግ አይኖርም ብለው የሚያምኑት አቶ አብዱራህማን ሠይድ፤ “ላሉ ችግሮች መፍትሔ በማበጀት አገሪቱ ተጠናክራ እንደትቀጥል ማድረግ የሚቻልበት ዕድል አለ” ይላሉ። በአገሪቱ ህልውና ላይ አደገኛ ሁኔታ መደቀኑን የሚናገሩት ውሂበእግዜር (ዶ/ር) አሁን የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ግን በሕዝቡ ውስጥ “አገር ለማዳን በጋራ የመቆም ሕዝባዊ ንቅናቄ እንደተፈጠረ ይታያል። ይህም በአግባቡ ከተያዘና ከተመራ አገሪቱ ከገባችበት ችግር ለማውጣትና አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር ይቻላል” ሲሉ ያላቸውን እምነት ይገልጻሉ።
በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ መሰረት አዲሱ መንግሥት ሲመሰረት ሁሉን አሳታፊ እንዲሆንና በተለያዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ ላሉ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት፣ አሁን የተጀመረውን አገራዊ ስሜት በማጠናከር አገሪቱ ያጋጠማትን ቀውስ መቀልበስ እንደሚቻል ይጠቁማሉ። “ለዚህ ደግሞ በአገሪቱ ህልውና ላይ አውንታዊ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ ወገኖች በጋራ ሆነው ኢትዮጵያ ወዴት እና እንዴት በሚለው ላይ መግባባትን በመፍጠር፤ በጋራ አስተሳሰብና ራዕይ ሕዝቡን ማንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው” በማለት ዶ/ር ውሂበእግዜር ፈረደ አጽንኦት ይሰጣሉ።