የመብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዋች ከቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ ከወራት በፊት ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር በተያያዘ በትግራይ ተወላጆች ላይ ከሕግ ውጪ አስርና እንግልት እየደረሰ መሆኑን አመልክቷል።

በዚህም መንግሥት ያሉበት ያልታወቁ የትግራይ ተወላጆችን ሁኔታ እንዲያሳውቅ ያለ በቂ ማስረጃ የታሰሩትም እንዲፈቱጠይቋል። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን (ኢሰመኮ) ጨምሮ ሌሎች የሰብአዊ መብት ተቋማት ቀደም ብለው ስጋታቸውን ገልጸው ነበር።

ይሁን እንጂ መንግሥት ማንኛውንም ግለሰብ በማንነቱ ምክንያት እንዳላሰረና እንግልት እንዳልደረሰ በመግለጽ የታሰሩ ሰዎች የሚባሉትም “የአማጺውን የህወሓትን አላማ በመደገፍና በተለያዩ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ” መሆናቸውን በመግለጽ የሚሰነዘረውን ክስ አጣጥሏል። በአገሪቱ ውስጥ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ግጭቶች ሲከሰቱ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችና እንግልቶች በተደጋጋሚ ሲከሰቱ መቆየታቸው አይዘነጋም።

በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ “ከሌሎች ክልሎች የመጡ” በሚባሉ ዜጎች ላይ በቡድኖች፣ በግለሰቦችና አንዳንድ ጊዜም በጸጥታ ኃይሎች የሚፈጸሙ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ከስተቶች ናቸው። በዚህም ሳቢያ በርካቶች ተገድለዋል፣ ቤት ንበረታቸውን አጥተዋል፣ ከኖሩባቸው አካባቢዎች ለመፈናቀልም ተዳርገዋል።

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በተከሰተው የኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር ጦርነት ወቅትም በኢትዮጵያ ለዘመናት ወልደው ከብደው ሲኖሩ የነበሩ ኤርትራውያንም ሀብና ንብረታቸውን ሳይዙ ከአገር እንዲወጡ መደረጋቸው ይታወሳል። በወቅቱ በአዲስ አበባ ሲኖር የነበረው የፋርማሲ ባለሙያው ዳኒኤል ተኽለ ይህ ድንገተኛ ክስተት “ዝናና ደስታ፤ ነጻነትና ዝምታ” በሚለው በትግርኛ መጽሐፉ ላይ አስፍሮታል።

የጸጥታ ኃይሎች “ምሽት ሦስት ሰዓት መጡ” የሚለው ዳንኤል፤ “የውጭ በር በኃይል ተንኳኩቶ ስከፍት መኝታ ቤቴ ድረስ ተከትለውኝ ገቡ። አንድ ወይም ሁለት ቅያሪ ልብስ እንድይዝ ነገሩኝ። ትንሿ ልጄ ተኝታ ስለነበረ ደንግጣ እንዳትነሳብኝ ያሉኝን አድርጌ ልወጣ ስል ልጄ ተነስታ ቤተሰብ እያለቀሰ ትቻቸው ወጣሁ” ሲል ያስታውሰዋል። በነጋታው በአንድ አዳራሽ የተሰበሰቡ ኤርትራውያንን ስማቸው ተመዝግቦ በቀጣዩ ቀን ከሰላሳ በላይ አውቶብሶች ተዘጋጅተው ከአዲስ አበባ ሲወጡ፣ ብዙ ሰዎች በእንባና በሀዘን ተሰናበቸው።

ደሴ ሲደርሱ የከተማዋ ነዋሪ ምግብና ውሃ አቀረበላቸው። ሆኖም ሁሉ ትቶት የመጣውን ንብረቱን እና ቤተሰቡን እያሰበ ለምግብ የሚሆን መነሳሳት አልነበረውም። በዚህ ሁኔታ መቀለ ደረሱ፤ የከተማዋ ሕዝብ በዋና መንገዶች ተሰልፎ ይህንን አስከፊ ታሪካዊ ክስተት ሲፈጸም አይቷል። አድዋ ሁለት ሌሊት ሲያድሩ አንዳንድ የአገር ሽማግሌዎች “ምንድን ነው እየሆነ ያለው? በሕዝቡ መካከል ጥላቻ አትትከሉ፤ እባካችሁ ሰላማዊ ሰዎችን አታስወጡ” ማለታቸውን ሰምቷል።

በጉዞው መካከል “. . .ከመካከላችን ተጠርተው የሄዱና ያልተመለሱ ሰዎች አሉ” የሚለው ዳንኤል መጽሐፉ ላይ ያሰፈረውም ይህንኑ እንደሆነ ይናገራል።

የኤርትራ መንግሥት ምን አደረገላቸው?

