ሰኔ 14 በተደረገው ብሔራዊ ምርጫ ባልተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች መስከረም 20 ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትናንትናው ዕለት በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
በነዚህ የምርጫ ክልሎች ከሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላም እዚህ ውሳኔ ላይ መደረሱ ተገልጿል። ምርጫው የሚከናወነው በሶማሌ፣ በሐረሪ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ነው ። ከዚህም በተጨማሪ ለሰኔ 14 ሊደረግ የነበረውና የተራዘመው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔም መስከረም 20 እንደሚካሄድ ከምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር ባደረገው ውይይት አገሪቱ አሁን ካለችበት አንጻር ምርጫ ማድረጉ ተገቢ አይደለም በማለት አስተያየት የሰጡ መኖራቸው ተጠቁሟል። ነገር ግን ሰኔ 14 የተደረገውም ምርጫ በተመሳሳይ የፀጥታ ችግር በነበረበት ሁኔታ መካሄዱን ጠቅሰው የመስከረም 20ም ምርጫ የተሻለ ፀጥታ ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት ማካሄድ ይቻላል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የምርጫው ቀን በክርስትና እምነት ዘንድ ለሚከበረው መስቀል በዓል የቀረበ በመሆኑ ማሻሻያ ይደረግም ብለው የተናገሩ መኖራቸው ተገልጿል። ስድስተኛው አጠቃላይ ብሔራዊ ምርጫ በዋናነት ሰኔ 14፣ 2013 ዓ.ም የተካሄደ ቢሆንም በጸጥታ ችግር፣ በመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ በታዩ ግድፈቶች፣ በመራጮች ምዝገባ ላይ በቀረቡ አቤቱታዎችን ለማጣራት ጊዜ በማስፈለጉ የድምፅ መስጫው ቀን በአንዳንድ ክልልሎችና የምርጫ ክልሎች እንዲራዘም መወሰኑ ይታወቃል።
ከዚህ በተጨማሪ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ ላይ ጉልህ የአሰራር ችግር በማየቱ ማጣራት እንዲካሄድ የወሰነባቸው ቦታዎችም እንዲሁ ምርጫው እንደማይከናወን ማስታወቁ ይታወሳል። ከዚህም በተጨማሪ በቀሪ የምርጫ ክልሎች ላይ የሚኖረውን ሂደት አስመልክቶ ቦርዱ ተጨማሪ መረጃዎችን እንደሚሰጥም በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ምንጭ – ቢቢሲ