እያንዳንዱ ተባሮ የመጣ ሰው ብረት ድስት እና 1500 ናቅፋ [በወቅቱ ምንዛሬ 20 ዶላር] ብቻ ይሰጠው ተብሎ ተወሰነ። ተፈናቅሎ የሄደው ሰው ግን መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት የፋይናንስ ተቋማት የምንቋቋምበት ብድር ይሰጡናል የሚል ተስፋ ነበራቸው፤ ግን አልሆነም። አንድ ቀን ይላል ዳንኤል፤ የመንግሥት ባለስልጣናት ሁሉንም ከኢትዮጵያ የመጣው ሰው አዳራሽ ላይ ሰብስበው “ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሰማርታችሁ ስኬታማ ነበራችሁ፤ እዚህም በሥራችሁ እንደሚሳካላቹ እናምናለን። ሆኖም መንግሥት ሌላ ትኩረት የሚያደርግበት ጉዳይ ስላለ ልናግዛችሁ አንችልም” አሏቸው።

ከዚህ በኋላ የንግድ ፍቃድ ለማውጣት በተንቀሳቀሰበት ወቅት ብዙ እንግልት እንደደረሰበት ዳንኤል ይናገራል። በየቢሮው የገጠመው ሙስና ቢያደክመውም የንግድ ፍቃድ ተሰጥቶት መድኃኒት ቤት ከከፈተ በኋላ የአገራዊ አገልግሎት ጥሪ መጣ። በዚህም ከባድ ጊዜ አሳልፎ፣ በብዙ ጥረት የትምህርት እድል አግኝቶ ከኤርትራ ወጥቶ አሁን ኑሮውን በአሜሪካ አድርጓል።

በማኅበረሰቡ መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች

ፕሮፌሰር ጋይም ክብረአብ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ኤርትራውያን ባለሀብት፣ አንዳንዶቹ የሚለብሱትም ሳይዙ፣ ለዓመታት ያፈሩት ንብረት ሳይሰበስቡ ልጆቻቸውና ሚስቶቻቸው ትተው ተባረዋል ይላል። የተለያየ የጤና ቀውስ አስከትሎባቸው በብስጭት የሞቱ ጥቂት አለመሆናቸው ያስታውሳል።

ፕሮፌሰር ጋየም፣ አሁን በኢትዮጵያ በትግራይ ተወላጆች ላይ እያጋጠመ ያለውና እሱ ያለፈበት ሁኔታ ቢለያይም እንኳ በትግራይ ተወላጆች ላይም ይሁን ሌላው ብሔር ላይ ማንኛውም አይነት ግፍ እንዳይፈጸም መከላከል ይገባል ይላል።

“በማንኛውም ቦታ ይሁን ክልል በሰላማዊ ሰዎች፣ ሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰው ግፍ ሊወገዝ ይገባል” ሲልም ያስረዳል። “ምን ማን ላይ ደረሰ ሳይሆን በመሰረቱ ተግባሩ ነው ሊኮነን የሚገባው። ችግሩ መሪዎች የሚፈጥሩት እንጂ ሕዝቡ ተጋብቶ የሚኖር ነው።” ለዚህም ለ20 ዓመታት ተዘግቶ የነበረው የሁለቱንም አገራት ድንበር ሲከፈት የነበረው የኤርትራና የትግራይ ሕዝቦች ፍቅርና ደስታን በአብነት ያነሳል።

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው አቶ መለስ ዜናዊ ኤርትራውያን ከአገሪቷ መባረራቸው በተመለከተ ‘ኤርትራዊ ይሁን ሌላ የአይኑ ቀለም አልማረከንም ካልን ያለው አማራጭ መውጣት ብቻ ነው’ የሚለው ንግግሩ አሁንም የደረሰውን ግፍ የሚያስታውስ በመሆኑ መሪዎች በሕዝቦች መካከል ጥላቻ ከሚፈጥር ንግግር እንዲቆጠቡ ይመክራል።

ኤርትራ ነጻነቷን ካገኘች በኋላ እንዲሁም በድንበር ጦርነቱ ወቅትም የኤርትራ መንግሥት በአገሩ ሲኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ከቤት ንብረታቸው በማፈናቀል ወደ ኢትዮጵያ እንዳባረረ በስፋት ይነገራል። አንዳንዶቹ ሊደርስባቸው ከሚችለው ጥቃት ነፍሳቸውን ለማዳን በቀይ መስቀል ተመዝግበው ወደ አገራቸው የተመለሱ እንደነበሩ በመግለጽ “ማን የት አደረገው ሳይሆን በማንነት ምክንያት የሚደርሰው በደል ሊወገዝ ይገባል” ሲል ፕሮፌሰር ጋይም ይገልጻል።

ዳንኤል በበኩሉ ኤርትራውያን ከትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ከኦሮሞና አማራ፣ ከሱዳንና ጁቡቲ . . . ከሁሉም ሕዝቦች ጎረቤት የሆንን አንድ አካባቢ ያለን በመሆናችን በሰላምና በመከባበር ልንኖር ይገባል ሲል ይመክራል። “በስደት ከኢትዮጵያውያን ጋር ይሁን ሌላ እንደ ጓደኛ አብረን እየኖርን፣ ለምን አገራችን ላይ በጦርነትና ግጭት የኋላ ቀር ምሳሌዎች እንሆናለን?” ሲልም ይጠይቃል።